የኃየሎም አርአያ አሟሟትና የጀሚል ያሲን አገዳደል! የመጨረሻ ክፍል በዳዊት ከበደ ወየሳ (አትላንታ)
ይህ የመጨረሻው ክፍል ነው። የመጨረሻውን ክፍል ከማቅረቤ በፊት የጽሁፌን አሃድ በምስጋና ልጀምር። ሁልጊዜ በህሊናዬ የነበረውን… ነገር ግን ለመጻፍ ጊዜ አጥቼ በነበረበት ወቅት ብርታት ለሆነኝ የእውነት እና የፍቅር አምላክ ምስጋና ይጋባው። ምንም እንኳን ባላነበውም ስለጽሁፉ በሰማሁ ጊዜ… ይህንን ታሪክ ለመጻፍ ምክንያት የሆነኝን የኢትዮ ሚዲያ ባለቤት አብርሃ በላይን በንፁህ ልቤ አመሰግነዋለሁ። ይህንን ጽሁፍ በነጻ ህሊና በድረ ገጾቻችሁና በሬዲዮናቸው ላይ ላቀረቡ ጋዜጠኞች፤ እንዲሁም ጊዜያቸውን ወስደው ይህን ታሪክ በመስማትና በማንበብ (ብትቀበሉትም ባትቀበሉትም) በጨዋ ኢትዮጵያዊነት ሃሳብ የሰጡኝን በሙሉ… በጽሁፍ ምስክርነታችውን የሰጡኝንም ጭምር፤ እኔም በተራዬ እጅ በመንሳት “እግዚአብሄር ያክብርልኝ” እላለሁ።
በመጨረሻም ይህንን ታሪክ ሥጽፍ አንዳንድ የህግ ጉዳዮች ብዥታ ሲፈጥሩብኝ፤ በምክር የረዱኝን ዳኛ ወልደሚካኤልን አመሰግናለሁ። ለብዙ አመታት አብረውኝ በነጻ ጋዜጠኝነት ለሰሩ የሙያ አጋሮቼም ምስጋና ይድረሳቸው። በፎረማችን ውስጥ ሃሳብ የሰጡትን እዚያው አመስግኛለሁ። ከዚያ ውጪ ግን እንደኔው የጀሚልን ጉዳይ እየተከታተለ ያቀርብ የነበረውን የመብሩክ ጋዜጣውን ሰይፉ መኮንን… የረሳኋቸውን ነገር እያስታወሱ የነገሩኝን የማዕበሉን አክሊሉ ታደሰ፣ የሞገዱን ክንፉ አሰፋ እና የኢትኦጱን ሲሳይ አጌና ላመሰግን እወዳለሁ። አሁን ስሟን ዘነጋሁት መሰለኝ… (ሃያት?) የጀሚል እህት በውጭ እየተገናኘን፤ ከጀሚል የሚላኩትን ደብዳቤዎች ታመጣልኝ… ስለወንድሟም ሁኔታ ታስረዳኝ ነበር። የቤተሰብ ፎቶ ያለበትንም አልበም የሰጠችኝ እሷ ናት። ባለችበት ምስጋናዬ ለሷም ይድረስ። በመጨረሻም አገር ቤት ይህንን ጉዳይ ስከታተል ፍርድ ቤት እየላኩ፤ ዜናውን እንዲዘግቡ አስቸግራቸው የነበሩ ወንድሞቼን ሃብታሙና ብሩክን ነገሩ አስር አመት ቢያልፈውም አመሰግናቸዋለሁ።
የኃየሎም አርአያ አሟሟትና የጀሚል ያሲን አገዳደል!
የመጨረሻ ክፍል
በዳዊት ከበደ ወየሳ (አትላንታ)
የካቲት 6 ለሊት፣ 1988 ዓ.ም. ኃየሎም አርአያ በተተኮሰበት ጥይት ግንባሩን ተመትቶ መገደሉን ፖሊስ አረጋግጧል። ግድያውን የፈጸመው ጀሚል ያሲንም ድርጊቱን አምኗል። ሁሉም ምስክሮች ጸቡ ድንገት እንደተጀመረ አረጋግጠው፤ የአልኮል መጠጡም ጸቡን ይባስ እንዳባባሰው አልካዱም። ጀሚል ቃታ ከመሳቡ በፊት፤ ኃየሎም በጥፊ የመታው መሆኑን… ሁሉም በስፍራው የነበሩት ምስክሮች የሰጡት ቃል ምስክር ነው።
እነዚህ ምስክሮች አቃቤ ህጉ በሚፈልገው መንገድ ምስክርነታቸውን ካልሰጡ፤ ሊደርስባቸው የሚችለውን ወከባ አላጡትም። ሆኖም ያዩትን መስክረዋልና… ማንንም ሳይፈሩ ያዩትን እውነት ተናግረዋልና ክብር ለ’ነሱ ይሁን።
በሌላ አንጻር ደግሞ የአቃቤ ህጉ አቶ መስፍን ግርማ ደጋግሞ ፍርድ ቤቱን በሞገተው መሰረት ጀሚል በሞት እንዲቀጣ ብሏል። የጀሚል ጠበቃ አቶ አህመድ ደግሞ… መጀመሪያ የተማታው ኃየሎም መሆኑን ገልጾ በምስክሮቹ ቃል መሰረት… የጸቡን ድንገተኛነትና ገዳዩ ወንጀሉን የፈጸመው በስካር መንፈስ መሆኑን አብራርቶ፤ ጉዳዩ መታየት ያለበት ራስን ከመከላከል ወይም በአልሞት ባይ ተጋዳይነት አንጻር በመሆኑ የሞት ፍርዱ እንዲቀል ጠይቋል። ሆኖም የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለት ለአንድ በሆነ ድምፅ በጀሚል ላይ የሞት ፍርዱን ያጸኑበት መሆኑን በክፍል ሁለት ጽሁፌ ላይ ገልጫለሁ።
ከዚህ በኋላ ጀሚልን ለመግደል የሚጠበቀው የኢትዮጵያ ርዕሰ ብሔር የነበሩት የዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ፊርማ ነበር። የግድያው ፊርማ የዘገየው… ፕሬዘዳንቱ ሰውን ለመግደል ወይም ለማስገደል ሃይማኖታቸው ስለማይፈቅድላቸው መሆኑ በጋዜጦች ላይ ታትሞ ወጣ። በዚህ መሃል ግን ፕሬዘዳንቱ ባይፈርሙም ግድያውን ሊያፋጥን የሚችል ነገር ከወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ይሰማ ጀመር። በጥቅምት ወር የተጀመረውና ከገንዘብ ለውጥ ጋር ተያይዞ የመጣው የናቅፋ ቅርሽ፤ የባድመን ቁርሾ ወለደ። ከወራት ውዝግም በኋላ… በአይ.ኤም.ኤፍ እና የአለም ባንክ አደራዳሪነት… በወቅቱ ለስብሰባ አስመራ ላይ የሄደው፤ በኢኮኖሚና ትብብር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ግርማ ብሩ ይመራ የነበረው የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን፤ በጠመንጃ ከሆቴላቸው እንዲወጡ ተደርገው እና ተሰድበው ከአስመራ እንዲወጡ ሲደረግ ነገሩ ደስ የማይል ስሜት ፈጥሮ ነበር። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ… የነግርማ ብሩን ከሆቴላቸው መባረር ጨምሮ በገንዘብ ልውውጡ ዙሪያ የነበረውን ውጥረት ነጻው ፕሬስ መዘገቡን ቀጠለ። ከዚያም በድንበር አካባቢ በብር እና በናቅፋ ልውውጥ ምክንያት የተነሱ ፀቦችን ጋዜጦች አስነበቡ። ሆኖም እውነተኛው ቀን እስኪመጣ ድረስ ብዙም ሰሚ ያጣ ወሬ ሆኖ ነበር። መለስ ዜናዊም አጋጣሚውን በመጠቀም ነጻ ጋዜጦችን ያዋረደ መስሎት፤ “በሁለቱ አገሮች መካከል ምንም አይነት የኢኮኖሚም ሆነ የድንበር ግጭት የለም” ሲል መግለጫ ሰጠ።
የድንበሩን ግጭት ከዘገቡት መሃከል የማዕበል ጋዜጣ አዘጋጅ፤ አበራ ወጊ… ታሰረ። የትግራይ ፕሬዘዳንት ገብሩ አስራትም “እንኳን የተተኮሰ የባረቀም ጥይት የለም” ሲል ተጨማሪ መግለጫ ሰጡ።
ይህ ሁሉ የሆነው የኃየሎም አርአያ 2ኛ ሙት አመት ከመድረሱ ቀደም ብሎ ነበር። መለስ ዜናዊ የድንበሩን ጉዳይ ቢክድም፤ በትግራይ አካባቢ የነበረው እውነታ ግን ከዚህ የተለየ ነው። ህዝቡ “ኃየሎም ቢኖር ኖሮ…” እያለ ቁጭቱን መናገር ጀምሯል። ይህንን “ኃየሎም ኃየሎም” እያለ የሚንተገተግ ቁጭት ለማብረድ… የኃየሎም ሁለተኛ ሙት አመት ከመከበሩ አንድ ሳምንት በፊት፤ ጥር 29 ቀን፣ 1990 ዓ.ም. ጀሚል ያሲን ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ተደርጎ ሞት ተፈረደበት።
ሆኖም ሞት የተፈረደበትን ሰው ወዲያው አይገደልም። ይህ አይነቱ የህግ ቢሮክራሲ ህወሃትን ውስጥ ውስጡን ያቃጥለው ጀመር። ምክንያቱም በኢትዮጵያ ህግ መሰረት አንድ ሰው ሞት ሲፈረድበት፤ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤት ማለት ይችላል። የሞት ፍርደኛው አቤት ማለት ባይፈልግም ወይም ፍርደኛው “በቃ ግደሉኝ” ቢልም እንኳን፤ ለደንቡም ያህል ቢሆን ጉዳዩ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ተወስዶ ውሳኔ ይሰጠዋል። በመሆኑም የህወሃት ሰዎች ጀሚልን በየካቲት 1990 ዓ.ም. ለመግደል የነበራቸው ጉጉት ሳይሳካ ቀረ። ስለዚህ ቢያንስ ግንቦት ሃያ ሲከበር፤ ጀሚልን በመግደል በዓሉን ማድመቅ አስፈለገ። እናም ከግንቦት ሃያ 1990 በፊት በማናቸውም መልክ ጀሚል እንዲገደል ቁርጥ ውሳኔ ተደረገ።
ጉዳዩ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሄዶ ውሳኔ ከመሰጠቱ አስቀድሞ… ጀሚል ደግሞ በምን አይነት ሁኔታ እንደተገደለ ከማውጋቴ በፊት፤ አንዳንድ ነገሮችን ወደ ኋላ መለስ ብዬ ላጫውታችሁ ፈለግኩ። ከላይ የገለጽኩት የናቅፋና የብር ጉዳይ እነግርማ ብሩን ካረፉበት ሆቴል በጠመንጃ አስወጥቶ ሜዳ ላይ ሲጥላቸው፤ የኢትዮጵያና የኤርትራ የወደፊት መልካም ግንኙነት ጥያቄ ውስጥ መግባት ጀመረ። ይህም የኃየሎም ጉዳይ በሠራዊቱ ውስጥ እንደገና እንዲነሳ እንዳደረገው ሁሉ፤ ታይቶና ተሰምቶ በማያውቅ ሁኔታ የጀሚል ያሲንንም ሞት አፋጥኖታል። ከዚያ በፊት ግን በሻዕቢያና በህወሃት ፍቅር መካከል ጣልቃ የገባውን የኢህዴን ድርጅት ጉዳይ በዚህ አጋጣሚ ማንሳቱ… በስተበኋላ ላይ ስለ21ኛው ሜካናይዝድ ብርጌድ መመታትና የጀሚልን አሟሟት ታሪክ ያጠናክረዋልና በትዝታ ጥቂት ወደኋላ እወስዳችኋለሁ።
ኢህአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ከህወሃት ባልተናነሰ መልኩ የኢህዴን እና የሻዕቢያ ወታደሮች ይታወሱናል። የኢህዴን ወታደሮች አማርኛ ተናጋሪዎች በመሆናቸው ቁልፍ የሆኑትን የአዲስ አበባ መንግስት መስሪያ ቤቶችን የተቆጣጠሩት እነሱ ነበሩ። በሌላ በኩል ድግሞ ወያኔና ሻዕቢያ ትኩረታቸውን ያደረጉት በወታደራዊ ጉዳዮች ላይ ሲሆን፤ የጋራ ወታደራዊ አመራር እስከመስጠት ደርሰው ነበር። በደብረዘይት የሚገኙ የጦር አውሮፕላኖች በሙሉ ወደ አስመራ ተወስደው፤ እዚያ እንዲቆዩ ሲደረግ የኢህዴን ሰዎች ቅሬታቸውን የገለጹ መሆኑ ይታወሳል። የኢትዮጵያ የባህር ኃይል የጦር መርከቦችን ወደ ኤርትራ ወደቦች ለመውሰድ የተደረገው የመጀመሪያ ጥረት የከሸፈው በኢህዴን ሰዎች ነበር። የበቅሎ ቤቱ ፍንዳታ መንስዔም በጥበቃ ላይ የነበሩት የኢህዴን ታጋዮች እና የሻዕቢያ ሰዎች ነበሩ። ግንቦት 27 1983 ዓ.ም. የጦር ግምጃ ቤቱ የጥበቃ ተራ በኢህዴን ጋንታዎች ስር ነበር፤ የሻዕቢያ ወታደሮች ቀደም ባሉት ቀናት ያደርጉ እንደበረው ከባድ የጦር መሳሪያ ጭነው ሊወጡ ሲሉ… “አናስወጣም” አሏቸው። በዚህ ምክንያት የተፈጠረው አለመግባባት ከጠመንጃ አልፎ የላውንቸውር ተኩስ አስነሳ… ከሻዕቢያ የተተኮሰው ላውንቸርም የበቅሎ ቤቱን የጦር ግምጃ ቤት ሙሉ ለሙሉ አወደመው።
ከነዚህ ነጥቦች በመነሳት… በኢህአዴግ ውስጥ የመጀመሪያ የ’ርስ በርስ ግጭት የተጀመረው በህወሃትና በኢህዴን መካከል መሆኑን ልናሰምርበት እንችላለን። የመለስ ህወሃት ቡድንም ኢህዴንን ዝም ለማሰኘት መጀመሪያ የተጠቀመው ሻዕቢያን መሆኑ፤ በኋላ ላይ ኃየሎም ሲገደል የጥርጣሬው ቀስት መልሶ እነሱን የወጋ መሆኑን በስተበኋላ ላይ እንመለከታለን። በወቅቱ ሆኖም ሻዕቢያን በኢትዮጵያ በውስጥ ጉዳይ እንዲገባ በማድረግ፤ ኢህዴን የሚባለውን የአማርኛ ተናጋሪ ድርጅት ቀስ በቀስ ለመደምሰስ ስለተጀመረው የቤት ስራ ጥቂት ላውጋችሁ።
በወቅቱ አምስቱ የኢህዴን ፖሊትቢሮ ከፍተኛ አመራሮች ታምራት ላይኔ፣ በረከት ስምኦን፣ ተፈራ ዋልዋ፣ አዲሱ ለገሰ እና ሙሉአለም አበበ መሆናቸውን ልብ ይበሉ። በታምራት ላይ የተደረገውን እስር ወይም ስለበረከት ኤርትራዊነት፤ አልያም ስለአዲሱ ለገሰ እና ተፈራ ዋልዋ ተንበርካኪነት በመዘርዘር ጊዜ ማጥፋት የለብንም። ነገር ግን ከአምስቱ አንዱ ስለነበረውና በሽግግሩ ዘመን የመጀመሪያውን የሞት ፅዋ ስለተቀበለው ወጣት የኢህዴን አመራር ሙሉአለም አበበ ማንሳት አስፈላጊ ነው። ኢህአዴግ አዲስ አበባ ሲገባ… ሙሉአለም አበበ በታሪክ ውስጥ 24ኛው የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆነ። የበቅሎ ቤቱ ፍንዳታ ከኢህዴን ታጋዮች ጋር ተቀብሮ ቀረ። የኢህዴንና የሻዕቢያ ሰዎች ሽኩቻ ግን አላበቃም። አዲስ አበባን ከተቆጣጠሩ በኋላ ራሳቸውን እንደአንደኛ ዜጋ እያደረጉ ህዝቡን ይረብሹ የነበሩ የሻዕቢያ ሰዎችን ገደብ ማስያዝ የአዲስ አበባ ከንቲባ ሃላፊነት በመሆኑ፤ ከንቲባው የሚወስዳቸው እርምጃዎች ሻዕቢያ/ህወሃትን ገና በሽግግሩ ዘመን ማስከፋት ጀመረ። በመሆኑም ከንቲባ ሙሉአለምን ማስወገድ አማራጭ ሆነና “ለስብሰባ ትፈለጋለህ” ተብሎ ወደ ባህር ዳር ተጠራ። ባህር ዳር… በተዘጋጀለት ቢሮ ውስጥ ብቻውን በነበረበት ወቅት፤ ቀደም ብሎ በስፍራው በነበሩት የህወሃትና የሻዕቢያ ሰዎች በተዘጋጀ የተጠመደ ቦንብ ከነቢሮው ብትንትኑ ወጣ።
ይህ በሙሉአለም ላይ የተወሰደው እርምጃ የኢህዴን ሰዎችን ዝም ለማሰኘት ታስቦ የተደረገ ነበር። በ’ርግጥም ፈርተው ይሁን ወይም እጃቸው ስላለበት አይታወቅም… ታምራት፣ በረከት፣ ተፈራና አዲሱ ስለሙሉአለም ሞትና አሟሟት ዝም አሉ። ውስጥ ውስጡን ግን የኢህዴን ሰራዊት ቅሬታውን ማሰማቱ አልቀረም። ይህንን ቅሬታ ለመሸፋፈን ሲባል ወይም ተፈራ እጁ ስለነበረበት አይታወቅም… በሙሉአለም ምትክ ተፈራ ዋልዋ የአዲስ አበባ ከንቲባ ሆኖ ቀጠለ። በተገደለው በሙሉአለም ስም ደግሞ በባህር ዳር ውስጥ ትልቅ አዳራሽ ተሰርቶ፤ በስሙ ተሰየመለት… “ሙሉአለም አዳራሽ” ተሰኘ። ህዝቡም እንባውን እያበሰ ዝም አለ።
ይህንን ጉዳይ ያነሳሁት ስለ ኢህዴን እና ሻዕቢያ ግጭት ለመተረክ አይደለም። ነገር ግን ገና ከጅምሩ የመለስ ህወሃት ቡድን ሻዕቢያን በመጠቀም ሰዎችን እንዴት አድርጎ ያስወግድ እንደነበረና ድንገት የኃየሎም ሞት ደግሞ በተመሳሳይ መልኩ ያደረሰባቸውን ጉዳት ለማሳየት ነው። እርግጥ ነው… የሻዕቢያ አመራር በኢትዮጵያ የመንግስት አስተዳደር ውስጥ ገብቶ መስራቱን ህዝቡ ሲቃወም፤ የነጻ ፕሬስ ጋዜጦችም ይህንኑ ጩኸት ሲያስተጋቡ ቆይተዋል። የመለስ ዜናዊ አጃቢዎች ሙሉ ለሙሉ የሻዕቢያ ሰዎች የነበሩ ሲሆን፤ አብዛኞቹ በሰራዊቱ ውስጥ በሻምበል እና በሻለቃ ማዕረግ የተቀመጡት መኮንኖች ግማሽ ኤርትራዊና ግማሽ የትግራይ ሰዎች ሆነው እንዲዋቀሩ ተደርጓል።
እነሆ በመለስ ዜናዊ አማካኝነት ኢትዮጵያ በሯን ወለል አድርጋ ከፍታ ሻዕቢያን ያለገደብ ስታስተናግድ ቆየች። ይህ ሁኔታ በህዝቡና በሰራዊቱ ውስጥ ቅሬታን ፈጥሮ ሳለ፤ አንድ ኤርትራዊ አንድን የህወሃት የጦር መሪ በመግደሉ… ቀደም ሲል ለነበረው ሃሜት ማጠናከሪያ ሆነ። ሙሉአለም በተጠመደ ፈንጂ ቢሮ ውስጥ ሲገደል ትንፋሽ ያጠረው ሰራዊት፤ የኃየሎምን ግድያ መሸከም አቅቶት ተንገዳገደ… ከዚህ በፊት በግልፅ ይደረጉ የነበሩትን የሻዕቢያና የህወሃት የግፍ ስራዎችን በመዘርዘር ጊዜ አናጠፋም። ነገር ግን ቀደም ብሎ ሻዕቢያና የመለስ ህወሃት ቡድን ሙሉአለም አበበን ካስገደሉ፤ አሁንም በኃየሎም ሞት መለስና ሻዕቢያን ሰው ቢጠረጥር… ነገሩ እውነት እንጂ ሃሰት አይመስልም። በመሆኑም በኃየሎም ግድያ የመለስ ህወሃት ቡድን ምንም ግንኙነት የሌለው መሆኑን ለማሳመን ብዙ ጥረቶችን አድርጓል። ሆኖም በሙሉአለም አበበ ላይ ያደረጉት የተቀነባበረ የግፍ ግድያ እና ሌላም ተመሳሳይ ታሪካቸው አሁንም ድረስ እየተከተለ… እየከተከተ አንካሳ አደረጋቸው።
መለስ ዜናዊ እራሱን ነጻ ለማድረግ ወይም በኃየሎም አርአያ ግድያ እጁ የሌለበት መሆኑን ለማሳመን ብዙ ጥረት አድርጓል። በመቃብሩ ላይ ተገኝቶ ስቅስቅ ብሎ እንደሴት ሲያለቅስ በቲቪ ታይቷል። ኃየሎም ከሞተ በኋላ የሜጄር ጄነራልነት ማዕረግ ሰጥቶታል። ከሞተ በኋላ አንድ የጦር መኮንን በህይወት ሳለ የሚደረግለትን ጥቅማ ጥቅም አስጠብቆለታል። ሌላው ቀርቶ ኃየሎም ከሞተ በኋላ በስሙ የመኖሪያ ቤት ማሰሪያ መሬት በነጻ እንዲሰጥ ተደረገ። ይህም ሁሉ ሆኖ አብዛኛውን ታጋይም ሆነ ህዝብ ለማሳመን… (ዛሬም ድረስ) አስቸጋሪ ሆነ። እናም መለስ ዜናዊ ንፁህ መሆኑን ለማሳየት የሚችለው፤ የኃየሎም ገዳይ ላይ የሞት ፍርድ አሰጥቶ ማስገደል ሲችል መሆኑ ግልፅ ነበር። ስለሆነም በ7ኛው የኢህአዴግ የግንቦት ሃያ በዓል ጀሚልን በሞት መሰዊያው ላይ ለማስቀመጥ ወሰነ።
7ኛው የግንቦት ሃያ በዓል ከመድረሱ 3 ሳምንት በፊት ግን ሚያዝያ 28 ቀን፣ 1990 ዓ.ም. የኤርትራ ወታደሮች የጋሽ ሰቲትን ወንዝ ተሻግረው፤ የባድመን ከፍታ ቦታዎች ያዙ። ከዚያም የታህታይ እና ላዕላይ አዲያቦ ወረዳዎችን ወረሩ። በስፍራው የነበሩትን ፖሊሶችና ሚሊሻዎችን ገደሉ… ህዝቡም ተፈናቀለ። እነ ግርማ ብሩን ከአስመራ ሆቴላቸው ያስወጣው ድግን ጠመንጃ ባድመ ላይ ተተኮሰ። ብዙ ሰዎች ከሞቱ በኋላ ግንቦት 4 ቀን፣ 1990 ዓ.ም. ዜናው በሬዲዮና በቴሌቪዥን ሲለቀቅ ዜናው በመላው አገሪቱ አስደንጋጭ እና አስፈሪ ድባብ ጣለ። ጦርነቱ ከመነሳቱ በፊት በድንበር አካባቢ የነበረውን ግጭት ይዘግቡ የነበሩት ነጻ ጋዜጦች ተነባቢነታቸው በአስር እጥፍ አደገ። ወቅቱ ስለባድመ፣ ስለፆረና ዛላንበሳ እና ቡሬ የሚወራበት ወቅት በመሆኑ፤ እንኳንስ የጀሚል ያሲን ጉዳይ ቀርቶ ሌሎች ትላልቅ አገራዊ ጉዳዮችም በዚህ የወሬ ማዕበል ውስጥ ተዋጡ።
ጦርነቱ ሲጀመር የተጠናከረ ሜካናይዝድ ጦር ወደ ስፍራው መላክ ስላስፈለገ፤ ተቀማጭነቱን አዲስ አበባ 4ኛ ክፍለ ጦር ያደረገው 21ኛ ሜካናይዝድ ብርጌድ እንዲዘጋጅ ተደረገ። ይህ ብርጌድ በአብዛኛው የኢህዴን ተዋጊዎች የነበሩበት ሲሆን፤ ቀድሞም ከሻዕቢያ ጋር በነበረው ቁርሾ ምክንያት በመጀመሪያው ረድፍ እንዲሰለፍ ሲደረግ ጦሩ ያለምንም ማቅማማት ተነሳሳ። ቀደም ሲል እንደገለጽኩት… ኢህአዴግ አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ይህ ብርጌድ በኢህዴን ጦር ስር ሆኖ በግንባር ቀደምትነት የተሰለፈ ነበር። ገና በመጀመሪያው ሳምንት ጥበቃ ላይ ሳሉ፤ “የበቅሎ ቤቱን የጦር ግምጃ ቤት አናዘርፍም” በማለታቸውና ከሻዕቢያ ጋር ባደረጉት ውጊያ… የጦር ግምጃ ቤቱ እንዳለ መፈንዳቱን እናስታውሳለን።
እናም ይህ ብርጌድ ቀድሞውኑም ከሻዕቢያ ጋር እልህ የተጋባ ጦር ሲሆን፤ ከህወሃት ጋርም በአንዳንድ ነጥቦች አይስማማም። ለምሳሌ የዚህ ጦር አባላት በተለይም ከሰሜን ወሎ፣ ከራያ፣ ከአዘቦ እና ከሰቆጣ የተውጣጡ አባላት ናቸው። ህወሃት መሳሪያ ያስታጥቃቸው እንጂ፤ ምድባቸው በኢህዴን ስር ነው። ቋንቋቸው አማርኛ ይሁን እንጂ፤ ጭፈራና ሽለላቸው በትግሪኛ ነው። ከሽግግሩ መንግስት በኋላ ክልላቸው ወደ ትግራይ ሲሄድ፤ “እህህ” እያሉ፤ ቀኝ እግራቸውን ኢህዴን ሌላኛው ህወሃት ላይ አድርገው ቆይተው ነበር። በመሆኑም ይህ ጦርነት ሲነሳ ወደ ባድመ ለመዝመት “ሆ” ብለው ተነሱ… “ከባድመ መልስ ወደ መለስ!” ብለው እየጨፈሩ፤ ተኩሳቸውን ወደ ሰማይ እያንዶቀዶቁ፤ አዲስ አበባን ለቀው ሲወጡ ህዝቡም በሆታ አጅቦ ሸኛቸው።
ጦርነቱ እንደተጀመረ… ቀደም ሲል የባድመ ክፍታ ቦታዎችን በጦር ሃይሉ የያዘው ሻዕቢያ መሳሪያዎቹን ደግኖ ታቹን በሚመጣው የኢትዮጵያ ጦር ላይ የጥይት በረዶ ያዘንብበት ነበር። ሆኖም የ21ኛው ሜካናይዝድ ብርጌድ በስፍራው መገኘት ለብዙዎቹ የሰራዊቱ አባላት የሞራል ድጋፍ ሆናቸው።
“ከባድመ መልስ ወደ መለስ!” ብሎ የዘመተው ብርጌድ… በመጀመሪያው ረድፍ ገብቶ እንዲዋጋ ሲደረግ ብዙዎቹ ለአገራቸው ክብር ተሰዉ። በመጀመሪያው ሳምንት ጦርነት ብቻ ከአርባ ሺህ በላይ ወታደሮች በባድመ ተራራዎች ላይ ህይወታቸው ሲያልፍ… 21ኛው ብርጌድም በዚህ የታሪክ አጋጣሚ በሻዕቢያ እንዲደመሰስ ተደረገ። የኢህዴን ሰራዊት ያነሳ የነበራቸው የኢትዮጵያዊነትና የፍትህ ጥያቄዎች… ከዚህ ብርጌድ ጋር አብረው ተደመሰሱ። በወቅቱ ይህንን ከዘገቡት የነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች በቀር ሌሎች ይህ ታሪክ በይፋ ሳይነገር ቀረ። ሆኖም ጦርነቱ እየገፋ ሲመጣ… የህወሃት ሰዎችም ስለ21ኛው ብርጌድ መደምሰሰ ጥያቄ ያነሱ ጀመር።
ኃየሎምን በመተካት በደቡብ ኢትዮጵያ ተመድቦ የነበረው ሳሞራ የኑስ፤ በሚያዝያ 1990 ዓ.ም. የደቡብ ስራውን ጨርሶ፤ አሸኛኘት ተደርጎለት አዲስ አበባ እያለ ነው ይህ ጦርነት የተቀሰቀሰው። ምንም እንኳን ስለጦርነቱ አዝማሚያ ቀደም ሲል ዝርዝር መረጃ አልነበረውም። ሆኖም ስለድንበሩ ግጭት ቀደም ሲል መረጃ ተልኮለት ምላሽ ያልሰጠው መለስ ዜናዊ ሲገመገም… ሳሞራ ከመለስ ዜናዊ ጎን በመቆም ውለታ ዋለለት። በተለይም በጦርነቱ ማግስት በህወሃት ውስጥ በተደረገው ዝግ ስብሰባ ወቅት የመለስ ዜናዊ የወደፊት እድል ጨለማ አጥልቶበት ሳለ፤ ሳሞራ የኑስ… “አሁን ጠላት የሆነውን ሻዕቢያ ከወጋን በኋላ እንነጋገራለን” በማለቱ በግምገማ እሳት ይለበለብ የነበረውን መለስ ዜናዊ ከውድቀት አተረፈው።
በወቅቱ በተደረገው ዝግ ስብሰባ ላይ በመለስ ዜናዊ ላይ ያነጣጠሩት ጥያቄዎች እና ክሶችን በጋዜጣዬ ላይ በዝርዝር ለህትመት አብቅቻለሁ። ከዚህ ቀጥሎ የምገልጸው የማስታውሳቸውን በመሆኑ፤ ትክክለኛ ቀኑን፤ ማን ምን እንዳለ ረስቼዋለሁ። ከዋና ዋና ክሶች መካከል ጥቂቶቹ እነዚህ ነበሩ፦
1ኛ – ሻዕቢያ ድንበር ተሻግሮ ባድመን በወረረበት ወቅት፤ መለስ ዜናዊ ለሚመራው የአዲስ አበባ መንግስት አመልክተን አስቸኳይ እርምጃ ባለመወሰዱ በሺህ የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ሞተዋል ተፈናቅለዋል።
2ኛ – በመለስ ዜናዊ አማካኝነት ሻምበል እና ሻለቃ ተብለው በሰራዊቱ ውስጥ የተመደቡት ግማሽ ኤርትራዊ መኮንኖች የሚሰሩት ለኛ ሳይሆን ለሻዕቢያ ነው።
3ኛ – ሻዕቢያ ለዚህ ጦርነት ከአመታት በፊት መዘጋጀቱን የሚያመለክተው፤ ከሁለት አመት በፊት በኃየሎም ላይ የወሰዱት እርምጃ ነው። አሁንም በህግ ሽፋን በገዳዩ ላይ እርምጃ ሳይወሰድ አዲስ አበባ ውስጥ እንዲቀመጥ የተደረገው ለምንድነው?
4ኛ – ሌላው ቀርቶ እራሱ መለስ ዜናዊ እኛን ማመን ትቶ አጃቢዎቹ ጭምር ኤርትራዊያን ናቸው… የሚሉት ይገኙበታል።
በወቅቱ በደረሰን የውስጥ መረጃ መሰረት… የዚያኑ ቀን የመለስ ዜናዊ ኤርትራዊ አጃቢዎች መሳሪያቸውን አስረክበው፤ ህወሃት ባዘጋጃቸው አዲስ የታጠቁ አጃቢዎች ተተኩ – እስከመጨረሻው።
ከዚህም በተጨማሪ የሎጂስቲክና የጦር ስትራቴጂ በማውጣት በኩል ስዬ አብርሃ ወደ ሰራዊቱ ተመልሶ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደረገ። ከዚህ ስብሰባ በኋላ በመለስ ዜናዊ እውቅና በሰራዊቱ ውስጥ የነበሩት ኤርትራዊ ሻምበልና ሻለቃዎች በሙሉ ተመልምለው እንዲወጡ መመሪያ ተሰጠ። ከዚያም በታጠቅ ጦር ሰፈር ውስጥ ታሰሩ።
አንድ በአንድ የህወሃት አመራሮች የጠየቋቸው መሰረታዊ ጥያቄዎች እየተመለሱ የመጡ መሰሉ። መለስም በአደባባይ ይደግፋቸው የነበሩትን የሻዕቢያ መሪዎች መወረፍ ጀመረ። “እኔ ይሳሳታሉ እንጂ፤ ያብዳሉ ብዬ አላሰብኩም ነበር።” አለ።
መለስ ዜናዊ ከትግራይ መልስ በኃየሎ ገዳይ ላይ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወሰድ ከማድረግ ውጪ በኤርትራዊያን ላይ አፋጣኝ እርምጃ አልወሰደም ነበር። በነክንፈ ገብረመድህን በኩል ለሻዕቢያ ገንዘብ ያዋጡ ሰዎች ከተያዙ በኋላ፤ ኤርትራዊያንን የማሰርና የማባረሩ ነገር ተፋጠነ። ከገንዘብ ሰብሳቢዎቹ ቀጥሎ ሳዋ ገብተው ስልጠና የወሰዱ ኤርትራዊያን ታሰሩ። ከነሱ ቀጥሎ ደግሞ ኤርትራ ስትገነጠል ድምፅ የሰጡ ሰዎች ተለቀሙ። በጥፋተኝነት ተገምግሞ የነበረው መለስ ዜናዊ፤ “የአይናቸው ቀለም ካላማረን እናባርራቸዋለን” አለ። ሆኖም በኣዲ ቛላ፣ ኤርትራ ውስጥ ተወልደው ያደጉት የመለስ ዜናዊ እናት ወ/ሮ አለማሽ ገብረልዑል፤ በምኒልክ ቤተ መንግስት ውስጥ ሲደበቁ፤ ሌሎች ኤርትራዊያን ግን “የአይናቸው ቀለም አላማረንም” ተብለው ተባረሩ። ከነዚህ ተባራሪዎችም መካከል አድዋ ውስጥ የነመለስ ዜናዊ ጎረቤት የነበሩት ሴትዮ፤ “እኔ ለኤርትራ ድምፅ የሰጠሁት ከአለማሽ ጋር አብረን ሄደን ነው። እሷ ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖረች እኔ መባረር የለብኝም።” ብለው እያለቀሱ ቢለምኑም የአይናቸው ቀለም አላማረምና እያለቀሱ የአድዋ ከተማን ተሰናበቱ።
በአንዳንድ ቦታዎች ህወሃት በኤርትራዊያን ላይ የሚወስደው የግፍ እርምጃ ደስ የሚል አልነበረም። በተለይም በፍቅራቸው ጊዜ አብረው ንግድ የከፈቱ የትግራይና ኤርትራዊ ሽርካዎች የተጣሉበት፤ ኤርትራዊያኑ ሲባረሩ ሌለኞቹ ሃብታቸውን የወረሱበት አጋጣሚ ተከስቷል። በዚያኑ መጠን ደግሞ ሌላው ኢትዮጵያዊ የኤርትራዊያኑን ንብረት በውክልና ተረክቦ በጨዋነት የጠበቀበት አጋጣሚም ተስተውሏል። አብዛኛዎቹ ኤርትራዊያን ሲባረሩ ከጦርነት ነጻ በነበረው በጎንደር በኩል ሲሆን፤ ብዙዎቹ በረሃብ እና ውሃ ጥም ተሰቃይተው ነበር። እናም ኢትዮጵያዊው ውሃ አጠጥቶና ስንቅ ሰጥቶ፤ የተጎዱትን አክሞ ነበር የመረብን ወንዝ ያሻገራቸው። (ይህንን ወደፊት ሌላ ታሪክ ፀሃፊ የሚያወሳው ይሆን ይሆናል)
ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ እያንዳንዷ ቀን በድርጊት የተሞላ ነበረች። ወሬ እንደንፋስ በፍጥነት የሚዳረስበት፤ ሃዘንም ሆነ ደስታ ተደበላልቀው የሚሰሙበት ወቅት ነበር – ግንቦት 1990 ዓ.ም.። በዚህ ድብልቅልቅ መሃል የጀሚል ቤተሰቦች ሌላ ጭንቀት ውስጥ መግባታቸውን ሰማሁ። አንዳንዶቹ የቤተሰብ አባላት ከኢትዮጵያ መባረር ጀምረዋል። አንድ ቀን ቢሮዬ ስልክ ተደወለ። የጀሚል ያሲን ትንሽ እህቱ ነበረች። “ቤታችን ውስጥ ያለውን ንብረት እያወጡት ነው” አለችኝ።
የጀሚል ቤተሰቦች ቤቱን ለቀው ከወጡ በኋላ ግቢው በወታደሮች ሲጠበቅ ነበር። ከዚህ ቀደም ንብረታቸው እንዲመለስ ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቅርበው አጥጋቢ ምላሽ አላገኙም። አሁን የህወሃት ሰዎች አጋጣሚውን ይጠቀሙበት ጀመር።
“ምንድነው የሚወስዱት?” አልኳት።
“ቲቪውን፣ ሶፋውን…” ተናግራ ሳትጨርስ ማልቀስ ጀመረች።
በሚቀጥለው የጋዜጣዬ እትም ላይ ይህንኑ ከመግለጽ ውጪ፤ ምንም ማድረግ እንደማልችል አውቃለሁ። በሳምንቱ በጀሚል ያሲን መኖሪያ ቤት ውስጥ የተደረገውን ብዝበዛ ጽፈን ለህትመት አበቃነው። ኢህአዴጎቹ ዝም አሉ። ምላሽ አልሰጡበትም ምክንያቱም ከዚያ በላይ ሌላ ጉዳይ ነበራቸው። የጀሚል ያሲን ንብረት መወሰድ ወይም መወረስ ለነሱ ትርጉም አልነበረውም።
ይህ ሁሉ ጣጣ በኤርትራዊያን ላይ ሲወርድ፤ በኃየሎም ገዳይ ላይ ምንም አይነት እርምጃ አለመወሰዱ ብዙዎችን ማነጋገሩ አልቀረም። ሰራዊቱ በውስጡ የነበሩት ግማሽ ኤርትራዊ የጦር መኮንኖች ሲወገዱ፤ በምትካቸው የህወሃት ሰዎች ተተኩ። መለስ ዜናዊ በሰራዊቱ ውስጥ ተቀባይነትን ለማግኘት አዳዲስ ሹመት ሲሰጥ፤ ለሳሞራ የኑስ የብርጋዲየር ጄነራልነት ማዕረግ ሰጠ። በ’ርግጥም ሳሞራ የኑስ በትግራዩ የዝግ ስብሰባ ወቅት ፊታችንን ወደጠላት ማዞር አለብን ብሎ ነገሩን ባያረግበው ኖሮ፤ የመለስ ዜናዊ ጉዳይ ቀደም ብሎ ያበቃለት ነበር። ለዚያም ውለታ ይመስላል… ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አሁን ድረስ ሳሞራ የኑስ የጦሩ የበላይ ሆኖ የተሾመው። (በአሁኑም ወቅት ብቸኛው ባለሙሉ ጄነራል ነው።)
እነኃየሎም ሞተው… እነጻድቃን ገብረትንሳይ ተረስተው፤ ሳሞራ የኑስ እየገነነ በመጣበት ወቅት አንድ ታሪካዊ ሊባል የሚገባው ቀስቃሽ ካሴት በትግሪኛ ታትሞ… በትግራይ ከተሞች ውስጥ ተሰራጨ። ካሴቱ ከህዝቡ አልፎ በሰራዊቱና በጦር አዛዦች ዘንድ ሲሰማ፤ በተለይ ያኔ ብርጋዲየር ጄነራል ተብሎ የተሾመውን ሳሞራ የኑስን በነገር የሚሸነቁጥ ሆኖ ተገኘ።
“ሳሞራ ሕኪ ቁሪ አትዩካ
ጄኔራል ተባሂልካ ክምቀካ?” ተባለ።
በወያኔ ትግል ወቅት ሳሞራ የኑስ በተቃራኒ በቆመው የኢትዮጵያ ሰራዊት ውስጥ ድንገት ሰርጎ በመግባት፤ ጦርነት በማስነሳት ይታወቅ ነበር። አንዳንዴ በለስ ቀንቶት ጦርነቱን ሲያሸንፍ በሌላ ጊዜ ደግሞ በጦር ተከቦ መውጫ ሲያጣ… ሁልጊዜ ወያኔዎች እንዲደርሱለት ሬዲዮ በማድረግ ይታወቅ ነበር። ሁልጊዜም ታዲያ ደጀን ሆኖ እየደረሰ የሚያድነው ኃየሎም አርአያ ነበር። ይህንን የሚያውቁ ሰዎች ኃየሎም ለሳሞራ “ሓክፈኑ” ላይ የዋለለትን የነፍስ ውለታ በማስታወስ፣ ያለእሱ የጄኔራልነት ወንበር እንዴት ይሞቅሃል? ኃየሎም ልብስህ ነበር። አሁንም የኃየሎም ሞት ካልተጣራ ነገ ያንተ ተራ ነው፣ የሚለው ረዥም ግጥም ሲሰማ ቀስቃሽም አስለቃሽም ነበር።
“ሳሞራ! ሕኪ ቁሪ አትዩካ
ጄኔራል ተባሂልካ ክምቀካ?
ኃየሎሜዩ ነይሩ ክዳንካ
ሃቄድዩ ብዘይንሱ ወንበር ክምቀካ?
ፀላ ጋሊሁ ካብ ሞት ከውፅአካ
ድሮ ነዚ ረሲዕዛ ንኃየሎም
ዋርዲያ ስኢንካ?
ናይ ኃየሎም ሞት ተፃሪያ
እንተዘይ ተመርሚራ
ፅባህ ናባኻ እያ ብተሩ።” ተብሏል።
በዚህ አይነት የነገር እሳት ተቀጣጠለ። ጀሚል ያሲን በህይወት የሚቆይባት እያንዳንዷ ቀን የህወሃት ባለስልጣናትን ሰላም የምትነሳ ሆነች። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች ባድመ ላይ እየሞቱና እየተዋደቁ ባሉበት ወቅት ሳይቀር፤ የጦሩን ህሊና ሰቅዞ የያዘው የኃየሎም ገዳይ ጉዳይ ሆነ። ብዙ ሺህ ኤርትራዊያን ከኢትዮጵያ ተባረውም ቢሆን፤ በብዙዎቹ የህወሃት አባላት ዘንድ እርካታ አልነበረም። የኃየሎም ገዳይ ሳይገደል፤ ድሉም ሆነ ገድሉ ባዶ ሆኖ ተሰማቸው። በመሆኑም በነመለስ ዜናዊ ላይ ሊኖር የሚችለውን ጥርጣሬ ጭምር ሊያፀዳ የሚችለው የጀሚል ያሲን ደም በመሆኑ… ከምንም ነገር የበላይ የሆነው ፍትህ መረገጡ ለመለስ የህወሃት ቡድን ምንም ማለት አልነበረም።
በመሆኑም “ኃየሎም አርአያ በሻዕቢያ ሰዎች ተገደለ” እየተባለ በውጭ የሚወራው ወሬ ለህወሃት የግፍ በትር ጥሩ ሽፋን ሆነለት። ጀሚል ያሲን ምንም በድርጊቱ ቢፀፀትም፣ ምህረትም ሆነ ፍትህ የማግኘት እድሉ እየመነመነ መጣ። ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘበት ጊዜ አንስቶ ከህግ ውጪ በርካታ ዜጎች ህይወታቸው አጥፍቷል። ሆኖም በህግ ሽፋን ፍርድ ቤት ሞት አስፈርዶ ስለማያውቅ ሊሆን ይችላል… የአገዳደሉ ሂደት ግራ ያጋባው ይመስላል።
ከዚህ በኋላ ስለፍርድ ቤቱ ሂደት አናወራም። ነገር ግን ጀሚል ያሲን ከመገደሉ በፊት ሞቱን ያላፋጠኑትን አንዳንድ ምክንያቶች ልግለፅ። አንደኛው ጀሚል ያሲን በግልጽ ኤርትራዊ ነው ከተባለ፤ በሌላ አገር ዜጋ ላይ የሞት ፍርድ መሰጠቱን ልብ እንበል። ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ ሞት የተፈረደበት ሰው “ይግባኝ” የማለት መብቱ የተጠበቀ በመሆኑ፤ ጀሚል ያሲን ይግባኝ በመጠየቅ ጊዜ እንዲባክን አልተፈለገም። ሶስተኛው ነጥብ ደግሞ በህጉ መሰረት የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር የጀሚል ያሲንን ሞት በፊርማ ማፅደቅ ይኖርባቸዋል። ነገር ግን ለይስሙላ ካልሆነ በስተቀር ለሶስቱም ጉዳዮች ስፍራ አልሰጣቸውም። ስለሆነም በግንቦት ሃያ ማግስት የሞቱ ድግስ በዚያው የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት እንዲፈጸም ተደረገ።
7ኛውን የግንቦት 20 በዓል መለስ ዜናዊ ትግራይ ሄዶ ነበር ያከበረው። ሃሙስ ቀን ነው… በዓሉን አክብረው ጨረሱ። አርብ እለት ለህወሃት አመራሮች ጥያቄያቸው ተፈጻሚ እንደሚሆን የመጨረሻ ቃል ተገባላቸው… ምንም ይሁን ምን የጀሚል ያሲን ጉዳይ ያበቃለት ነገር መሆኑ ታወቀ።
ቅዳሜና እሁድ ስራ የለም። እሁድ ‘ለት ከርቸሌና ቤተ ክርስቲያን ይጣበባል። የቤተ ክርስቲያ ደጀ ሰላም በፀሎት… የከርቸሌ ደጃፍ በኤሎሄ ይናወጣል። ስለዚህ የጀሚል መሞቻ ቀን ለሚቀጥለው ሳምንት፤ በሳምንቱም መጀመሪያ ላይ እንዲሆን ተወሰነ። ግንቦት ሃያን የሸኘው እሁድ ሰኞን አስከተለ። እነሆ የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤትም በአስፈሪ የጭንቅ ድባብ ውስጥ ሰጠመ።
የማረሚያ ቤቱ አስተዳዳሪ አብርሃም ወልደአረጋይ ቅዳሜና እሁድ የግቢው ጥበቃ እንዲጠናከር አደረገ። ግንቦት 24 ቀን፣ 1990 ዓ.ም. ሰኞ እለት በጠዋት ወደ ከርቸሌ መጥቶ የማረሚያ ቤቱን የኢንዱስትሩ ግምጃ ቤት ቁልፍ ተረከበ። ከዚያም ጥቂት የህወሃት ታጋዮችን አስከትሎ ወደ እንጨት መጋዘኑ አመራ። በእንጨት መጋዘኑ ውስጥ ሰውን ለመስቀል የሚያስችል ግንዲላዎች መኖራቸውን አረጋገጠ።
ሰው ለመስቀል የሚያስችሉት ግንዲላዎች ተመርጠው፤ ሰኞ እለት እዚያው መጋዘኑ ውስጥ የመሰቀያ ባላዎች ተዘጋጁ። ከምሽቱ 3፡00 ሲሆን፤ የእስር ቤቱ አስተዳዳሪ አብርሃም ወልደአረጋይ ወደ መሰቀያው ስፍራ በመሄድ የመሰቀያውን ገመድ አዘጋጅቶ፤ ነገ ጠዋት ግንቦት 25 ቀን ስቅላቱ እንደሚፈጸም ለጥቂት ሰዎች ተናግሮ… ዝግጅቱ ተጠናቀቀ። የዚያን ቀን ለሊት አስተዳዳሪው ወደ ቤታቸው አልሄዱም። እዚያው ከርቸሌ በሚገኘው ቢሯቸው ውስጥ አደሩ።
ይህ ሁሉ ሲሆን በወህኒ ቤቱ ያለወትሮ ጥበቃው መጠናከርና የተለየ ትዕዛዝ መተላለፍ የተደናገሩት ፖሊሶች የራሳቸው የራሳቸውን ግምት እየሰጡ ይወያያሉ። አንዳንዱ ፖሊስ “ እስረኛ ጠፍቶ ይሆን?” ሲል ሌሎች ደግሞ “ምርኰኛ ሊያስገቡ ይሆን?” በማለት የራሳቸውን መላምት ይሰጣሉ። ምን ለማድረግ እንደተዘጋጁ የሚያውቁት ግን ከህወሃት የበላይ አካል ት ዕዛዝ የመጣላቸው አስተዳዳሪና ጥቂት የታጠቁ የህወሃት ታጋዮች ነበሩ።
ግንቦት 25 ቀን 1990 ዓ.ም እስረኞች ለቁርስ ወጥተውና ሽንት ቤት ተጠቅመው ባስቸኳይ ወደ እስር ቤታቸው ውስጥ እንዲገቡ ተደረገ። ማንም ሰው በእስር ቤቱ ውስጥ ምንም አይነት እንቅስቃሴ እንዳያደርግ ታገደ። እስረኛው በሙሉ ከቁርስ መልስ ወደ እስር ቤቱ ተመልሶ ሲገባ፤ ግቢው ጭር አለ። ከዚያም በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ በአራት ሰዓት ላይ ጀሚል ያሲን ከታሰረበት ክፍል ውስጥ ተወሰደ። እጆቹ ታስረዋል። አይኑ በጥቁር ጨርቅ ታስሯል። ወዴት እንደሚሄድ እና ለምን እንደሚወሰድ አያውቅም። ነገር ግን በጥቂት ወታደሮች ታጅቦ ወደ እንጨት መጋዘኑ ተወሰደ። ከዚያም አስተዳዳሪው አብርሃም ወልደአረጋይና አብረዋቸው የነበሩት የህወሃት ታጋይ ወታደሮች ባሉበት ስቅላቱ ተፈጻሚ ሆነ። የኃየሎም ገዳይ ጀሚል ያሲን በዚህ አይነት ተገደለ። የተኩስ ድምፅም ተሰማ። ምናልባት ደስታቸውን መግለጫ ወደ ሰማይ የተኮሱት ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ይዘን …ከዚያ ቀጥሎ የሆነውን ነገር አብረን እንመልከት።
የጀሚል ያሲን ስቅላት ከተፈጸመ ከአንድ ሰዓት በኋላ የኃይሎም አርአያ ቤተሰቦች ባለቤታቸው ወ/ሮ አልጋነሽ መለሠ እና ሁለቱ ልጆቻቸው በነጭ ዲ.ኤክስ መኪና መጥተው የጀሚል ያሲንን አስክሬን ተመለከቱ። ከዚያም ብዙ ሳይቆዩ ወጥተው ሄዱ።
የማረሚያ ቤቱ ማዕከላዊ ቢሮ አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም ወ/አረጋይ የግድያ ተልዕኳቸውን ጨረሱ። ከዚያም የጀሚል ያሲን አስከሬን ክተሰቀለበት ወርዶ፣ ከመጋዘኑ ውጭ ሜዳ ላይ እንዲጣል ካደረጉ በኋላ፤ የግምጃ ቤቱን ቁልፍ አስረክበው በ5፡30 ላይ በሌላ ነጭ ዲ.ኤክስ መኪና ግቢውን ለቀው ወጡ።
በዚህ ሁኔታ የጀሚል አስክሬን ሜዳ ላይ ተዘርግቶ እንዳለ የወህኒ ቤቱ ፖሊሶች ሟችን ተጠግተው ለማየትና ጀሚል ያሲን መሆኑን ለማወቅ ቻሉ።
ከሰዓት በኋላ ታግዶ የነበረው የበር ዘብ ትዕዛዝ ተነስቶ መውጣትና መግባት ሲፈቀድና የእስረኛ ቤተሰብም ስንቅ እንዲያስገባ ተደረገ። በመሃከሉ በግምት የ14 ዓመት ሴት ልጅ የጀሚል ያሲንን ስንቅ ይዛ ቀረበች። ተራዋ ደርሶ ስንቁን ስታስፈትሽ “የጀሚል ያሲን እህት ነሽ?” አላት ፈታሹ።
«አዎ» ስትል የህወሃት ታጋይ የሆነው ታጣቂ በኩራት መንፈስ እየተጀቦነ፤ “ነይ” አለና ወደ ግቢው እንድትገባ አደረጋት።
ከዚያም ከተሠቀለበት ወርዶ ከቤት ውጪ ሜዳ ላይ ተጥሎ ወደሚገኘው ወንድሟ አስክሬን ወሰዳት። ከዚያም አይኑ ታስሮበት የነበረበትንና አሁን ደግሞ ፊቱ ላይ ፊቱ ላይ ጣል የተደረገውን እራፊ ጨርቅ ገልጦ «ጀማል ማለት ይሄ ነው» ብሎ አሳያት።
የ14 አመቷ ልጅ የወንድሟን አስከሬን አይታ በድንጋጤ ደርቃ ቀረች። ማልቀስ ልትጀምር ስትል፤ እያመናጨቁ አስቆሟት። ከዚያም አንደኛው ታጋይ “አሁንን መሄድ ትችያለሽ” ብሎ ከግቢው ስትወጣ ለወንድሟ የያዘችውን ስንቅ እንደተሸከመች ነበር።
ግቢውን ለቅቃ ልትወጣ ስትል፤ “የሬሳ ሳጥን ይዛችሁ መጥታችሁ ዛሬውኑ እንድትወስዱት” ተባለች። ብርክ ይዟት በድንጋጤ ትዝለፈለፍ የነበረችው ልጅ «ቤተሰቦቼ በሙሉ ወደ ትውልድ ሃገራቸው ኤርትራ ሄደዋል፤ እኔም ያለሁት ከዘመድ ጋር ነው። ቤተሰቦቼ በጦርነቱ ምክንያት መምጣት አይችሉም» በማለት እያለቀሰች ተናገረች። ማንም አላዳመጣትም ታጋዮቹ ጥለዋት ወደ ግቢው ሲመለሱ፤ ፖሊሶቹ አባብለው ወደ ቤት እንድትሄድና ለትልቅ ሰው እንድትነግር አስረዷት።
ከሰዓት በኋላ ይህንን የሰሙት የጀሚል ዘመዶች ሰሌን እና የአስከሬን መሸከሚያ የብረት ወሳንሳ ይዘው የመጡ ቢሆንም፤ “የሬሳ ሳጥን እንጂ ሰሌን አምጡ አልተባላችሁም” ተብለው፤ ከአንድ ሰአት በኋላ የሬሳ ሳጥን ካመጡ በኋላ አስከሬኑን ከተጣለበት ሜዳ አንስተው፤ በሳጥን ውስጥ አድርገው ሲወጡ… ያልተዘጋጁበት በመሆኑ… የሬሳ ሳጥኑ ጠቦ፤ የሳጥኑ መክደኛም እንዲሁ ገርበብ ብሎ፤ አንድ እጁ ከሳጥኑ ውጪ ሆኖ ይዘውት ወጡ።
የጀሚል ያሲንን በዚህ ሁኔታ መገደል ስመለክት አዘንኩ። ሆኖም ከመገደሉ አንድ ሳምንት በፊት በጠበቃው በአቶ አህመድ በኩል የላከልኝ ረዥም የኑዛዜ ቃሉ አብሮኝ አለ። ከአስር ገጽ በላይ የሆነው የኑዛዜ ቃል ከኃየሎም ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ያትታል። በዚሁ ደብዳቤ ላይ ፍርድ ቤት ሲቀርብ ጥቁር ለብሰው ያያቸውን የኃየሎም አርአያ ሚስት የሆኑትን ወ/ሮ አልጋነሽ መለሰን እና ቤተሰባቸውን አንስቷል። “በተለይ ወ/ሮ አልጋነሽ ጥቁር ለብሰው ፍርድ ቤት ሳያቸው ልቤ በሃዘን ተሰብሯል።” በማለት የተሰማውን ከፍተኛ ሃዘን ለቤተሰቡ ገልጿል።
በመጀመሪያዎቹ ገጾች ላይ፤ በግል የተሰማውን ፀፀትና ሃዘን ለኃየሎም ቤተሰቦች ካቀረበ በኋላ… በቀጣዮቹ ገጾች ላይ ሲታሰር የደረሰበትን ስቃይ አልሸሸገም። በፍርድ ቤቱ የአድልዎ አሰራር ያዘነ መሆኑንም ገልሷል። በታሪኩ ውስጥ የተገለጸው 5ኛው ሰው ለመስቀለኛ ጥያቄ እንዲቀርብለት ጠይቆ መከልከሉን፤ ከዚያም ይኸው 5ኛው የአቃቤ ህግ ምስክር ከአገር በመውጣቱ ምክንያት ፍርድ ቤት ቀርቦ ቃሉን ያልሰጠ መሆኑን፤ በአጠቃላይ 5ማው ሰው በፖሊስ አስገዳጅነትም ሊሆን በሚችል መልኩ ለፖሊስ የሰጠው ቃል በኔ ላይ በአስረጅነት ሊቀርብ አይገባም… የሚሉና ሌሎችም ዝርዝሮች ያለበት ነው። ሆኖም ዛሬ የማቀርበው የኑዛዜውን ቃል ዋና ዋና ሃሳብ ብቻ ይሆናል። መጀመሪያ አካባቢ ካሉት ገጾች ልጀምር… እንዲህ ይላል።
” … የተወሰነብኝ የመጨረሻው የሞት ፍርድ እንደመሆኑ መጠን ፍርድ ቤቱ ፈጣሪ የፈጠረውን ሕይወት በህጉ መሰረት ሊጠፋ ይገባዋል ብሎ ለመወሰን ያበቃውን ሁኔታ ሁሉ የምጠብቀውም ሆነ የምዋሽበት ምክንያት ስለሌለኝ በኑዛዜ መልክ ቅሬታዬንና ትዝብቴን እንደሚከተለው አቀርባለሁ፣
” … ጠበቆች ስለእኔ የአዕምሮ ሁኔታ የተረዱትን ሁሉ በመዘርዘር የወ.መ.ሕግ ቁጥር 51 በሚፈቅደው መሰረት የአዕምሮ ጤንነት ምርመራ እንዲደረግልኝ ጠይቀው በማስረጃ ያልተደገፈ ጥያቄ ነው፣ አጠራጣሪ የሆነ ምልክት አላየንም በሚል ጥያቄውን ውድቅ አድርጐታል። ለጥርጥር ምልክት የሚለው ማስረጃዎች እንዲቀርቡ በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲተላለፍ ለቀረበውም አማራጭ ከሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤት ጋር ተነጋግራችሁ ራሳችሁ ፈፅሙ እንጂ ፍ/ቤቱ አያገባውም ተብሎ ታለፈ። በጠበቆችም ሆነ በዘመዶቼ በኩል ማስረጃው እንዲቀርብ ለማድረግ ተብሎ ውክልና ለመስጠት ቢሞከርም የማረሚያ ቤቶች አስተዳደር በጉዳዩ ስላላመነበት ውክልና ለመስጠት ባለመቻሉ ማስረጃ የማቅረብም ሆነ በሌሎች ክሶች ፍርድ ቤት ቀርቦ ለመከራከር መብት ተነፍጐኝ የጤንነት ምርመራውም ሳይከናወን ክርክሩ ተከናውኖ የሞት ፍርድ ተወሰነ። እንደ እኔ በዕለት ጠብ ምክንያት በተፈጠረ ግጭት በተፈፀመ ወንጀል ብቻ ሳይሆን ከባድ ወንጀሎች የተፈፀሙባቸው እጅግ በርካታ መዝገቦች በጅምር ላይ ወይም ገና ያልተነኩ መሆናቸው እየታወቀ የእኔ ጉዳይ በሳምንት በሳምንት ተቀጥሮ በጥድፊያ የሞት ፍርድ ውሳኔ ላይ መድረሱ እንደማንኛውም ዜጋ እኩል የፍትህ ዕድል በነፃ ዳኝነት አግኝቻለሁ ለማለት አልደፍርም።
” … በእርግጥ ሜጀር ጀኔራል ሃየሎም ሰራዊት የሚወዳቸውና የሚያከብራቸው ጀግና ሰው ነበሩ። እኝህን ጀግና ሰው ደጋግሜ እንደገለፅኩት ከጓደኞቻቸው ባለነሰ ሁኔታ የማከብራቸውና የማደንቃቸው ሰው ናቸው። ብቀላ እሳቸውን መልሶ የሚያመጣ ቢሆን እንኳን አንድ ጊዜ ሺህ ጊዜ ብሞትም አይቆጨሯም። እንኳን እኔ እሳቸውም ሞተዋል። የሚቆጨኝ የማዝነው ግን በነፃ ፍርድ ቤት ክርክር ተካሄዶ ባላሰብኩት ወቅት ባልጠበቅሁት ቦታ በተፈጠረ የዕለት ጠብ ምክንያት በስካር መንፈስና በደረሰብኝ ጥቃት ልቆጣጠረው በአልቻልኩት ስሜት ወንጀልን መፈፀሜ በግልጽ በማስረጃ የተረጋገጠውን ድርጊት እኝህን ክቡር ጀግና ሰው ለማጥፋት አስቤ ተዘጋጅቼ አድፍጨ በጭካኔና በአስነዋሪ ሁኔታ እንደገደልኩ ሁኖ ፍርድ ቤት በመተቸቱ ነው። የእኔ መገደል የአድናቂዎቻቸውን የብቀላ ስሜት ያረካዋል ከተባለም በፍትህ ሂደት ሳይሆን በሌላ መንገድ ግድያው ቢፈፀም ቅር አይለኝም ሞትንም አልፈራም። ፍትሕ ከተባለ ግን የሕጉ አባባል ከማስረጃው ጋር ተመዝኖ የሚወሰን ከሌሎች ተመሳሳይ መዝገቦች ጋር የሚመጥን ውሳኔ ለታሪክ ከትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ ጥቁር ነጥብ መሆን አይገባውም። እንዲህ አይነቱን ለፍትህ ለህብረተሰብ የቆመ ጀግና በእኔ እጅ በመጥፋቱ ፀፀቱና ቁጭቱ እስከ ዕለተ ሞቴ አይበርድልኝም። ለሰዎች ጥሩ እድል (ሎተሪ) እንደሚደርሳቸው ሁሉ ለእኔ ደግሞ ይህ መጥፎ ዕድል ደርሶኝ ይህን ጥፋት መፈፀሜ እንደፈጣሪ ቁጣ አድርጌ እወስደዋለሁ።
” … ብቀላ እርካታን አይሰጥም ቢሰጥም ለአጭር ጊዜ ነው። የማረሚያና የማስተማሪያ ቅጣት ግን የሕብረተሰብን ብስለትና ሥልጣኔ ደረጃ መለኪያ ከመሆኑም በላይ በጊዜያዊ ስሜትና ፍትሕን ተፃራሪ በሆነ መልኩ እርካታ ማግኘቱ የጀግናና የሃቀኛ ታጋዮችን አላማ ጥሻ ውስጥ መጣል ይሆናል። ለፍትሕና ለህብረተሰብ ዕድገት የታገሉ ጀግኖች በተለያየ ምክንያት ሕይወታቸው ቢያልፍም አላማቸው ያብባል ይደምቃል። በሜ/ጄ ሃየሎም ምክንያት ስሜታቸው የተነካ ሁሉ በእኔ መገደል ከመርካት ይልቅ እሳቸው የታገሉለት የፍትህና የሕግ ልዕልና የማስፈን አላማ ግብ ማድረሱ የበለጠ ያፅናናቸዋል ብዬ እገምታለሁ።”
በማለት ነበር የኑዛዜ ቃሉን የተወልን። ከላይ የገለጽኩትን ቃል ኢትዮጵያ ውስጥ በጋዜጣዬ ላይ ታትሞ የነበረ ነው።
የጀሚል ያሲንን መገደል ከሰማሁ በኋላ ለእህቱ ደወልኩ። ለቅሶ መምጣት የምፈልግ መሆኔን ገለጽኩላት። እያለቀሰች ምንም መደማመጥ አልቻልንም። ስለዚህ በሚቀጥለው ቀን ከሰዓት ላይ በቀጥታ ለቅሶ ወደተቀመጡበት መኖሪያ ቤታቸው ሄድኩ። ድንኳን አልተጣለም። ብዙ ግርግርም የለም።
ወደ ውስጥ ዘልቄ ስገባ ዘለግ ባለ የጩኸት ድምፅ ለቅሶ ሰማሁ። በትግሪኛ ነው የሚለቀሰው። አስተናጋጆቹ የሚያወሩት ትግሪኛ ነው። በቋንቋ አለመግባባታችንን ሳውቅ የጀሚልን እህት ስም ጠራሁላቸው። አሁን ተግባባን። ከዚያም እሷ ወደነበረችበት አንዲት ክፍል ወሰዱኝ። ሌሎች ወጣት ሴቶች እና ወንዶች በዚያች ክፍል ውስጥ በሃዛን ኩርምት ብለው ቁጭ ብለዋል። እኔም እነሱን ተቀላቀልኩ።
አገዳደሉንም ሆነ አሟሟቱን በጋዜጣዬ ላይ በተከታታይ እዘግብ ስለነበር፤ እዚያ ገብቼ ዝም ከማለት ውጪ… ምንም የምለው ነገር አልነበረኝም። በዚያ ላይ በሹክሹክታ ትግሪኛ እኔን እያሳዩ ሲያወሩ አየሁ። ስለ እኔ ምን ሊባባሉ እንደሚችሉ አላውቅም። ነገር ግን ደስ የማይል ስሜት ተሰማኝ። መገኘት በሌለብኝ ቦታ ላይ የተገኘሁ መሰለኝ። ሃዘኔም ደረቅ ሃዘን ሆነ። ባይተዋርነት ተሰማኝ… የሚዘገን ንፍሮም ሆነ የሚታደል ውሃ በጣቴ አልነካሁም።
በዚህ አይነት ደስ የማይል ስሜት ውስጥ… ለምን ያህል ጊዜ እንደቆየሁ አላስታውስም። ‘ሰላይ መስያቸው ይሆን?’ አልኩ ለራሴው። ጋዜጠኛ መሆኔም ደስ አላላቸው ይሆናል። ነገር ግን አሁን የመጣሁት ሃዘኑን ለመዘገብ ሳይሆን ሃዘን ለመድረስ ነው። ‘ለምን መጣሁ?’ የሚል ጥያቄ ህሊናዬን በጥፊ እያዳፋው ተሰቃየሁ። በመጨረሻ ግን ለመሄድ ተነሳሁ።
እንደባህላችን ከተቀመጥኩበት ብድግ ብዬ ፊቴን ወደ ሃዘነተኞቹ አዞርኩና… “አላህ ነፍሱን ይማር። እናንተንም እግዚአብሄር ያፅናችሁ” ብዬ እጅ ነሳሁና ወጣሁ። ከለቅሶው ቤት ስወጣ ዛሬም ድረስ ስቅጥጥ የሚለኝን የሃፍረት ስሜት ይዤ ወጣሁ። ለራሴው መላልሼ፤ “መምጣት አልነበረብኝም” እላለሁ። ወደኔ እያዩ በትግርኛ የተንሾካሾኩትን ሳስበው፤ “ምን ብለውኝ ይሆን?” ብዬ ከራሴ ጋር ሙግት መግጠሜ አልቀረም። ዛሬም ድረስ ታዲያ… “እነዚህ ሰዎች ካሳለፉት ጭንቀት አንጻር ቢጠራጠሩኝ አልፈርድባቸውም” እላለሁ።
ብቻ ግን… ‘ማድረግ ያለብኝን እንደጋዜጠኛ ዘግቤያለሁ። እንደሰው ለሰው ልጅ አዝኛለሁ። እንደአንድ ኢትዮጵያዊ በአገሬ ላይ ፍትህ አለመኖሩን አይቼ… ‘ፍትህ ይከበር’ ብዬ ለእውነት ቆሜያለሁ። ከዚህ በላይ ምንም መሆን አልችልም።’ እያልኩና ከሃሳቤ ጋር እየተጣላሁ፤ ከለቅሶ ቤት ወጥቼ ጥቂት ደቂቃዎች እንደተጓዝኩ፤ ከኋላዬ “ዳዊት” የሚል ድምፅ ሰማሁ። ዞር ስል፤ ለቅሶ ቤት ሲያስተግዱ ከነበሩት ወጣቶች አንዱ ነው።
ዞር ብዬ እስኪደርስብኝ ጠበኩት። አሯሯጡ መልዕክት ሊነግረኝ ይመስል ነበር። ግን አልነበረም… በጣም እንደሚያውቀኝ ሆኖ ቀረበኝ። በአማርኛ እያወራኝ ወደ ታክሲ መጠበቂያው አብሮኝ ሲሄድ “ጋዜጠኛ መሆንህን ነግራኛለች።” አለና ወሬ ጀመረ።
“ላስተናግድህ ስመጣ እኮ ሄደሃል አሉኝ” አለ።
“አዎ ለአጭር ጊዜ፤ የሃዘናችሁ ተካፋይ ለመሆን ነበር የመጣሁት” አልኩት።
ዝም ብዬ ወደ ታክሲው ተራ መሄዴን ቀጠልኩ። ከዚያ እሱ ወሬውን ቀጠለ…
“አዎ አየህ…” ብሎ ጀመረልኝና ራሱ ወሬውን ቀጠለ። “ጀሚልን በጣም የሚወደው ልጅ እዚሁ ጎረቤት አለ። እሱ ራሱ ታሞ ሊሞት እየተጠበቀ ነው። እና ዛሬ ጠዋት እንደምንም በርትቶ መናገር ሲጀምር መጀመሪያ የጠየቀው ጀሚልን ነው። ‘ጀሚል ደህና ነው ወይ?’ ብሎ ሲጠይቅ፤ ቤተሰቡ እንባ እየተናነቀው ‘አዎ ደህና ነው’ ብለው መለሱለት።” ወሬውን ቀጠለ። “አየህ ይህ የጀሚል ጓደኛና ዘመድ የጀሚልን መገደል አልሰማም። ሰውም ጮክ ብሎ እንዳያለቅስ ተብሎ፤ ሁሉንም በሆዳችን ይዘን እያለቀስን ነው” አለኝ።
ታክሲ መቆሚያው ላይ ወደ ፒያሳ የሚሄዱ ታክሲዎች ይጣራሉ። የኔም መንገድ ወደዚያው ነው። ከመሰናበቴ በፊት ግን በፈቃደኝነት የሚሸኘኝ ልጅ እንዲህ አለ። “ለምን ግን ሁለት ጊዜ ይገድሉታል?” ሲለኝ… አባባሉ ጠንከር አለብኝና… “ምን ማለትህ ነው?” አልኩት። “ከርቸሌ ውስጥ በስቅላት የገደሉት መሆኑን ነው የነገሩን። ነገር ግን አስከሬኑን ያመጡት ሰዎች እንደነገሩን ከሆነ፤ ግንባሩ ላይ በጥይት ተመትቷል።” አለኝ። እሱ ይሄን እየነገረኝ እኔ የማስበው ከኃየሎም ስቅላት በኋላ ተሰምቷል ስለተባለው የተኩስ ድምፅ ነበር። ሆኖም ከለቅሶ ቤት ስወጣ ጀምሮ ስሜቴ ስለተነካ ነው መሰለኝ ምንም አልመለስኩለትም።
ሸኚዬ ይሄን እየነገረኝ፤ እኔም ተጨማሪ ጥያቄ ሳልጠይቀው ተሰናብቼው፤ “ፒያሳ! ፒያሳ!” የሚለው ታክሲ ውስጥ ገባሁ። ከዚያም የግንቦት ወር መገባደጃ በመሆኑ፤ የሰኔ ወር የመጀመሪያ ሳምንት ህትመቴ ላይ የማወጣቸውን ቁምነገሮች እያሰብኩ ፒያሳ ወደሚገኘው ቢሮዬ አመራሁ። በሚቀጥለውም እትም የጀሚል ያሲንን አገዳደልና የኑዛዜ ቃሉን ይዤ ወጣሁ። የለቅሶ ቤቱንም ሆነ፤ ከለቅሶ ቤት ስወጣ የሰማሁትን “የሁለት ጊዜ ግድያ” ለህትመት ሳላበቃው ቀረሁ። በወቅቱ የነገረኝን ግን ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ አጋጣሚ ተነፈስኩት።
በወቅቱ ኢትዮጵያ እያለሁ በርዕሰ አንቀጼ ላይ ብዬዋለሁ። “ከጀሚል ያሲን ሞት በስተጀርባ… ፍትህም ተገድሏል!” አሁንም እደግመዋለሁ። ፍትህ በኢትዮጵያ ውስጥ መሞት ከጀመረ ቆይቷል። ፍትህን እየገደሉ ያሉት ደግሞ ነገሮችን ከፖለቲካ ጥቅም አንጻር በማየት የሚፈርዱት ናቸው። ሁሉም ዳኞችና የህግ ሰዎች ግን እንደጥቂቶቹ አይደሉም። ለ’ነዚህ… ለእውነት ለቆሙና ለሚመሰክሩ …ለፍትህ ልዕልና እራሳቸውን አሳልፈው ለሰጡት ሁሉ… ክብር ለነሱ ይሁን። አበቃሁ።
ከጊዜ በኋላ የሆኑ ነገሮች…
-ይህንን ታሪክ መጻፍ ከጀመርኩ በኋላ የጀሚል ያሲንን ቤተሰብ የሚያውቁ ሰዎች በርግጠኝነት እንደነገሩኝ ከሆነ፤ ቤተሰቡ በሙሉ የኤርትራ ሳይሆን የሽሬ፣ ትግራይ ተወላጆች ናቸው። ነገር ግን አስመራ ውስጥ ስለኖሩ… ጀሚልም ቢሆን አስመራ ስላደገ “ኤርትራዊ” ተባለ እንጂ የትውልድ ዘር ሃረጉ ሽሬ፣ ትግራይ ውስጥ መሆኑን ነግረውኛል።
-የድንበር ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በሁለቱ አገሮች መካከል የድንበር ግጭት መኖሩን የዘገበው፤ የማዕበል ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የነበረው አበራ ወጊ… የተፋፋመ ጦርነት ያደርጉ በነበረበት ወቅት ጭምር እሱ በዚያው ክስ እስር ቤት ውስጥ ነበር።
-ከጦርነቱ በፊት ኢሳያስ አፈወርቂን በ እባብ መስሎ ካርቱን ያወጣው እስክንድር ነጋም፤ “የክቡር ኢሳያስን ስም አጥፍተሃል” ተብሎ ተከሶ ነበር። በኋላ ጦርነቱ ሲፋፋም ክሱ ውድቅ ተደረገ።
-ብዙ የነጻው ፕሬስ ጋዜጦችን በመከሰስ የሚታወቀው አቃቤ ህግ መስፍን ግርማ… በጀሚል ያሲን ላይ ሞት እንዲፈረድበት ባደረገ በሁለት አመቱ በድንገተኛ አደጋ ህይወቱ አለፈ። በብዕሬም ሆነ በአንደበቴ ክፉ አልናገርም… እንደሥራው እግዚአብሄር ነፍሱን ይማረው።
-ከኢትዮጵያ ኤርትራ ጦርነት በፊት ሆርን ኦፍ አፍሪካ የሚባል የኢንሹራንስ እና ባንክ አክሲዮን ድርጅት ሊቋቋም ህጋዊ ፈቃድ ተሰጥቶት ነበር። ህጉን ያረቀቁት የጀሚል ያሲን ጠበቃ አቶ አህመድ ነበሩ… ጀሚል ከተገደለና ጦርነቱ ከተፋፋመ በኋላ አንድ ቀን “Horn of Africa” የሚባል የ ኤርትራዊያን ድርጅት ፈቃዱን መነጠቁንና መስራቾቹ መታሰራቸውን በመንግስት የዜና ማሰራጫ ሰማሁ። የጀሚል ጠበቃም በዚያው አጋጣሚ ተይዘው ሳይባረሩ እንዳልቀሩ እገምታለሁ።
በግንቦት ወር በህወሃት ውስጥ ተደርጎ በነበረው ዝግ ስብሰባ ወቅት የመለስ ተቃዋሚ የነበሩት፤ ገብሩ አስራት፣ ስዬ አብርሃ ወ/ሮ አረጋሽና ሌሎችም ነበሩ። በዝግ ስብሰባው ወቅት “አሁን የጋራ ጠላታችን የሆነውን ሻዕቢያን እንዋጋ። የድርጅቱን ጉዳይ በኋላ እንመለስበታለን።” ብለው ነበር የተለያዩት። በዝግ ስብሰባው ወቅት ሙሉ ለሙሉ ተሸንፎ የነበረው መለስ ዜናዊ በኋላ ላይ የራሱን ሰዎች አደራጅቶ ዳግም ስብሰባ ሲደረግ እነዚህ ተቃዋሚዎቹን በተራው …ድምፅ ብልጫ አሰጥቶ አገለላቸው።
-ከጦርነቱ በፊት… የኢህዴን ህብረ-ብሔር ድርጅት ወደ ብሄር ድርጅትነት ወርዶ፤ ራሱን ብአዴን ብሎ የአማራ ድርጅት ሆነ።
-ከጦርነቱ በፊት… አስመራ ተወስደው የነበሩ በርካታዎቹ የጦር አውሮፕላኖች ወደ ደብረዘይት ተመለሱ። የኢትዮጵያ የጦር መርከቦች በጂቡቲ ወደብ ላይ ሳሉ ጨረታ ወጥቶባቸው የመን ጨረታውን አሸነፈች። ኤርትራ ግን ለኔ ይገባኛል ስትል ተቃወመች… (መከላከያ ሚንስትር ከነበረው ታምራት ላይኔ ጋር የነበረው ውዝግብ ሰፊ ታሪክ ያለው ነው)
-“ከባድመ መልስ ወደ መለስ” ብሎ የዘመተው 21ኛው ሜካናይዝድ ብርጌድ… የመጀመሪያ ፊታውራሪ ሆኖ ሙሉ ለሙሉ እንዲደመሰስ ተደረገ። (ክብር ለሰማዕታት ይሁን)
-የመለስ ዜናዊ እናት ወ/ሮ አለማሽ ገብረልዑል በህወሃት መከፋፈል ሰሞን ሞቱ። መለስ ለቀብራቸው ትግራይ ሄደ። በእናቱ የቀብር ስነ ስርዓት ላይ ተገኘ። ሆኖም ለኃየሎም ያለቀሰውን ያህል እንባ አላወረደም። ምናልባት በወቅቱ የነበረው የእናት ድርጅቱ ህወሃት መሰንጠቅ ከእናት ሞት በላይ ሆኖ አስለቅሶት ሊሆን ይችላል።
– ሌላ ምን ቀረኝ? ከጦርነቱ ሁለት አመታት በኋላ ፊያሜታ ጋዜጣዬ ስራዋን እንድታቆም ተገደደች። እዚህ ላይ የጻፍኳቸውን ነገሮች በነዚያ ጋዜጦች ላይ ታገኙዋላችሁ። ወደፊት በህግ ጉዳይ ወረቀታቸውን ለሚሰሩ ተማሪዎች ወይም ተመራማሪዎች ሙሉውን የፍርድ ቤት ውሳኔ ከፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መዝገብ ቤት ሊያገኙ እንደሚችሉ በማስታወስ አስጀምሮ ያስጨረሰኝን አምላክ በማመስገን እሰናበታለሁ