የታላቁ ሩጫ ቲኬት ገበያ ላይ መሆኑ ሳይታወቅ ተሸጦ ማለቁ አነጋጋሪ ሆኖ ሰነበተ

በ1994 አመተ ምህረት በአትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ ተቋቁሞ እና በየአመቱ ሲካሄድ የቆየው ታላቁ ሩጫ በዘረኛውና አምባገነናዊው የወያኔ አገዛዝ ቁጥጥር ስር ሳይወድቅ እንዳልቀረ የሚያመለክት መረጃ ለግንቦት 7 ድምጽ የዝግጅት ክፍል ደርሷል።

በህዝቡ ዘንድ “የብሶት መግለጫ” የሚል ቅጽል ስም የተሰጠው ዝግጅት፤ በተለይ ከ97ቱ ምርጫ በኋላ ሰላማዊ ሰልፍ እና ስብሰባ የማድረግ ሰብአዊ መብታቸውን በተከለከሉ ወጣቶች የተቃውሞ ድምጽ አሸብርቆ እንደሚያልፍ ይታወቃል።

የግንቦት 7 ድምጽ ዘጋቢ ከአዲስ አበባ አጠናቅሮ የላከው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የዝግጅቱ አስተባባሪዎች የዘንድሮው ሩጫ መግቢያ ቲኬት ገና ሳይተዋወቅ ተሸጦ አልቋል ብለው ማወጃቸው በብዙዎች ዘንድ አነጋጋሪ ሆኖ ሰንብቷል። ከዚህ ቀደም ቲኬቱ መሸጥ ሲጀመር በመገናኛ ብዙሃን እና በትምህርት ቤቶች የማስታወቂያ ዘመቻ ይካሄድ እንደነበር ያስታወሰው ዘጋቢያችን፤ በዚህ አመት ምንም ሳይሰማ ተሸጦ አልቋል መባሉን ጠቅሷል።

ሩጫው ከተጀመረበት አመት አንስቶ አምልጦን አያውቅም ያሉና ዘጋቢያችንን ያናገሩ ሰዎች፤ ቲኬት ሊያገኙ እንዳልቻሉ እና ያገኘ ሰውም እንደማያውቁ ተናግረዋል። በርካታ አስተያየት ሰጪዎች፥ የወያኔ አገዛዝ በሩጫው ላይ የሚገለጹትን ተቃውሞዎች ከወዲሁ ለማፈን ሲል ካድሬዎቹ ቲኬቶቹን ለደጋፊዎች እና ለፓርቲ አባላት እንዲያከፋፍሉ በጅምላ ሳይጠቀልለው አልቀረም ሲሉ ግምታቸውን ገልጸዋል።

አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ በቅርቡ በተካሄደው የገዢው ፓርቲ ጉባኤ ላይ ተገኝቶ ለወያኔ አገዛዝ ድጋፍ የሚሰጥ ንግግር ማድረጉ እና አንድ ሬከርድ ሲሰብር ለብሶት የነበረውን ከነቴራ ለዘረኛው አምባገነን መለስ ዜናዊ በስጦታ መልክ ማቅረቡ ይታወሳል። በርካታ አስተያየት ሰጪዎች፥ ታዋቂው አትሌት ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የንግድ እንቅስቃሴ የሚያደርግ በመሆኑ ድጋፍ እንዲሰጥ ጫና ሳይደረግበት አይቀርም ይላሉ።

በህዳር 12 የሚካሄደው ሩጫ ቲኬቶች ከውጭ አገር ለሚመጡ ሯጮች እስካሁን በሽያጭ ላይ የሚገኙ መሆናቸውን ከድርጅቱ ድረ-ገጽ ለመረዳት የቻልን ቢሆንም፤ የአገር ውስጥ ተሳታፊዎችን በሚመለከት የዝግጅት ክፍላችን ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም።