ሰማዕታት ለጣሉብን ኃላፊነት ብቁዎች ነንን? እራሳችንን እንጠይቅ!

ጥቅምት 1998 በዘረኝነት የተለከፉ ሰዎች ጭካኔን፣ በየቤታችን በራፎች፤ በገዛ ዓይኖቻችን ያየንበት ወር ነው። ዘረኛ የሆነ ሰው ከራሱ ዘውግ ውጭ ያሉ ሰዎችን እንደ ጥቃቅን ነፍሳት በመቁጠር እየተዝናና እንደሚጨፈልቃቸው ተመልክተናል። ቀድሞ በአውሮፓ በናዚ ጀርመን፣ በቅርቡ በሰርቪያና በኮሶቮ፤ እንዲሁም በአፍሪካ ሩዋንዳ የታየው ዓይነት የዘር ፍጅት እኛም ላይ ደርሶ አየነው።

ለዓመታት በአስመሳይ ፕሮፖጋንዳ ተሸፋፍኖ የቆየው የትግራዩ ገዢ ጉጅሌ እውነተኛ ባህርይ የዛሬ አምስት ዓመት በጥቅምት ወር አደባባይ ወጣ። ይህ በጥላቻ የታወረ ዘረኛ በጉልበት የያዝኩትን ሥልጣን በምርጫ ካርድ ሊቀሙኝ ቃጥተዋል ባላቸው ሁሉ ላይ፤ በተለይም ደግሞ ከራሱ ዘውግ ውጭ ያሉትን በሙሉ ሊፈጅ ተነሳ። የቻለውን ያህል ገደለ፤ በሺህዎች በሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎች ላይ የአካል ጉዳት አደረሰ፤ ሚሊዮኖችን አዋረደ።

በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣ በባህርዳር፣ በጎንደር፣ በአዋሳ፣ በሃረር፣ በድሬዳዋ እና ሌሎች ከተሞች እንዲሁም ገጠሮች በሚገኙ ሰላማዊ እናቶችና አባቶች፤ ወጣቶችና ህፃናት ላይ ዘመተ። አግዓዚ የተባለው የክፋት ሠራዊት መርሆዎች ጥላቻ፣ ትዕቢት እና ጭካኔ ነበሩ። በዚህም ምክንያት ደብተርና እርሳሶቻቸውን እንደያዙ ከትምህርት ቤት የሚመለሱ እምቦቃቅላ ህፃናትን ሳይቀር በጥይት ግንባርና ደረታቸውን እየመታ ጣለ።

በጥቅምት ወር 1998 አዲስ አበባ ለመስማት የሚዘገንኑ ጭካኔዎችን አስተናገደች። በጥይት ግንባሩን ተመትቶ ወደወደቀው ታናሽ ወንድሙ የሮጠው ህፃን ደረቱን ተመትቶ የታናሹን ጽዋ ተካፈለ። ባሏ በአጋዚዎች ሲወሰድ ያለቀሰች ሚስት በልጆቿ ፊት በጥይት እሩምታ ተገደለች። እናቶችና እህቶች በማልቀሳቸው ብቻ ጥይት ዘነበባቸው። ታንክና ብረት ለበስ መኪናዎች ድንጋይ በሚወረውሩ ወጣቶች ላይ ተሰማሩ። ሆስፒታሎች በአስከሬኖችና ቁስለኞች ተሞሉ። በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ወደ በረሃ ተጋዙ። የትግራዩ ገዥ ጉጅሌ ለዘመናት የቋጠረውን ጥላቻ በጥቅምት ወር በይፋ አሳየ።

የዚህ ሁሉ ጭካኔ ምንጩ ምንድነው? እውን ሰው በሌላ አምሳያው ላይ ይኸን ያህል መጨከን ይችላል?

በጭራሽ!!! ሰው ብቻ ሳይሆን በጣት ከሚቆጠሩት በስተቀር እንስሳም ቢሆን አምሳያውን አይበላም። ጭካኔን ለመፍጠር “ከራሴ ወገን ውጭ ያለው ሰው በሙሉ ሰው አይደለም” ብሎ ማመን ያስፈልጋል። ዘረኝነት እንዲህ ዓይነቱን የታመመ ጭንቅላት ይፈጥራል። ለዘረኛ ሰው “ሌላው ሰው” ሰው አይደለም። ጥራት ያለውን ሰው ለመፍጠር “ሌሎቹ ሰዎች” መወገድ አለባቸው። እንዲያውም “ምርጦች” ብቻ እንዲፋፉ ሌሎችን ማስወገድ ተፈጥሮን መርዳት አድርጎ የሚወስድ ጭንቅላት ይፈጥራል – ዘረኝነት። ለዘረኛ ጭንቅላት ሌሎች ተባዮችና ተውሳኮች ናቸውና እነሱን ማስወገድ ያሸልማል።

በጥቅምት 1998 ያየነው ይህንን ነው። የትግራዩ ገዢ ጉጅሌ ያደረገው ይህንን ነው። በጉጅሌው እሳቤ መሠረት ወጣት ሽብሬ፣ ህፃን ነቢዩ፣ እናቶችና አባቶች ሰዎች አይደሉም። እንዲያውም ሰው መስለው መፈጠራቸው ስህተት ነው። በጉጅሌው እሳቤ መኖራቸው ጉዳት እንጂ ጥቅም የለውም። ስለሆነም ያለምክንያት ተገደሉ። ገዳዮቻቸው በመግደላቸው ተሾሙ፤ ተሸለሙ።

የጥቅምት ሰማዕታትን የምናስባቸው በጥልቅ ሃዘን ብቻ ሳይሆን በቁጭትና እልህም ጭምር ነው። ወገኖቻችን እንደሰው ባለመቆጠራቸው ተገደሉ። አሁንም እንደሰው የማይቆጠሩ በመሆኑ ሙት ዓመታቸውን መዘከር ወንጀል ነው። መቸ ነው ይህ ውርደት የሚያበቃው?

ሰማዕታቱ የህይወት ዋጋ ከፍለው ዘረኝነትን የማስወገድ ሸክም እኛ ላይ ጥለዋል። ይህንን ኃላፊነት ለመሸከም ብቁዎች ነንን? እያንዳንዳችን የገዛ ራሳችንን እንጠይቅ።

ዘላለማዊ ክብር ለሰማዕቶቻችን !!!

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!!