በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየው የኑሮ ውድነት ከባድ ፈተና ሆኖብናል ሲል የወያኔ ሹም ኩማ ደመቅሳ አስታወቀ
ህወሃት ለሁለት በተከፈለበት ወቅት ከነ አቶ ተወልደ ቡድን ጋር በመወገኑ ከሥልጣን ተባሮ የነበረውና ቦኋላ ንሰሃ ገብቶ የመለስ ዜናዊን ቡድን በመቀላቀል ድህረ ምርጫ 97 የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ሆኖ ለመሾም የበቃው ኩማ ደመቅሳ በከተማው ውስጥ እየታየ ያለው የኑሮ ውድነት ከባድ ፈተና ሆኖብናል በማለት ከትናንት በስቲያ ማክሰኞ ለተሰበሰበው የወያኔ ፓርላማ አስታወቀ።
እንደ ኩማ ደመቅሳ አነጋገር ከተማውን ለከባድ ችግር ዳርጎታል የተባለው የኑሮ ውድነት መንስኤው አገዛዙ የዘረጋው ዘረኛ ድርጅታዊ መዋቅር እና የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሳይሆን በኢኮኖሚ የበለጸጉ አገሮች በገጠማቸው ቀውስ የተነሳ ነው። መለስ ዜናዊ ላለፉት 5 እና ከዚያም በላይ አመታት አገሪቷ በተከታታይ የሁለት አሃዝ እድገት አስመዝግባልች በማለት ባዶ ድስኩሮችን ለፕሮፖጋንዳ ፍጆታ በሚያሰማባቸው ወቅቶች አሁን የሚሳበብበት የአለም የኢኮኖሚ ቀውስ ምንም አንድምታ እንዳልነበረው ሲገለጽ የሰነበተ ቢሆንም ኩማ ደመቅሳና ሌሎች የበታች ባለሥልጣናት ግን የአለቃቸውን ቃል በመጻረር ችግሩን በሌሎች አገር ከተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ ጋር ለማመሳሰል ሲባዝኑ ይስተዋላል።
በማክሰኞ ዕለቱ የኩማ ንግግር ከተንጸባረቀው አንዱ “የአቅም ግንባታና የመልካም አስተዳደር እጦት ችግር እየተባባሰ መሄድ ሲሆን በአገር ሃብት ዘረፋና በሙስና የተዘፈቀው የወያኔ አገዛዝ በመንግሥታዊና አገልግሎት ሰጪ ተቋሞች ለፖለቲካ ሥር ዓቱ ታማኝነትንና ታዛዥነትን መስፈርት በማድረግ ምንም አቅምና ችሎታ የሌላቸውን ሰዎች ሲያሰማራ ቆይቶ አሁን ችግሩ የአገዛዙን የስልጣን ዕድመና ሂሊውና የሚፈታተንበት ወቅት ላይ ሲደርስ ማንን ለመወንጀል ወይም በማን ላይ ለማላከክ መወትወት እንደጀመረ የታወቀ ነገር የለም።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ሆኖ የተሾመውን ኩማ ደመቅሳን ጨምሮ የዛሬ 20 አመት ባዶ እጃቸውን አዲስ አበባ የገቡት አብዛኛዎቹ የወያኔ ባለሥልጣኖች ዛሬ ላካበቱት ሃብት መሠረቱ የአዲስ አበባን የከተማ መሬት በሚሪት እየወሰዱ አሳልፎ በመቸብቸብ የተገኘ እንደሆነ፤ የነርሱንም ዱካ ተከትለው ዛሬ በአቅም ማነስ እየተወነጀሉ ያሉት ካድሬዎች በሙሉ በዘረፋውና በሙስናው እንደተሰማሩ ህዝብ ጠንቅቆ ያውቃል።