የወያኔ አገዛዝ የአዲስ አበባን ህዝብ ለመበዝበዝ የሚያደርገው ስንድት ምሬት ቀሰቀሰ

የአዲስ አበባ መስተዳደር፥ የመጪው አምስት አመታት እቅዱን በገንዘብ በመደገፍ ስም ነዋሪው ስድስት መቶ ሚሊዮን ብር እንዲያዋጣለት እቅድ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ተዘግቧል።

የግንቦት 7 ድምጽ ሪፖርተር ከአዲስ አበባ በላከው ተከታይ ዘገባ፥ አንዳንድ ነዋሪዎች፣ “ልጆቻችንን የምናበላው አጥተን ባለንበት ዘመን ከየት አምጥተን እንድንሰጣቸው ፈለጉ?” ሲሉ ተደምጠዋል። በከተማይቱ ውስጥ ሰባት መቶ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ማእከላት መመስረታቸውን የገለጸው ዘጋቢ፤ ነዋሪዎች ስብሰባ ቢጠሩም ከካድሬዎች በስተቀር አብዛኛው ህዝብ እንዳልተገኘ አመልክቷል።

የአዲስ አበባ የገቢ ቢሮ፥ ህዝቡ ገንዘቡ ምን አይነት ጥቅም ላይ እንደሚውል እና በአግባቡ ጥቅም ላይ መዋሉን እንዲረዳ የከተማይቱን በጀት በዝርዝር ለህዝብ ማሳወቁን ተናግሯል። ይሁን እንጂ፥ ይህንን በሚመለከት ዘጋቢያችን ያናገራቸው ዜጎች፣ ይህ አገዛዙ ተጠያቂነት እንዳለ በማስመሰል ህዝቡን ለመዝረፍ ያዘጋጀው ማታለያ ነው ብለዋል።

የሚሰጡት ገንዘብ እንደሌላቸው የሚናገሩት ነዋሪዎች፤ ኖሯቸው ቢሰጡ እንኳ የት እንደሚሄድ እንደሚያውቁ እና ያም ወደካድሬዎቹ ኪስ ነው ሲሉ ገልጸዋል። ከዚህ የሚጠቀሙት የወያኔ ካድሬዎች ራሳቸው ስለሆኑና፣ የህዝብን ሃብት በመበዝበዝ የከበሩትም እነሱው በመሆናቸው፤ አስተዳደሩ እነሱኑ ቢጠይቅ ይሻለዋል ሲሉም አስተያየት ሰንዝረዋል።