የመምህር የኔሰው አሙዋሙዋት የበርካታ ዜና አውታሮች ሽፋን ሆኖ ሰነበተ ዓለም አቀፍ ትኩረትንም እየሳበ ነው

የአረመኔውን የወያኔ አገዛዝ ግፍና በደል በመቃወም ራሱን በቤንዚን አርከፍክፎ በማቃጠሉ ኢትዮጵያዊው ቡአዚ የሚል ቅጽል ስም እየተሰጠው ያለው አርበኛው መምህር የኔሰው ገብሬ በተለይም በሃገር ውስጥና ከሃገር ውጭ ባሉት ኢትዮጵያዊያን ከፍተኛ የመወያያ አጀንዳ ሆኖ ሲሰነብት በርካታ የሬዲዮ ፕሮግራሞችና የመረጃ ድረገጾች ሰፊ ሽፋን ሰጥተው ሲዘክሩት ሰንብተዋል።

በሃገር ውስጥ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ በርካታ ወጣቶች የመምህር የኔሰው ገብሬ ሞት ከመቼውም በላይ የዘረኛውን አገዛዝ ለመጣል ለሚደረገው ትግል የሚያነሳሳቸውና ጽናትንም የሚሰጣቸው መሆኑን መግለጻቸውን አዲስ አበባ የሚገኘው ዘጋቢያችን ባስተላለፈልን ዘገባ አመልክቱአል። ወጣቶቹ ለዘጋቢያችን እንደተናገሩት የዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ግፍና በደል ሞልቶ የተረፈው ለየኔሰው ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያዊያን ጭምር በመሆኑ፣ የየኔሰው ሞት መከፈል የሚገባውን መስዋእትነት በመክፈል አምባገነኑን አገዛዝ በሚቻለው መንገድ ሁሉ ለመጣል በቆራጥነት እንዲነሱ እንደሚያነሳሳቸውና አደራም እንደሆነባቸው ገልጸዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በመላው አለም የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን፣ በቅርቡ ዘረኛና አምባገነኑን የወያኔን አገዛዝ በመቃወም ራሱን መስዋእት ያደረገውን መምህር የኔሰው ገብሬን ከፍተኛ የመወያያ አጀንዳቸው አድርገው የሰነበቱ ሲሆን ኢትዮጵያዊያኑ የኔሰው ገብሬ ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ በኢትዮጵያዊያን ላይ እያደረሰ ያለው ግፍና መከራ የመጨረሻው ደረጃ ላይ መድረሱን ማረጋገጫ ነው፣ እናም ሊከፈል የሚገባው መስዋ እትነት ሁሉ ተከፍሎ አገዛዙ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲወገድ የማድረጊያችን ወቅት አሁን ነው ብለዋል።

የየኔሰው ገብሬ መስዋእትነት የዘረኛውን አገዛዝ በሚቃወሙ የኢትዮጵያዊያን የመረጃ ድረገጾች፣ ሰፊ ሽፋን ተሰጥቶት የሰነበተ ሲሆን የአለም አቀፍ የዜና አውታር የሆነውን ቢቢሲን፣ እንዲሁም ቪ ኦ ኤና የጀርመን ሬዲዮ ጣቢያዎች ሽፋን ሰጥተውታል።

በሌላም በኩል የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ኢትዮጵያውያኑ ቀደም ብሎ በየፌስ ቡክ አድራሻቸው ላይ ይጠቀሙባቸው የነበሩ የየራሳቸውን ፎቶግራፎች በማንሳት በምትኩ የኔሰው ገብሬን ፎቶግራፍ የሚጠቀሙበትን ምክንያት አንዳንዶች እንደገለጹት “ወንድማችን የኔሰው በሀገራችን ውስጥ ነጻነት፣ ዲሞክራሲ እና የህግ የበላይነት እንዲመጣ ካለው ከፍተኛ ፍላጎት በመነሳት እራሱን በእሳት አቃጥሎ መሰዋቱን በቀላል እንደማንመለከተው እና እሱ የተሰዋለትን አላማ አንግበን እንደምንታገል ለመግለጽ ነው” ብለዋል። ሌሎች ደግሞ ሲያስረዱ “ጉዳዩ አገር አቀፍና አለም አቀፍ ትኩረት እንዲያገኝ”መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ የዬኔሰው ገብሬ አድናቂ ኢትዮጵያዊያን የሀዘን መግለጫዎችንና የተነሱ ጥሪዎችን እያስተላለፉ ሲሆን የቶሮንቶ የሰብአዊ መብቶችና የዲሞክራሲ ህብረት በየኔሰው ገብሬ ሞት የተሰማውን ሀዘን ገልጦ፣ የካናዳ መንግስት ለመለስ ዜናዊ መንግስት የሚሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ እንዲያቋርጥ ጠይቋል። የኢትዮጵያ ወጣቶች ለለውጥ አባል የሆነው ዮናታን ወግደረስ በበኩሉ የየኔሰው ሞት ለሁለት ቀን ያክል ህመም ፈጥሮበት እንደነበር ገልጦ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የግፍ አገዛዝ እንዲያበቃ ሁላችንም በጋራ እንነሳ ሲል ጥሪ አቅርቧል።

ታዋቂው የህግ ባለሙያና ጸሀፊ የሆኑት ፕሮፌሰር አለማዬሁ ገብረማርያም ደግሞ “ነጻነቴን ስጡኝ ወይም ግደሉኝ” በሚል ርእስ ባወጡት ጽሁፍ የኔሰው ፣ በአለም ላይ ለነጻነታቸው ሲሉ ራሳቸውን ከሰውትና ለዘላለሙ በታሪክ ሲዘከሩ ከሚኖሩ ጀግኖች መካከል ተቀላቅሎአል” ብለዋል።