ህዝብ ንብረት ከሆኑት የቀበሌ መናፈሻዎች የሚገኘው ትርፍ የወያኔ ካድሬዎች ሽልማት ነው ተባለ
የዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ ባለስልጣናት እና ካድሬዎች የኢትዮጵያን ህዝብ ከሚበዘብዙባቸው መንገዶች ውስጥ ብዙ የማይወራላቸው የቀበሌ መናፈሻዎች መሆናቸውን የሚጠቁም መረጃ ሰሞኑን ለዝግጅት ክፍላችን ደርሷል።
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሁሉም ቀበሌዎች ሊባል በሚችል ሁኔታ በወሳኝ አካባቢዎች የተቋቋሙ የህዝብ መናፈሻ ማእከላት እንዳሉ ይታወቃል። እነዚህ መናፈሻዎች ለአካባቢው ሰዎች የስራ እድል ከመፍጠራቸው በተጨማሪ፤ በዝቅተኛ ዋጋ የባር፣ የምግብ፣ የካፌ እና የመዝናኛው አገልግሎቶች ለያሉበት ማህበረሰብ ይሰጣሉ።
ከፍተኛ ገቢ እንዳላቸው የሚነገርላቸው እነዚህ የህዝብ ድርጅቶች ግን ግልጽ የሆነ የገንዘብ አያያዝ መዋቅር እንደሌላቸው ለማወቅ ተችሏል። የአዲስ አበባውን የግንቦት 7 ድምጽ ዘጋቢ ያናገሩ የውስጥ አዋቂ ምንጮች እንደሚሉት፣ ከነዚህ ተቋማት የሚገኘው ገቢ በቀጥታ የዘረኛው አገዛዝ ካድሬዎች ወደሆኑ የቀበሌ ባለስልጣናት ኪስ እየገባ ነው።
መረጃውን በድብቅ ያቀበሉት ዜጎች ጉዳዩን የሚያጋልጡበት መድረክ እንደሌላቸው እና አለ በሚባለው መንገድ ለመሄድ እንደሚፈሩ ተናግረዋል። ይህ አሰራር የወያኔ አገዛዝ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያሉ ካድሬዎቹን ከሚሸልምባቸው መንገዶች አንዱ ነው ብለው እንደሚገምቱ የገለጹት ምንጮች፤ የካድሬዎቹን ስርቆት ብናጋልጥ ተቀጪዎቹ ካድሬዎቹ ሳይሆኑ እኛው ራሳችን እንሆናለን በሚል አንሰጋለን ብለዋል።