ወያኔ የመረጃ ፍሰትን ለመቆጣጠር በኢንተርነትና ስልክ አገልግሎት ላይ የጣለው ቁጥጥር ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ የሚገኙ የውጪ አገር ኤምባሲዎችን ጭምር እንዳስመረረ ተዘገበ
በአገራችን የተዘረጋው የስልክና የኢንተርኔት አቅርቦት ወያኔ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ለመገደብና ዜጎች ስለአገራቸውና ስለሚያስተዳድራቸው መንግሥት በቂ መረጃ እንዳያገኙ ለመከላከል እንዲያስችል ተደርጎ የተዋቀረ በመሆኑ ፤ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑ ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ የሆነ አለም አቀፍ ድርጅቶችና ዲፕሎማቲክ ሚሽኖች ጭምር እያስመረረ መምጣቱን ባለፈው ሳምንት ይፋ የሆነ ዜና አረጋገጠ።
በወያኔ አገዛዝ ቁጥጥር ሥር የሆነው የኢትዮ ቴሌኮም ኮርፖሬሽን ከደንበኞቹ ጋር ባለፈው ሳምንት በሂልቴን ሆቴል ባካሄደው የሃሳብ ልውውጥ ላይ የተሳተፉ የበርካታ አገራት ኢምባሲ ተወካዮች እንደገለጹት፤ የተለያዩ አለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ድርጅቶች ጽቤት በሚገኝበት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እየታየ ያለው የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት አቅርቦት እጂግ የሚያስመርር ኋላቀርና ደካማ መሆኑን ገልጸው ይህ አሰራር ባፋጣን ሊሻሻል ግድ ይላል ብለዋል።
ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ ከሆኑ ኤምባሲዎችና አለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካይ በተጨማሪ በውይይቱ ላይ ከተሳተፉ አገራዊ መሥሪያቤቶች መካከልም አንዳንዶቹ በአቅርቦቱ ኋላቀርነት መማረራቸውን እንደገለጹ የተዘገበ ሲሆን የአዲስ አበባ መስተዳድር ጽህፈት ቤትም ከቅሬታ አቅራቢዎቹ አንዱ እንደነበር ተዘግቦአል።
የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፤የአፍሪካ መዲና የሆነችው ኢትዮጵያ በስልክና በኢንተርኔት አገልግሎት ፤ከመንግስት አልባዋ ሶማሊያ ሳይቀር የማትሻልና ከአፍሪካ አህጉር መጨረሻ ላይ የምትገኝ ናት።
የኢንቴርኔት አገልግሎት በቱኒዚያና ግብጽ ሚሊዮኖችን ለለውጥ በማነሳሳት አገልግሎት ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ ወያኔ በወሰደው ጠበቅ ያለ የአፈና እርምጃ ወትሮውኑ የአገልግሎት አቅሙ ደካማ የነበረው የአገራችን የኢንተርኔት አቅርቦት ከነበረው አቅም በታች እንዲወርድ በመደረጉ በርካታ ድርጅቶችና ተቋሞች አገልግሎቱን ማማርር አዘወትረዋል።
ቀደም ሲል የ ኢትዮጵያ ቴሌኮሚኒከሽን ባለሥልጣን በመባል ይታወቅ የነበረው መንግሥታዊ ተቋም ውስጥ የሚሰሩ የስራ ሃላፊዎችና በርካታ ሺ ሠራተኞች ተባረው በቻይና በሰለጠኑ የህወሃት አባላትና ከመከላኪያ ሰራዊት በተገለሉ ሰዎች እንዲያዝ መደረጉ ሲዘገብ ቆይቶአል።
ባለፈው ሳምንት የወያኔን ኢፍትሃዊነት በመቃወም ራሱን በ እሳት አቃጥሎ የሰዋ የመምህር የኔሰው ገብሬ ዜና እንደተሰማ፤ ወደ አካባቢው የሚደረጉ የስልክ ጥሪዎች በአስቸኳይ ከአገልግሎት ውጪ እንዲሆኑ መደረጋቸው አይዘነጋም። የኢትዮ ቴሌኮም ወያኔ የዘጎችን ስልክ መስመር ለመጥለፍ የሚያደርገውን ሥራ እያገዘ መሆኑ በቅርቡ በቅርቡ በእነ ኤልያስ ክፍሌ መዝገብ ተከሰው ፍርድ ቤት በቀረቡት በእነ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬና መምህርት ርእዮት አለሙ ላይ የቀረበው የስልክ ንግግር መረጃ አጋልጦአል።