ፍኖት – እነ አንዱዓለም አራጌ የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለፍ/ቤት ሰጡ

“በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሠላማዊ ትግል ለማፈን የተሠራ ድሪቶ ነው”
አንዱዓለም አራጌ

“የሚነገረው ድርሰት ነው ሠላማዊ ትግል ወንጀል ካልሆነ በስተቀር ወንጀል አልፈፅምኩም”
ናትናኤል መኮንን

“የፃፉትን ተረታ ተረቶች አልፈፀምኩም”
ክንፈሚካኤል ደበበ

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ /አንድነት/ም/ሊቀመንበርና ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ የአንድነት ማዕከላዊ ም/ቤት አባል ናትናኤል መኮንን፣ ዮሐንስ ተረፈ፣ የሸዋስ ይሁንዓለም /ሻምበል/፣ ክንፈ ሚካኤል ደበበ፣ ምትኩ ዳምጤና ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ረቡዕ ዕለት ፍ/ቤት ቀርበው የእምነትና ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ ፍ/ ቤቱ ባለፈው ቀጠሮ በሰጠው ብይን መሠረት ዐቃቢ ህግ የተሻሻለውን ክስ አቅርቧል፡፡ የክስ ቻርጁ ለተከሳሾች እንዲደርስ ከተደረገ በኋላ ፍ/ ቤቱም ክሱን በንባብ አሰምቷል፡፡

ክሱ ከተነበበ በኋላ የ1ኛ፣የ2ኛ፣የ5ኛና የ7ኛ ተከሳሾች ጠበቃ ደርበው ተመስጌንና ጠበቃ አበበ ጉታ የክስ መቃወሚያ አቅርበዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ባቀረብነው የክስ መቃወሚያ ክሱ የሞተ የታገተ፣ የወደመ ንብረት አይገልጹም፡ ፡ ባለስልጣናትን ለመግደል በማሴር ይላል የትኛው ተከሳሽ ማንን ለመግደል እንዳሴረ ክሱ በግልጽ ባለመግለጹ የተከሳሾችን የመከላከል መብት ያጠባል፡፡ በማለት ተቃወመውታል የ3ኛ የ4ኛ የ6ኛ የ8ኛ ተከሳሾች ጠበቃም ይኽው እንደመዘገብላቸው ጠይቀዋል፡፡

አቃቢ ሕግ በሕግ በሰጠዉ ቃቢ ህግ በሰጠው መልስ “ግንቦት ሰባት የተባለው አሸባሪ ድርጅት በ2003 ዓ.ም በመንግስት ባለስልጣናት ላይ ግድያ እንዲፈጸም አፈና እንዲከናወን ባንክ እንዲዘረፍ እቅድ ሲወጣ ተከሳሾች ተባባሪ ሆነው የሥራ ክፍፍል አድርገው አሲረው ነበር፡፡ ድርጊቱ ተፈጽሟል አልተባለም፡፡ ለመፈፀም አቅደው ነበር ነው የሚለው ክሱ” በማለት መልስ ሰጥቶአል፡፡ የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ፍ/ቤት ክሱ በቀረበው ሁኔታ እንዲቀጥል ብይን በመሰጠቱ የክስ ማየቱ ሂደት ቀጥሎአል፡፡ በዚሁ መሠረት የእምነት ክህደት ቃላቸውን የተጠየቁት ተከሳሾች ለፍ/ቤቱ ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

1ኛ ተከሳሽ አንዱዓለም አራጌ የተከሰሱበትን ወንጀል ፈጽመዋል አልፈጸሙም ተብሎ ከፍ/ቤቱ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ “ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሠላማዊ ትግሉን ለማፈን የተወሰደ እርምጃ ነው፡፡ ወንጀል አልፈጸምኩም፡ ፡ 2ኛ ተከሳሽ ናትናኤል መኮንን በበኩሉ በሰጠው መልስ “የሚነገረውን ድርሰት አልፈጸምኩም፡፡ የተከሰስኩት በሠላማዊ ትግል በመታገሌ ነው፡፡ ሠላማዊ ትግል ወንጀል ከሆነ ብቻ ነው ወንጀለኛ የምሆነው ወንጀል አልፈፀምኩም”፡ ፡ ብሎአል፡፡ 5ኛ ተከሳሽ ክንፈሚካኤል ደበበ/አበበ ቀስቶ/ “የተጻፉትን ተረታ ተረቶች አልፈፀምኩም” ሲል መልስ ሰጥቷል፡፡ ተከሳሾች ወንጀሉን ፈጽሜአለሁ አልፈጸምኩም ጥፋተኛ ነኝ ጥፋተኛ አይደለሁም በማለት ብቻ መልስ እንዲሰጡ ተጨማሪ ቃላቶችን እንዳይጠቀሙ የፍትሐብሄር ህጉ እንደማይፈቅድ በተደጋጋሚ ፍ/ቤቱ በማዘዙ ሌሎች ተከሳሽ ጥፋተኛ አይደለሁም በማለት መልስ ሰጥተዋል፡፡

ዐቃቢ ህግ በበኩሉ “ማስረጃዎቻችንን ከክስ ማመልከቻ ጋር አቅርበናል፡፡ የሰው ማስረጃንንም እናቀርባለን” በማለት መልስ ሰጥቶአል፡፡ በመቀጠልም የተከሳሽ ጠበቆች ጠበቃ አበበ ጉታና ጠበቃ ደርበው ተመስጌን እንዲሁም ተከሳሾች ለፍ/ቤት የምናቀርበው አቤቱታ አለ በማለት አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ ጠበቆቹም ለፍ/ቤቱ ባቀረቡት አቤቱታ “የተከሳሾችን ህገመንግስታዊ መብት የሚጥስ አኬልዳማ የሚል ድርማ በማዘጋጀት እያሰሙ ነው፡፡ አንድ ሰው እስኪፈረድበት ድረስ እንደንጹህ ሰው የመታየት መብት አለው የሚለው ህገመንግስታዊ መብት እየተጣሰ ነው፡፡ ፍ/ ቤት የያዘውን ጉዳይ ፍትህ አካሉ ላይ ተጽኖ የሚያሳድር ሥራ እየተሰራ ነው”፡፡ በማለት ሲያመለክቱ ተከሳሾችም በጉዳዩ ላይ ሐሳብ መስጠት ሲጀምሩ ፍ/ቤቱ አቤቱታችሁን በጽሑፍ አቅርቡ፡፡ አሁን ፍ/ቤቱ በያዘው ቀጠሮ መሠረት በፍትሐብሄር ሥነ ሥርዓት ህጉ መሠረት አሁን መከናወን ያለበት ይሠራ”፡፡ በማለት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡

ሆኖም ግን 1ኛ ተከሳሽ አቶ አንዱዓለም አራጌ “እኔ ፍ/ ቤት ስቀርብ የመጀመሪያዬ አይደለም፡፡ ፍ/ቤቱ አቤቱታችንን ለመስማት ፍቃደኛ አይደለም፡፡ እየተፈጸመብን ያለውን በደልና የመብት ጥሰት ለማን እናመልክት? በማለት ሲናገር 5ኛ ተከሳሽና ሁለተኛ ተከሳሽም “የፍ/ቤቱን ሥልጣን የሚጋፋ የተከሳሾችንም ህገ መንግስታዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመብን ነው”፡፡ በማለት አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ ፍ/ቤቱም አቤቱታው በጽሑፍ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ከ9ኛ-24ኛ ተከሳሾች ባለመቅረባቸው ጥሪ ተደርጐላቸው ህዳር 27/2004 ዓ.ም እንዲቀርቡ ሲቀጠር መደበኛው ቀጠሮ ለታህሳስ 16 ቀን 2004ዓ.ም ተቀጥሮአል፡፡

የአንድነት ፓርቲ ለሕዝብ መብት መከበር የቆመ፣ በአገር ዉስጥ በሰላም የሚታገል ፣ በአገር ቤት ኢትዮጵያዉያንን ለማደራጀት የሚንቀስቀስ የሰለጠነ ሰላማዊ የፖለቲካ ድርጅት ነዉ። ሕዝቡን ለማስተማርና ለማንቃትም በየሳምንቱ የፍኖት ጋዜጣን አትሞ ያስራጫል። የፍኖት ጋዜጣን በብዛት ለማሳተምና በስፋት በየክልሎቹ ለማሰራጨት ከፍተኛ የገንዝብ አቅም ይጠይቃል። በአገር ቤት ከሚታገሉ ወገኖቻችን ጎን ይቁሙ ! በገንዘብዎት የአንድነት ፓርቲን ይደግፉ !
ፍኖት እትም 19ን በሙሉ ለማንበብ ከዚህ ይጫኑ !