ፍኖት – የመኢአድ ላዕላይ ም/ቤት በሥራ አስፈጻሚው አብላጫ ድምጽ ውሳኔ ስብሰባ እንደሚጠራ ተገለፀ
በመላ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ ላዕላይ ም/ቤት ሥራ አስፈጻሚ መካከል በተፈጠረ አለመግባባት በሁለት ቦታ ተከፍሎ መቆየቱ ይታወቃል፡፡ የሁለቱንም አመራር አካላት አቤቱታ የተቀበለው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሁለቱም በጋራ በመሆን እስከ ህዳር 30 ቀን 2004 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤ ጠርተው አለመግባባታቸው በጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔ እንዲያገኝ መመሪያ ሰጥቶ ነበር፡ ፡ ዋናው ጽ/ቤት የሚገኘው በፓርቲው ፕሬዘዳንት ኢንጂነር ኃይሉ ሻወል የሚመራው አካል ምርጫ ቦርድ “በአዋጅ ከተሰጠው ሥልጣን በላይ በፓርቲው ጉዳይ ጣልቃ ገብቶብኛል፤ በፓርቲው ደንብ እንዳልመራ ተጽኖ እየፈጠረብኝ ነው፡፡ ጠቅላላው ጉባኤ የምጠራበት የደንብ አግባብ የለም፡፡ የፓርቲው ጠቅላላ ጉባኤ ከተደረገ አንድ ዓመት አልሞላውም፡፡ ፓርቲውን የሚበጠብጡት ፓርቲው ውስጥ ሰርገው የገቡ ናቸው፡፡ ከፊሎቹ በራሳቸው ጥያቄና በዲስፕሊን የተባረሩ ናቸው” በማለት ለጋዜጠኞች ገልፀዋል፡ ፡
በሌላ በኩል ከትላንት በስቲያ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ መኢአድ ጽ/ቤት በተከናወነ ስበሰባ የተለየ ሐሳብ ሲንሸራሸር መመልከት ተችሎአል፡፡ በስብሰባው ላይ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈጻሚ፣ የአዲስ አበባ መኢአድ ም/ቤት ሥራ አስፈጻሚ አምስት አባላት ያሉት የሽማግሌዎች ቡድን ለስብሰባው ሪፖርት አቅርበዋል፡፡ የአቃቂ ቃሊቲ ክ/ከ ሥራ አስፈጻሚ በስብሳቢያቸው አማካኝነት ባቀረቡት ሪፖርት ፓርቲው በአመራር ችግር አደጋ ላይ መውደቁን፣ የፓርቲው ዋና ፀሐፊ የ13 ወር የፓርቲው ጽ/ቤት ኪራይና የሥራ ማስኬጃ እንዳይሰጥ ማገዳቸውን፤ ጽ/ቤቱ እንዲዘጋ ትዕዛዝ መስጠታቸውን፣ ፓርቲው እንዲበተን እየተደረገ ነው” በማለት ሪፖርቱን አቅርቧል፡፡
የአዲስ አበባ መኢአድ ም/ቤት ተወካይ በበኩላቸው ባቀረቡት የሥራ ሪፖርት ኢ/ር ኃይሉ “እኔ የምላችሁን እንጂ እናንተ የምትሉትን አልቀበልም በማለታቸው ፓርቲው ውስጥ የተፈጠረውን ችግር በሰለጠነ መንገድ በውይይት መፍታት አልተቻለም፡፡ የፓርቲው ላዕላይ ም/ቤት ያወጣውን ደንብ አልቀበልም ብለው ራሳቸው ባወጡት ደንብ እየሰሩ ነው፡፡ የፓርቲውን ሥራ አስፈጻሚ የምመርጠው እኔ ነኝ፡፡ በፈለኩ ጊዜ ደግሞ አባርራለሁ፡፡ የዞን ተጠሪዎችን የምመድበው እኔ ነኝ፡፡ ላዕላይ ም/ቤት ያወጣውን ደንብ አልቀበልም ብለዋል” ሲሉ ገልፀዋል፡ ፡ ጉዳዩን በውይይት ለመፍታት አምስት አባላት ያሉት የሽማግሌዎች ቡድን ተቋቁሞ በራሳቸው ገንዘብ ረጅም ጊዜ ሙከራ አድርገው እንዳልተሳካላቸው ተገልጻóል፡፡
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ መኢአድ ጽ/ቤት ማህተም በአዲስ አበባ መኢአድ ም/ቤት ም/ሰብሳቢ በአቶ ማሙሸት መኮንን ፊርማ የተጠሩ ጋዜጠኞች በስብሰባው ላይ ተገኝተው የስብሰባውን ሂደት ተከታትለውታል፡፡
ባለፈው የፓርቲው ላዕላይ ም/ቤት ተመርጠው ከነበሩት ሥራ አስፈጻሚዎች ውስጥ ሰባት አባላት የተገኙ ሲሆን ሁለቱ በተለያየ ምክንያት በዕለቱ አለመገኘታቸውን ገልፀዋል፡፡ ሥራ አስፈጻሚውን ወክለው ለተሰብሳቢዎቹ አስተያየት እንዲሰጡ የተጋበዙት አቶ ማህተመ በኩረ እንደገለጹት “ፓርቲው ይበተናል ብላችሁ አትስጉ፡ ፡ ፓርቲው አይበተንም፡፡ እስከ አሁን ድረስ ፕሬዝዳንቱ ከስህተታቸው ይመለሳሉ ብለን ከፍተኛ ጥረት አድርገናል፡ ፡ እሳቸው ፍቃደኛ አልሆኑም፡፡ እስከ ህዳር 30 ቀን 2004 ዓ.ም በጋራ ጠቅላላ ጉባኤ እንድንጠራ ተወስኖ እንቢተኛ ሆነዋል፡፡ የፓርቲው ደንብ አይገዛኝም ብለው ቀጥለዋል፡ ፡ እኛ በፓርቲው ደንብ እንሠራለን፡፡ በተሰጣቸው እድል ተጠቅመው የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባኤ ካልጠሩ እኛ ከህዳር 30 በኋላ በፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ አብላጫ ድምጽ ላዕላይ ም/ቤቱን እንጠራለን፤ በላዕላይ ም/ቤቱ ውሳኔ ደግሞ ጠቅላላ ጉባኤውን አጣርተን አስፈላጊውን ውሳኔ እናሰጣለን፡፡ ፓርቲው የሚበተንበት ሁኔታ አይኖርም” በማለት ተናግረዋል፡፡
የአንድነት ፓርቲ ለሕዝብ መብት መከበር የቆመ፣ በአገር ዉስጥ በሰላም የሚታገል ፣ በአገር ቤት ኢትዮጵያዉያንን ለማደራጀት የሚንቀስቀስ የሰለጠነ ሰላማዊ የፖለቲካ ድርጅት ነዉ። ሕዝቡን ለማስተማርና ለማንቃትም በየሳምንቱ የፍኖት ጋዜጣን አትሞ ያስራጫል። የፍኖት ጋዜጣን በብዛት ለማሳተምና በስፋት በየክልሎቹ ለማሰራጨት ከፍተኛ የገንዝብ አቅም ይጠይቃል። በአገር ቤት ከሚታገሉ ወገኖቻችን ጎን ይቁሙ ! በገንዘብዎት የአንድነት ፓርቲን ይደግፉ !
ፍኖት እትም 19ን በሙሉ ለማንበብ ከዚህ ይጫኑ !