በአዲስ አበባ ከተማ በምጥ ላይ ያሉ ነፍሰ ጡሮች የሆስፒታል አልጋ ለማግኘት እንደሚንከራተቱ ታወቀ
የመንግስት ሆስፒታሎች በጉቦ እና በዝምድና ካልሆነ በስተቀር አገልግሎት ወደማይሰጡበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል ሲል የግንቦት 7 ድምጽ ዘጋቢ ከአዲስ አበባ በላከው መረጃ አመልክቷል።
ከጊዜ ወደጊዜ ብቃታቸው እየጎደለ የሄደው የመንግስት ተቋማት፣ እና በተለይም ሆስፒታሎች፣ የአገልግሎት ደረጃቸው እና ሽፋናቸው ዝቅ እያለ መሄዱን በተደጋጋሚ የዜጎችን ስሞታ በመጥቀስ መዘገባችን ይታወሳል።
ዘጋቢያችንን ያናገሩት አንድ ተጠቃሚ እንደሚሉት፥ ምጥ ላይ ያሉ ባለቤታቸውን ይዘው ከሆስፒታል ሆስፒታል አልጋ ፍለጋ ሲንከራተቱ ለመዋል ተገደዋል። በስተመጨረሻ “አልጋ የለም” ካሏቸው ሆስፒታሎች ውስጥ ባንዱ የሚሰራ ዘመዳቸውን አግኝተው በመማጸን ወዲያውኑ ቦታ እንደተሰጣቸው እና ባለቤታቸውም በሰላም ለመገላገል እንደታደሉ ገልጸዋል።
በየሆስፒታሉ አልጋ ፍለጋ ሲንከራተቱ በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ብዙ ሰዎችን እንዳዩ የሚናገሩት ግለሰብ፤ ወደ ግል ሆስፒታል ሄደው መታከም የማይችሉ ድሆች እና እንደሳቸው ዘመድ የሌላቸው ሰዎች እጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን አሳስቦኛል ብለዋል።
ዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ በአገሪቱ ውስጥ ከሚያካሄዳቸው የመብት ረገጣዎች የተነሳ በየአመቱ በአስር ሺሆች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን እየጣሉ የሚሰደዱ ሲሆን፤ ከዚህም ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የአገሪቱ የተማረ የሰው ሃይል ነው። በተጨማሪም፥ አገዛዙ ቁጥራቸው የማይታወቅ መንግስት ሰራተኞችን በፖለቲካ ምክንያት ከስራ እንደሚያባርር እና ብቃት በሌላቸው ካድሬዎች እንደሚተካ ይታወቃል።