ባለፈው እሁድ የተካሄደው የዘንድሮው ታላቁ ሩጫ እንደወትሮው የብሶት መግለጫ ሆኖ ማለፉ ተዘገበ

ባለፈው እሁድ ለ11ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በተካሄደው ታላቁ ሩጫ የተሳተፉ ዜጎች፤ ወያኔ መራሹ የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ በአገራችን ውስጥ እያሰፈነ ያለውን ኢፍትሃዊነትና አፈና የሚያወግዝ መፈክሮችን ሲያሰሙ እንደዋሉ የግንቦት 7 ዜጋቢ ከአዲስ አበባ በላከልን ዜና አስታወቀ።

በዚይ የህዝብ ብሶት ሲስተጋባበት በዋለው የሩጫ ውድድር የተሳተፉት፤ ከምዝገባው ጀምሮ በተቻለ መጠን ለወያኔ ፖለቲካ ወገንተኝነት ያላቸው እንዲሆኑ በአዘጋጆች በኩል ጀምሮ አስፈላጊው ጥረት ተደርጎ እንደነበር የጠቀስው ዘጋቢያችን፤ በአገራችን የሰፈነው የፖለቲካ፤ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግሮች ያልዳሰሱት የህብረተሰብ ክፍል ባለመኖሩ በውድድሩ ላይ በየአመቱ ሲስተጋቡ የቆዩትን እንዲህ አይነቱን ብሶቶች ዳግም እንዳይሰማ ለማድረግ ተደርጎ የነበረው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቶአል ብሎአል።

ታላቁ ሩጫ በድህረምርጫ 97 የታሰሩት የቅንጅት መሪዎች፤ ጋዜጠኞችና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ጉዳይ በህብረተሰቡ ውስጥ የቀሰቀሰውን ተቃውሞና ጸረ ወያኔ ስሜት መግለጫ መሆኑ ተደጋግሞ በመታየቱ፤ ብዙ አፍቃሪ የፈጠረውን ይህንን ታላቅ ሩጫ ከማስቀረት መነሻው ከመስቀል አደባባይ ሆኖ አገዛዙ ቁንጮ በከተመበት ቤተመንግሥት በኩል ወደ አራት ኪሎ ያልፍ የነበረውን መስመር በመዝጋት ካለፈው አመት ጀምሮ ከመስቀል አደባባይ በሜክስኮ አድርጎ ወደ ጎተራ አቅጣጫ ደርሶ መልስ እንዲሆን ተወስኖአል። ይህም ሆኖ ግን ህዝብ የተሰማውን ብሶት ለማፈን እንዳልተቻለ ባለፈው እሁድ የተካሄደው ሩጫ አረጋግጦአል እንደዘጋቢያችን ሪፖርት።

ቁጥራቸው ከሰላሳ ስድስት ሺህ በላይ ህዝብ ተሳትፎበታል የተባለው የዘንድሮው ታላቁ ሩጫ የወያኔ ፕሮፖጋንዳ መሳሪያ ሆኖ በማገልገል ላይ በሚገኙ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን በቀጥታ ይተላለፍ እንደነበረ የዘገበው ዘጋቢያችን፤ ሩጫው ከተጀመረ ጥቂት ደቂቃዎች ቦኋላ የተቃውሞ መፈክሮች መስተጋባት እንደጀመሩና እቤቱ ሆኖ ፕሮግራሙን ይከታተል የነበረው ህዝብ ሯጮች ጣቶቻቸውን እየቀሰሩ “ሌባ ሌባ ኢህአደግ ሌባ” እያሉ ያደርጉትን የነበረውን ጩሄት ይመለከት እንደነበር ገልጾአል። ሆኖም አገዛዙን የሚያወግዙ መፈክሮች እየተበራከቱ በመምጣታቸው በኢትዮጵያዊያን ግብር ከፋይ ሥም እየተዳደረ መልሶ ህዝብ ለማፈኛ አገልግሎት ላይ እየዋለ ባለው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሚስልና ድምጽ ውህደቱን በማቋረጥ ድምጽ አልባ የሆነ ምስል በስቱዲዮ ሰራተኞች የድምጽ ቅንብር ለማስተላለፍ እንደተገደደ ለማረጋገጥ ተችሎአል።

በዜማ እየታጀበ በዕለቱ ከተስተጋቡ መፈክሮች ጥቂቶቹ ኢህ አደግ ሌባ!!!!!፤ መንግሥት ሌባ!!!!!፤ ለዛሬ አመት አሃሃ ለዛሬ አመት በአዲስ መንግሥት!!!!! ምን አለ እስክንድር ምን አለ? ሀገሬን ተቼ ሀገሬን ትቼ አልሄድም አለ፤ ምን አለ ተመስጌን ምን አለ? ሀገሬን ትቼ አሃሃ አገሬን ትቼ አልሰደድም አለ፤ መለስ በቃ!!!!! ወያኔ በቃ!!!!! ብርሌ ከነቃ አይሆንም እቃ!!!፤ ፒስ ነው እያለ፤ መሬቱን ሸጠው፣ አይቀርም አንድ ቀን አይቀርም አንድ ቀን መለስ እንደጋዳፊ ሊሆን!!! ፍትህ ለኢትዮጵያ!!! ፍትህ ለኢትዮጵያ!!! ፈዴራል ፖሊሶች ካሉበት ሲደርሱ ደግሞ “ፌደራል፤ ውሻ ውሻ፤ ፌደራል ውሻ ውሻ፤ ይጩህ እንደ ውሻ፤ የሚል ነበር ተብሎአል። በየአመቱ የሚደረገውን የሩጫ ውድድር ዋና አዘጋጅ የነበረው ሃይሌ ገብረስላሰንም ለማሞካሸት እድሜ ለሃይሌ፤ ተነፈስን የሚሉ ድምጾችም ጎላብለው እንደመፈክሮቹ ሲደመጡ እንደነበር ዘጋቢያችን ገልጾአል።

የህዝብ ብሶት ማሰሚያ ሆኖ በዋለው ከትናትና በስቲያ እሁድ ሩጫ ላይ ለተስተጋቡት መፈክሮች ቀስቃሾች ናቸው የተባሉ በርካታ ሰዎች ወዲያው በፌዴራል ፖልሲ ተይዘው ወደአልታወቀ ስፍራ እንደተወሰዱ ተያይዞ የደሬሰን ዜና ያስረዳል።