“አኬልዳማ” ፊልም ወይስ የፍርድ ውሳኔ? የፍትህ ጋዜጣ ርእሰ አንቀጽ
በዚህ ሳምንት እንደተለመደው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ድርጅት አፍዝዝ አደንግዝ የሆነውን ዘጋቢ ፊልም አቀርቧል፡፡ ርዕሱንም አኬልዳማ ብለውታል፡፡ “አኬልዳማ” የሚለው ርዕስን የተጠቀሙት የርዕሰ ጉዳዩን አሳሳቢነት ለማስመር በመፈለግ ይመስላል፡፡ የዚህ ፊልም ጭብጥ ዋነኛ ማጠንጠኛ በዚህ ወቅት ለእስር የተዳረጉትን ጋዜጠኞችና የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ መሪና አባላት የሆኑ ግለሰቦች በሽብር ስራ ተሳታፊ መሆናቸውን ለማረጋገጥ አስረጅ መረጃ ይዘው ለመቅረብ ቢሆንም ፊልሙ ከብዙ አተያይ አንፃር በብዙ ጉድልት ከመሞላቱም በላይ ህገ-ወጥ ነው፡፡
ከዚህ በፊት ይቀርቡ እንደነበሩት ዘጋቢ ፊልሞች ይኼኛውም ፊልም ላይ የእውቀትና እውነት ጉድልቶች ይስተዋሉበታል፡፡ እንደዚህ አይነት ዘጋቢ ፊልም ለማቅርብ በተረጋገጠ መረጃና በተለየ አኳኋን ርዕሰ ጉዳዩን ማየት ተገቢ ነው፡፡ ገና ለገና ሰዎቹ ተከሰዋልና ህብረተሰቡ በጥርጣሬ እንዲያይ ለማድርግ የግለሰቦቹን ወንጀለኝነት ለማረጋገጥ፣ ግብረ-መልስ በሌለበት፣ ለብቻቸው በያዙት የቴሌቪዥን ጣቢያ ፊልም እየቆራረጡ፣ ንግግር እያሳመሩ ማቅረብ ተገቢ አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በፓርላማ ቀርበው ንግግር ባደረጉበት ወቅት ትልቅ አፅንኦት ሰጥተው የተናገሩት ዋነኛው ርዕሰ ጉዳያቸው የነበረው የነፃ ጋዜጣ ዘጋቢዎች ተከሳሾችን ከፍርድ ቤት አስቀድመው ነፃ ማለታቸውን በማውገዝና ለዚህም “ጋጠ-ወጥ… የጋዜጠኝነት ሀሁ ያልገባቸው” የሚሉ በዘለፋ የተሞሉ ንግግሮችን ማድርጋቸውን እናስታውሳለን፡፡
የርሳቸው መንግስት በበላይነት በሚቆጣጠረው የሚዲያ ተቋም ግን በማን አለብኝነት ያቀረቡትን ዘጋቢ ፊልም ከፍርድ ቤት በፊት ፍርድ ሰጥተው መጨረሳቸውን ስንመለከት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዘለፋ ለማን ይሆን? እንድንል እንገደዳለን፡፡
ኢቲቪ ፍርድ ቤት ነገሩን አጣርቶ ውሳኔ እስኪሰጥ ትዕግስቱን አሳጥቶታል፡፡ ሰዎቹ ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ፍርዱን ጨርሶ መዝገቡን ዘግቷል፡፡ ከዚህ በኋላ ፍርድ ቤቱ በምን አይነት ጫና ውስጥ ሊገባ እንደሚችል መገንዘብ እንችላለን፡፡ምክንያቱም ዳኞቹም እንደማንኛወም ዜጋ ኢቲቪን መመልከታቸው ስለማይቀር ነው፡፡ ፍትህ እንዲህ አይነቱን በፍርድ ቤት ስራ ላይ የሚደረግ ጣልቃ ገብነትን አጥብቃ ትቃወማለች፡፡ ኢቲቪም ሆነ ፕሮግራሙ እንዲቀርበ መመሪያ የሰጡ ባለስልጣናት ለፍርድ ይቀርቡ ዘንድ ፍትህ ትጠይቃለች፡፡ ነፃ ጋዜጠኞች ላይ የሚሰነዝሩት ቁጣዎች እና ማስፈራሪያዎች ለምንድን ነው የመንግስት ተጠሪዎችን የማይመለከተው? ፍርድ ቤቱ በራሱ አጣርቶ እንዲወስን ጊዜ የሚሰጠው መቼ ነው? ዜጐች ባልሰሩት ስራ የሀሰት ትረካዎችን በቃላት እያሳመሩ የሚከሱትና ፍርድ የሚሰጣቸው ማቆሚያው መቼ ነው? ፍትህን ለሚፈልጉ ዜጐች አሁንም ፍትህ ከደጃፋቸው ትሆን ዘንድ አቋማችንን እንገልፃለን፡፡
በመጨረሻም ከፊልሙ በኋላ አንዳንድ “ግለሰቦች” በቴሌቪዥን በሰጡት አስተያየት መሰረት “እነዚህን ግለሰቦች መፍታት በራሱ እኛን ለማስጨረስ ነው” ብለዋል ተብለው ህዝቡን በራሱ ዜጐች ላይ እንዲረባረብ አድርጎ ፍርድ ቤቱ ላይ ጫና ለማሳደር የተደረገውን ድርጊት ፍትህ አጥብቃ ትቃወማለች፡፡