በካናዳ ዋና ከተማ፡ ኦታዋ፡ የኔሰው ገብሬ በሻማ ማብራት ስነስርአት ታሰበ

አያሌ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችና የፖለቲካ ድርጅቶች አባላት ተገኝተው ነበር

Ethiopia Zare (ማክሰኞ ህዳር 26 ቀን 2004 ዓ.ም. December 6, 2011)፦ ከማል አቡበከር ይባላል። የአገሩ ጉዳይ የሚያንገበግበው ጎልማሳ ነው። በእለቱ የቤቱን እቃ ለማጓጓዝ የጭነት መኪና ለስድስት ሰዓት ያህል ቢከራይም፡ የየኔሰው ገብሬ መታሰቢያ እንደሚደረግ ስነግረው፡ መኪናውን ከመንገድ ጥግ አቁሞ ወደ ካናዳ ፓርላማ ለመጓዝ ሰከንድም አልፈጀበትም። “አረ ትኬት እንዳይሰጡህ” ቢባልም “እንኩዋን ትኬት መስጠት፡ ጎትተውም ይውሰዱት ከፈለጉ” ብሎ ወደ ሻማ ማብራቱ አቀና። እሁድ፡ ዲሴምበር 4፡ 2011 ዓ.ም፡ ከሰኣት በኋላ።