በክፉዎች ምክር ያልሄደ ምስጉን ነው!!
በአገራችን ላይ ክፉ ምክር ሲመከር እነሆ ሁለት አስርተ ዓመታት ተቆጠሩ። አንድ ህዝብ የሌላው ህዝብ ጠላት እንዲሆን ተሰብኳል። በህዝብ መካከል ቋሚ ጥላቻን የሚመሰክሩ ሃውልቶችም ቆመዋል። አገሪቷ የነበራት እሴቶች ሆን ተብለው በጥናት ተዘምቶባቸዋል። የአገሪቷ ህግ በአንድ ክፉ ጣኦት ስሜት ተተክቶ ፍትህ በመጥፋቱ ዜጎች ለእስራት፤ ለስደትና ለውርደት ተዳርገዋል። ውርደቱ ወደ ክፉ ሮሮ በመሸጋገሩ ዜጎች እያለቀሱ ነው። መጽሃፈ ምሳሌ “ኃጥአን በሰለጠኑ ግዜ ህዝብ ያልቀሳል” ያለው በአገራችን እውነተኛ ታሪክ ሆኖ እየታየ ነው። የመምህር የኔሰው ገብሬ በራሱ ላይ ላምባ አርከፍክፎ መቃጠልም የዚህ ውጤት ነው።
መለስ ዜናዊና ግብረአበሮቹ ስቃዩ በዝቶበት ራሱን መሰዋእት ያደረገውን ምስጉን መምህር የአእምሮ ህመምተኛ ነው ብለዋል። የዋካ ከተማ ሃኪሞችንም በዚህ ውሸታቸው እንዲተባበሯቸውና ከክፉ ምክራቸው ጋር እንዲቆሙላቸው ለማድረግ እየሞከሩ ነው። እነመለስ ዜናዊ የገዛ ውሸታቸውን አምነው ዜጎችም እንዲዋሹላቸው ለማድረግ ከላይ እግዜርን ከታች ሰውን የሚያፍሩ አይደሉም። ባለንበት ወቅት ከእነዚህ ዘረኞችና የህዝብ ጠላቶች ጋር አለመቆም በምክራቸውም አለመሄድ ትልቅ መስዋእትነት የሚጠይቅ ተግባር ነው። የዋካ ከተማ ሃኪሞች መምህር የኔሰው ገብሬ የሞተለትን ዓላማ ለመረዳት እዝነ ልቦናቸው መለስ ዜናዊ በሚወረውረው ፍርፋሪ የተያዘ አይደለም። ያዩትን ለመመስከር የሞራልም ሆነ ህጋዊ ግዴታ አለባቸውና ከዘረኞችና ከህዝብ ጠላቶች የሚሰነዘርባቸውን ዛቻና ማስፈራሪያ ችላ በማለት እውነቱን መናገር ይጠበቅባቸዋል። እውነቱም መምህር የኔሰው ገብሬ የአእምሮ ህመምተኛ ሳይሆን ሙሉ ጤነኛ የሆነና የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ መሆኑ ነው።
የኔሰው ገብሬ የእኛ ሙሃመድ ቡዛዚ ነው።በመለስ ዜናዊ የተዘረጋው ዘረኛ አገዛዝ የመረረው፤መከራው በዝቶ በሮሮ ውስጥ መኖር የሰለቸው ነጻነት ፈላጊ ክቡር ዜጋ ነው። ይህን ለነጻነት ራሱን መስዋእት አድርጎ ያቀረበውን ወጣት መምህር የአእምሮ ህመምተኛ ነበር ብለው የጻፉ እጆችን በጥንቃቄ እየተመለከትን ነው። ዜናውን ያወጁትን ይዘናቸዋል። ዋካ ድረስ ገስግሰው ሂደው የነጻነት አርበኛውን ታሪክ የሚያጠፋ ጉድፍ ዘገባ ያዘጋጁትንና ዜናውን ያቀናበሩት እንማን እንደሆኑ አውቀናቸዋል። እንዲህ ያለ ነውር ተግባርን ለእንጀራየ ብየ ሰራሁ ማለት ከምንም የሚያድን ተግባር እንዳልሆነ አበክረን ማሳሰብ እንወዳለን። የመለስ ዘረኛና ዘራፊ ስርዓት ንፋስ ጠርጎ እንደሚወስደው ትቢያ የሚሆንበት ግዜ ሩቅ አይደለም። ያን ግዜ እውነት ትነገራለች። እውነት በተነገርች ግዜ በአፋቸው እውነት ተፈልጎ የሚገኝባቸው ዜጎች ይመሰገናሉ። እውነት ተፈልጋ ስትታጣ ለእንጀራየ ብየ ስዋሽ ኖርኩ የሚሉትን ግን እግዜር እላይ ከሰማይ ሰውም ከዚህ ከምድር ይታዘባቸዋል። ያን ግዜ የሞራልም ሆነ የህግ ተጠያቂነትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ነውር ተግባራት ሁሉ ይገለጣሉ።
በአገሪቷ ላይ ክፉ ጣኦት ነግሶ እንዲህ ወገንን በሚያሰቃይበት ወቅት የስቃዩን ምንጭ ጣኦት አለመዋጋት ነውር ነው። ክፉ አድራጊዎችን አለመቃወም ነውር ነው። ሃሰት የሚናገሩትን ዝም ማለት ነውር ነው። ዜጎችን የሚያሳድዱትን ተው አለማለት ነውር ነው። ጉሮሮአቸው እንደተከፈተ መቃብር ዜጎችን ሲውጥ እያዩ ዝም ማለትም ነውር ነው።
የመለስ ዜናዊ ጉሮሮ እንደተከፈተ መቃብር ዜጎችን እየዋጠ የአገራችን ስቃይና መከራዋን አብዝቷል። ይህን ስቃይና መከራ የሆነ ግለሰብ ከዚያች አገር ለአንዴና ለመጨረሻ ግዜ ተነቅሎ ስም አጠራሩ እንዳይታወቅ ለማድረግ ግንቦት ሰባት የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። ዜጎችም በያሉበት ሁነው በሚችሉት ሁሉ ይህን የእኩይ ተግባራት ምንጭ የሆነውን ግለሰብና ቡድኑን መታገል ወቅቱ የሚጠይቀው ትክክለኛ ተግባር ነው።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!!