የአምስት ዓመቱን የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለመስበክ ዛሬ እና ነገ “ሕዝባዊ ንቅናቄ” ይካሄዳል
ሙሉ ገ.
ኢሕአዴግ በአዲስ አበባ ከተማ ዛሬ እና ነገ “ከፍተኛ የኾነ ሕዝባዊ ንቅናቄ እና ውይይት” ማከሄድ ጀመረ። በዚሁ “ሕዝባዊ ንቅናቄ” ላይ የአምስት ዓመቱን የዕድገት እና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለሕዝቡ ለመስበክ የኢሕአዴግ ካድሬዎች ክፍተኛ የኾነ ርብርብ ሲያደርጉ መሰንበታቸውንም የአዲስ ነገር የአዲስ አበባ ምንጮች ገልጸዋል።
ሰሞኑን የፓርቲው ካድሬዎች እና የመስተዳድሩ አባላት በሕዝባዊ ውይይቱ ላይ ንቁ ተሳተፊ ያሏቸውን አባወራዎች፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች እና ታዋቂ ሰዎች ሲያበረታቱ እና ሲያነቃቃ ነበር። እነዚሁ ሰዎች በስፍራው ላይ እንዲገኙላቸው በቅድሚያ ለቅዳሜው ስብሰባ የግብዣ ጥሪ ያደረጉ ሲኾን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ደግሞ በእሁዱ ስብሰባ ላይ እንዲገኙ አርብ ጥቅምት 25 ቀን 2010 ዓ.ም የጥሪ ወረቀቱ ሲበትኑ ውለዋል።
የአዲስ ነገር ምንጮች እንደገለጹት ዛሬ እና ነገ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን ለማወያየት እና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለመስበክ በየቀበሌዎቹ (አሁን የልማት ጣብያ ተብለዋል) ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፓርቲ አባል በማንቀሳቀስ ላይ እንደኾነም ታውቋል።
“በሕዝባዊ ንቅናቄው” የአዲስ አበባ ነዋሪን የልማት እንቅስቃሴው ተሳታፊ በማድረግ እና ከፓርቲው ጎን እንዲሰለፍ በማድረግ እያንዳንዱ የኢሕአዴግ ካድሬ ጥብቅ የኾነ መመርያ ተሰጥቶት ውጤታማ እንዲያደርግ ጥብቅ የዀነ ትዕዛዝ ተላልፎለታል። ፓርቲው “ሕዝባዊ” በሚል ስያሜ ባቀደው በዚሁ “ንቅናቄ” በአዲስ አበባ እና በአካባቢዋ ከሚገኙ ነዋሪዎች ስድስት ሚልዮን ብር ያህል የመሰብበስብ ዕቅድ አለው።