ከመለስ ዜናዊ ክስ መረዳት የሚኖርብን ሃቅ!

የኢትዮጵያን ፍርድ ቤቶችን በቁጥጥራቸው ሥር ያደረጉት የመለስ ዜናዊ ካድሬዎች ሰሞኑን የተለመደ ድራማቸውን አጧጡፈዋል። የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ በሆኑት በአቶ አንዱዓለም አራጌ መዝገብ ውስጥ ሃያ አራት ዜጎች በበርካታ የፈጠራ የሽብር ወንጀሎች ተከሰዋል።  ከተከሳሾቹ ስምንቱ ብቻ ናቸው በመለስ መዳፍ ውስጥ ያሉት። ሌሎቹ  የገቡት ለማዳመቂያና ለማስፈራሪያ ነው።

አስራ ሰባት ገፆች ያሉት “የክስ ቻርድ” የተሰኘው ጦማር በየገጹ ሥር ከሚገኘው “ፍትህ በተለወጠ አመራር፤ በተለወጠ ሠራተኛ፣ በተለወጠ ተቋም” ከሚል አዝናኝ፣ አስቂኝና አስገራሚ መፈክር በስተቀር በይዘቱ ከምርጫ 97 ጀምሮ ከምናውቃቸው ተመሳሳይ እንቶ ፈንቶ ድርሳናት የተሻለ ነገር የለበትም።

በተከሳሽነት የተዘረዘሩት ዜጎችም ያው የተለመዱ ወገኖች ናቸው:

  • ለፍትህ፣ ለእኩልነት፣ ለነፃነትና ለዲሞክራሲ የቆሙ የፓለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችና አባላት፣
  • የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣
  • እውነትን ለመዘገብ የደፈሩ ጋዜጠኞች፣ እና
  • የማይታወቁ ሰዎች ናቸው፣

በምርጫ 97 ማግስት የወጣው የክስ ዝርዝርም የያዘው እነዚሁኑ ወገኖች ነበር።

ያም ሆኖ ግን ይህን ክስ ከዚህ በፊት ከነበሩት ተመሳሳይ ክሶች በሁለት አበይት ነገሮች ይለያል። እነዚህም:-

  1. ተከሳሾች በሙሉ የግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አመራርና አባላት ናቸው መባላቸው፤ እና
  2. ህገ-አልባነትን ህጋዊ ያደረገው “የፀረ- ሽብር” ህግ ተጠቅሶ የተከሰሱ መሆናቸው ናቸው።

እነዚህ ሁለት ነጥቦች በጥልቀት መጤን ያለባቸው ነገሮች ናቸው።

ለፍትህ፣ ለነፃነት፣ ለዲሞክራሲ፣ ለእኩልነት እና ለእውነት የቆመ ኢትዮጵያዊ የየትኛውም ድርጅት አባል ቢሆን፣ ወይም ደግሞ የማንኛውም ድርጅት አባል ባይሆን፣ ለመለስ ዜናዊ ለውጥ የለውም። በመለስ ዜናዊ አገዛዝ ሥር ባለችው ኢትዮጵያ ማንኛውም ለመብትና ለእውነት የቆመ ኢትዮጵያዊ በግንቦት 7 አባልነት ተፈርጆ በሽብርተኝነት  ሊከሰስ ይችላል።

ይህ ምን ማለት ነው?

ይህ ማለት ለፍትህ፣ ለነፃነት፣ ለዲሞክራሲ፣ ለእኩልነት እና ለእውነት የቆምን ዜጎች ሁሉ ትግላችንን ማስተባበር እንዳለብን የሚጠቁም ነው። ይህ በመካከላችን ያሉ ትናንንሽ ልዩነቶች ከትላልቆቹ ግቦቻችን አንፃር ሲታይ ቦታ የማይሰጣቸው መሆኑ ጎልቶ የታየበት ክስተት ነው። ይህ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ የተደረገ ጥሪ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ይህ ክስ፣ “የፀረ-ሽብር ህግ” ተብሎ የሚጠራው የመለስ ፓርላማ ውሳኔ በህግ፣ በህጋዊነትና በፍትህ ላይ እያደረሰ ያለውን ጥፋት አጉልቶ የሚያሳይ ነው። በዚህ “ህግ” ምክንያት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ አንዳችም የደህንነት  ዋስትና የሌለው መሆኑ ይህ ክስ አረጋግጧል።  ህግ የግለሰቦች መጫወቻ በሆነበት   አገር  ተፈርቶም ሆነ ተሸሽጎ የሚመለጥ ነገር የለም።

ህግ የግለሰቦች መጫወቻ በሆነበት  አገር በቅድሚያ መፈጸም  ያለበት ተግባር  ህጋዊ ሥርዓትን ማቆም ነው። ህጋዊ ሥርዓት ሳይኖር ስለምንም ሌላ ነገር (ለምሳሌ ስለ ተለያዩ ፓሊሲዎች) መናገር ፋይዳ የለውም። በአገራችን ህጋዊ ሥርዓት ማቆም ማለት የመለስ ዜናዊን ዘረኛ ቡድን ከሥልጣን ማባረር ማለት ነው። ይህ ተግባር ጊዜ የማይሰጥ አጣዳፊ ጉዳይ እንደሆነ ክሱ በሚገባ አረጋግጧል።

ስለሆነም ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ በመለስ ዜናዊ ዘረኛ አምባገነን ሥርዓት “ሽብርተኛ” ተብላችሁ የተፈረጃችሁ ወይም ነገ መፈረጃችሁ የማይቀር ለፍትህ፣ ለነፃነት፣ ለዲሞክራሲ፣ ለእኩልነት እና ለእውነት የቆማችሁ ዜጎች ሁሉ በአንድ  ላይ ቆመን የአገዛዙን ፍፃሜ እንድናፋጥን ጥሪ ያደርጋል።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!