ዘረኛው እና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ ሲገለበጥ በትግራይ ተወላጆች ላይ ሊደርስ የሚችለው አደጋ ስጋት እየፈጠረ ነው

ጄኖሳይድ ዋች የተባለው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ፕሬዚደንት የሆኑት ዶ/ር ግሬጎሪ ስታንተን፤ በዋሽንግተን ዲሲ የሰማእታት መታሰቢያ ዝግጅት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፣ የወያኔ አገዛዝ ሲወድቅ ለወንጀሉ የሚከፍለው የትግራይ ህዝብ እንዳይሆን እሰጋለሁ ብለዋል።

“ከጥንት ስልጣኔዎች ውስጥ አንዷ የሆነችው ኢትዮጵያ፤ በአሁኑ ሰዓት በአረመኔያዊ አገዛዝ እየተመራች ነው” በሚል ንግግራቸውን የጀመሩት ዶ/ር ግሬጎሪ፤ አሁን ያለው ሁኔታ የትግራውያን የበላይነት የተረጋገጠበት በመሆኑ፤ ለዚህ የሚከፍሉት እና የሚጠሉት የትግራይ ተወላጆች ናቸው ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ዘረኛውና አምባገነናዊው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ፤ በተወሰኑ ምርጥ ትግራውያን ድጋፍ በኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈጽመው ግፍ እና ዘረፋ እየፈጠረ ያለው ቁጣ ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ እንደሄደ አሰተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ። በርካታ ኢትዮጵያውያንም፣ የትግራይ ምሁራን ለነፃነት የሚደረገውን ትግል በጉልህ ሁኔታ ከወዲሁ ካልተቀላቀሉ፤ አገዛዙ ከስልጣን ሲወገድ ስሜታዊ የበቀል እርምጃዎች ሊቀሰቀሱ እንደሚችሉ ያላቸውን ስጋት ሲገልጹ ቆይተዋል።

ዶ/ር ግሬጎሪ፥ ከዚህ ቀደም በሩዋንዳ እና በቡሩንዲ ኖረው እንደሚያውቁ ገልጸው፤ ከአንድ ዘር ብቻ የተውጣጡ ልሂቃን አንድን አገር ሲቆጣጠሩ የሚደርሰውን አደጋ ለመመልከት እንደቻሉ በማስረዳት፤ አሁን የሚሰጉት ለማንም ሳይሆን ለትግራይ ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት የቀድሞ የመለስ ዜናዊ አማካሪ የሆኑት የትግራይ ምሁር ፕሮፌሰር ተኮላ ሃጎስ፤ የመለስ ዜናዊ አገዛዝ በኢትዮጵያ እና በህዝቧ ላይ የሚፈጽማቸውን ግፎች ያለ ትግራውያን እርዳታ ሊያደርገው ባልቻለ ነበር ሲሉ ብዙዎችን ያስገረመ ጽሁፍ አውጥተዋል። ፕሮፌሰሩ፥ የትግራይ ተወላጆች የተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያደርገውን ትግል በመቀላቀል ከወዲሁ ጎራ እንዲመርጡ ጥሪ አቅርበው እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም።