የከተማ ውስጥ ረሃብ በኢትዮጵያ መስፋፋቱን እንደቀጠለ ዘገባዎች አመለከቱ
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት ተማሪዎች ከረሃብ የተነሳ እራሳቸውን እየሳቱ እንደሚወድቁ ዘገባዎች አመልክተዋል።
የግንቦት 7 ድምጽ ሬድዮ ባለፈው አመት ግንቦት ወር፥ በርካታ ህጻናት በቂ ምግብ ካለማግኘታቸው የተነሳ በየትምህርት ቤቶች እራሳቸውን መቆጣጠር እያቃተቸው እንደሚወድቁ መምህራንን በመጥቀስ መዘገቡ ይታወሳል።
ሰሞኑን ለዝግጅት ክፍላችን የደረሰ መረጃ እንዳመለከተው፤ አዲስ ቲቪ የተባለው እና በወያኔ ቁጥጥር ስር የሚገኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ ቃለ መጠይቅ ያደረጋቸው መምህራን እና የአንድ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ሰራተኞች የችግሩን መኖር አረጋግጠዋል። የአስተዳደር ሰራተኛዋ በተለይ በክፍለ ከተማው ብቻ ይህ ችግር እስካሁን በ7 ሺህ ተማሪዎች ላይ መከሰቱን እንደመሰከረች ለማወቅ ተችሏል።
እራሳቸውን እየሳቱ የሚወድቁ ህጻናት በተደጋጋሚ እንደሚያጋጥሟቸው የተናገሩት መምህራን፤ ዳቦ ገዝተው ሲያበሏቸው እንደሚሻላቸው ማስተዋላቸውንም በቃለ መጠይቁ ገልጸዋል።
የወያኔ አገዛዝ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የኢኮኖሚ እድገት እንዳለ በተደጋጋሚ ቢናገርም፤ አብዛኛው ህዝብ ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ከፋ የድህነት አረንቋ እየገባ እንደሆነ ተመልካቾች ይናገራሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ በየአመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች የእርዳታ ጥገኞች እንደሆኑ ቢታወቅም፤ አብዛኞቹ ተቆጣሪዎች ግን የገጠር ነዋሪዎች ናቸው። የከተማ ውስጥ ድህነት እስካሁን በቂ ትኩረት ሳያገኝ ቆይቷል።
ከአንድ አመት በፊት ጄኒፈር ፓርሜሊ የተባሉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰራተኛ፥ “ኢትዮጵያ ውስጥ ደሃ ቤተሰቦች ምግብ በፈረቃ መብላት ጀምረዋል። ታላቁ ልጅ ሰኞ፤ መሃከለኛው ማክሰኞ፤ ታናሹ እሮብ እያለ ይቀጥላል” በማለት መመስከራቸው ይታወሳል።