ገብረመድህን (አባ ጳውሎስ) ‹‹ሐውልት ፍለጋ›› ጀመረ
አቡነ ጳውሎስ ትናንት ጥቅምት 21 ቀን 2003 ዓ.ም በዋለው እሑድ ሰንበት በሰሜን ምዕራብ ሸዋ – ሰላሌ ሀገረ ስብከት የምትገኘዋን የደብር ቅዱስ ደብረ ጽጌ ማርያም ገዳምን ጎበኙ፡፡ የሥሪቷ ጥንታዊነት እስከ መካከለኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ወደኋላ በሚቆጠርላት የደብር ቅዱስ ደብረ ጽጌ ማርያም ገዳም አሁን ቆሞ የሚታየው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን የተሠራው በኢትዮጵያዊው ቀዳማዊ ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ዘመን በ1952 ዓ.ም ነው፡፡ በገዳሟ ቤተ መቅደስ ውስጥ ያለውን በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ መልክእ የተቀረጸውን ምስል የጎበኙት ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ምስሉ ፎቶ ግራፍ እንዲነሣ ማዘዛቸውን፣ በቃላቸውም ትእዛዝ መሠረት ምስሉ ፎቶ ግራፍ መነሣቱ ተዘግቧል፡፡ ነዋሪነታቸውን በጀርመን ሀገር ያደረጉ ወገኖች ‹‹ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ ስለነበራቸው ፍቅር›› ከዜና ዕረፍታቸው በኋላ እንዳሠሩት የሚነገርለትን ይህንኑ የቁም ምስል የጎበኙት ፓትርያርኩ ከነገ በስቲያ የሐውልት ማፈላለግ ዑደታቸውን በመቀጠል በግብጽ በርሓ ከሚገኙት ገዳማት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሐውልት ይገኛል የሚባልበትን ገዳም እንደሚጎበኙ ተነግሯል፡፡
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 20 ቀን 2003 ዓ.ም በተጠናቀቀው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የሐውልቱን መሠራት ጨምሮ የሲኖዶሱን ማእከላዊ አሠራር ያልጠበቁ አካሄዶች በተመለከተ በተዘረጉት አጀንዳዎች ላይ በመንፈስ ልዕልና እና በሐሳብ የበላይነት አቋማቸውን ፊት ለፊት እያስረገጡ ከመወያየት ይልቅ በዝምታ/ቸልታ ሲያዘናጉ ቆይተዋል፤ በስብሰባው መዳፊያ ላይ ግን እንዲህ ባለው ወሳኝ አካል የሚካሄዱ ውይይቶች እና የሚተላለፉ ውሳኔዎች የሕዝቡን ቀልብ የሚይዙ በመሆናቸው በስተመጨረሻ የሚሰጡ ጋዜጣዊ መግለጫዎች እና የሚዘጋጁ ጋዜጣዊ ጉባኤዎች ከፍተኛ የሕዝብ ግንኙነት ፋይዳ ይኖራቸዋል፡፡ ይህን ለመረዳት ብፁዓን አባቶች የልምድ ውስንነት እንደነበረባቸው ታይቷል፡፡ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ግን የሳምንት አርምሟቸው የአንደበት እንጂ እንደ በቁት አባቶቻችን የጽማዌ እንዳልነበር መድረኩ ያለውን ዋጋ በስተመጨረሻ በብልጣብልጥነት በመጠቀም አሳይተውናል – ብልጥ ያለአንድ ቀን አይበልጥም እንጂ!! ከብፁዓን አባቶች የነበረባቸውን ተግዳሮት ከአንድ ዓመት በፊት እንደነበረው ‹‹በተውሶ ጡንቻ›› ሳይሆን በብልጣብልጥነት ቀጭን ጎዳና የተወጡት የመሰላቸው አቡነ ጳውሎስ፣ አሁን ደግሞ በዳሰሳዊ ዕውቀት ላይ የተመሠረቱ ሙግቶችን (Empirical evidences) በማቅረብ በራሳቸው አስተሳሰብ የክብራቸው ትእምርት የሆነው ሐውልታቸው እንዳይፈርስ በመትጋት ላይ ናቸው፡፡
በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የመጨረሻው ከፍተኛ ሥልጣን ባለቤት የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ ስለሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎች አፈጻጸም ሕገ ቤተ ክርስቲያኑ የሚለውን የተመለከትን እንደሆነ ግን፣ በአንቀጽ 11 ንኡስ አንቀጽ አንድ ቋሚ ሲኖዶሱ፣ በአንቀጽ 15 ፓትርያርኩ፣ በአንቀጽ 20 ኤጲስ ቆጶሳቱ፣ በአንቀጽ 25 የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊው እና በአንቀጽ 30 የቤተ ክህነቱ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ የመፈጸም እና የማስፈጸም ግዴታ እንደተጣለባቸው ይደነግጋል፡፡ በመሆኑም ስለ ሐውልቱ መፍረስ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም አንገብጋቢ አጀንዳዎች ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ ያስተላለፋቸው ውሳኔዎች ተፈጻሚነት በተጠቀሱት አካላት የቅርብ ክትትል ሊደረግባቸው ይገባል፡፡ በአፈጻጸሙ ሂደት አስቸኳይ እና ድንገተኛ እክሎች ቢያጋጥሙ በየዓመቱ ጥቅምት 12 እና ትንሣኤ በዋለ በሃያ አምስተኛው ቀን/በርክበ ካህናት/ ከሚደረገው ጉባኤ ውጭ ቅዱስ ፓትርያርኩ ወይም የቋሚ ሲኖዶስ አባላት በሚያደርጉት ጥሪ አልያም ከጠቅላላው አባላት ከሦስት ሁለቱ እጅ የሚሆኑ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ምልአተ ጉባኤ እንዲደረግ በጠየቁ ጊዜ ጥሪ ሊደረግ እና ስብሰባው ሊካሄድ ይችላል (አንቀጽ 10 ንኡስ አንቀጽ 1 – 2)፡፡