የኢትዮጵያዊያን ጋዜጠኞች ሃገራቸውን ጥሎ መሰደድ ቀጥሎአል፣ የሲ.ፒ.ጄ የ2010- ሀሳብን የመግለጽ ነፃነት ሽልማት አሸናፊ የሆነው የአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ አገሩን ጥሎ ተሰደደ

የዘረኛውና አረመኔው የወያኔ አገዛዝ የሚያደርስባቸውን ግልጽና ስውር አፈና ተቋቁመው ህትመት ላይ ቀርተው ከነበሩ ጋዜጦች መካከል የአውራ አምባ ታየምስ ጋዜጣ ዋና መስራችና አዘጋጅ የነበረው ዳዊት ከበደ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጋዜጠኞች ላይ የተከፈተው አዲስ ዙር መንግሥታዊ ሽብርና ዛቻ ለህይወቱ አስግቶት አገር ጥሎ መኮብለሉን ኢሳት በትናትናው የዜና እወጃ ፕሮግራሙ ዘግቦአል።

የጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ አገር ጥሎ መሰደድ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ለስደት የተዳረጉ ጋዜጠኞችን ቁጥር ሶስት ያደረሰው ሲሆን ጋዜጠኛ ዳዊት ሲ.ፒ.ጄ የተባለው አለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት አስከባሪ ድርጅት የ2010- ሀሳብን የመግለጽ ነፃነት ሽልማት አሸናፊ ያደረገው ወጣት ጋዜጠኛ እንደሆነ ይታወቃል።

የ 1997 ምርጫን ተከትሎ ከቅንጅት መሪዎችና ከሌሎች ጋዜጠኞች ጋር ታስሮ የነበረውና ዕድሜ ልክ ከተፈረደበት በሁዋላ በይቅርታ የተፈታው ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ፣ የሚወዳትን አገሩን ጥሎ ለመሰደድ የተገደደበትን ምክንያት ሲገልጽ፤ የፖለቲካ ተቀናቃኞችንና ነጻ ጋዜጠኞችን ሆን ብሎ በማጥቃት ዳግም የምርጫ 97 አይነት ህዝባዊ የለውጥ መነሳሳት በአገሪቱ እንዳይፈጠር ሲባል ተረቆ ሥራ ላይ በዋለው የጸረ ሽብርተኝነት ህግ አዋጅ ሊከሰስ የፈጠራ ወንጀሎች እየተቀነባበሩበት መሆኑን ማስረጃ ስለደረሰው መሆኑን ገልጾአል።

የጸረ ሽብርተኝነት ህግ አገርንና ዜጎችን ከአሸባሪዎች ለመከላከል ተግባር መዋል ሲኖርበት መለስ ዜናዊ ግን የፖለቲካ ተቀናቃኞችንና ነጻ ሂሊና ያላቸውን ዜጎች ለማጥቃት እያዋለው ነው ያለው ጋዜጠኛ ዳዊት፤ በየትኛውም የአለማችን ክፍል ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ የሽብርተኝነት ትርጉም አገራችን ውስጥ ተፈጥሮ በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ እንደመድረክ አይነቶቹ ድርጅቶች ሁሉ በሽብርተኝነት እየተወነጀሉ ነው ብሎአል።

በርሱና በሙያ ባልደረቦቹ ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃትና ስጋትም ሲገልጽ እነ ውብሸት ታዬ፣ እስክንድ ነጋና ርእዮት አለሙ በሽብረተኝነት ተከሰው ማዕከላዊ እስር ቤት ከተወረወሩ ጊዜ ጀምሮ ስራቸውን በከፍተኛ ስጋትና ጭንቀት ውስጥ ሆነው ለማከናወን እንደተገደዱ አልሸሸገም።

አፋኙ የወያኔ አገዛዝ ኢትዮጵያዊያን እየደረሰባቸው ያለውን ግፍና በደል የሚያጋልጡና በአገዛዙም ላይ የሰላ ሂስ በሚያቀርቡ ጋዜጠኞች ሃገራቸውን ጥለው እንዲኮበልሉ የሚያደርግ ዛቻና ማስፈራሪያ እየፈጸመ መሆኑ በተከታታይ የተዘገበ ሲሆን በቅርቡ የፍትህ አምደኛ የሆነው ታዋቂው ሀያሲ አቤ ቶክቾው ወይም አበበ ቶላ፣ ከደህንነት ሀይሎች የተሰነዘረበትን ማስፈራሪያ ተከትሎ ከአገር መውጣቱ መዘገቡ ይታወሳል።

በሌላም በኩል የወያኔው አገዛዝ ጠንካራ ሂስ የሚያቀርቡበትን ጋዜጠኞች አሸባሪ እያለ ወደ እስር ቤት ማጎሩን በማስመልከት አለማቀፉ የጋዜጠኞች መብት ተንከባካቢ ድርጅት ማውገዙ ይታወሳል።