የወያኔ አገዛዝ በአገሪቱ ላመጣው የኤሌክትሪክ ሃይል ቀውስ ህዝቡን ለማስከፈል እየተሰናዳ መሆኑ ታወቀ
ለረዥም ጊዜ በአገሪቱ የተለያዩ ከተሞች ሲከሰት የነበረውን የኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ ለማመን የተገደደው የወያኔ አገዛዝ ችግሩን ለመቅረፍ በየአመቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር እንደሚያስፈልገው እና ለዚህም ህዝቡን ለማስከፈል በስንድት ላይ እንዳለ ፍንጭ መስጠቱ ታውቋል።
ከሳምንት በፊት ለሪፖርተር ጋዜጣ ቃሉን የሰጠው የኤሌክትሪክ ኮርፖሬሽኑ ቃለ አቀባይ “በአሁኑ ጊዜ የሃይል ችግር የለም” ብሎ መካዱን እና እየታየ ያለው መቆራረጥም በኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ ያለው መጨናነቅ የፈጠረው እንደሆነ፤ ይህም ተጨማሪ መስመሮች ሲዘረጉ የሚወገድ ጊዜያዊ ችግር ነው ማለቱ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ማክሰኞ ጥቅምት 9 ቀን ፓርላማ የቀረበውና በቅርቡ የስኳር ልማት ኤጀንሲን ጨምሮ የኤሌክትሪክ ኮርፖሬሽኑ በግል ቁጥጥሩ ስር እንዲቀመጥ ያዘዘው መለስ ዜናዊ፤ አገሪቱ የገጠማት የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ከሥርጭት ኋላቀርነት የመነጨ ነው ሲል መናገሩን ይኸው ለአገዛዙ ቅርብ የሆነ ጋዜጣ ዘግቧል።
የዘረኛውን አምባገነን ቃል ለመደገፍ በሚመስል መልኩ አርብ ጥቅምት 12 ቀን ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠው የኮርፖሬሽኑ ሃላፊ ምህረት ደበበ፥ ለተከሰተው የሃይል መቆራረጥ መፍትሄው ጊዜ ያለፈባቸውን የኤሌክትሪክ ኃይል ማሰራጫ መስመሮች መለወጥ እንደሆነና፤ ለዚህም በየዓመቱ ለኤሌክትሪክ ኃይል ኢንቨስትመንት ብቻ እስከ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ማለቱን ሪፖርተር ጋዜጣ ዘግቧል።
ምህረት ደበበ ከዚሁ ቀጥሎም፥ ከአውሮፓ እና ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ሲወዳደር የኢትዮጵያ ህዝብ ለኤሌክትሪክ ሃይል የሚከፍለው ገንዘብ በጣም ዝቅ ያለ እንደሆነ በመግለጽ፤ ይህም እንደሚቀየር ፍንጭ ሰጥቷል።
የወያኔ አገዛዝ ከዚህ ቀደም የመብራት ሃይል መቆራረጥ እንደሚያበቃ በአገዛዙ ቁንጮ መለስ ዜናዊ በኩል ጨምሮ ተደጋጋሚ ቃል መግባቱ ይታወሳል። ገለልተኛ ኤሌክትሮኒክስ ሚድያን ለማፈን እና ለመሳሰሉት እኩይ ተግባራቱ ከፍተኛ መጠን ያለው የኤሌክትሪክ ሃይል እንደሚያባክን የሚነገርለት የወያኔ አገዛዝ፤ እየተከሰተ ላለው የኤሌክትሪክ ሃይል እጥረት አዲስ ምክንያት በመፍጠር በህዝቡ ላይ ዋጋ ለመጨመር የሚሰናዳው ዘረፋውን ለማጠናከር ብቻ ነው ሲሉ ለዝግጅት ክፍላችን አስተያየት የሰጡ ግለሰቦች ይናገራሉ።