አባ ጳውሎስ የተቀቡ ካህን ወይስ የተሳካላቸው ባንዳ?
ለረጅም ዘመናት ድምጹን ያጠፋ (የተለዮት) ወንድም፣ ወዳጅ፣ አብሮ አደግ፣ የሥራ ባለደረባ፣ የትምህርት ቤትና የሰፈር ጓደኛ ስሙን አልያም ኢ-ሜይል አድራሻውን አወቁዉት በትክክል እንደሆነ “ፍለጋ” በሚለው ስፍራ ላይ በመጻፍና በመጨቆን ብቻ ዛፍ ተደግፎ፣ ፍቅረኛውን አቅፎ፣ ልጁ እያጫወተ እንደኔው ዓይነቱ ደግሞ ድንጋዩ ማን ያንከባልልናል? ሲል ሰማይ ምድሩ ለተዘጋበት ዜጋ መፍትሔው ወደ ላይ መመልከት ነው ሲሉ ሰማየ ሰማዩን የሚመለከቱም አይጠፉም ብቻ ሌላ ሌላ ምስል የሚያስቀምጥም አይታጡም። የሰጡትን (ያስቀመጡትን) ምስል ይዞ ለፈላጊ የሚገኝበት እንዲሁም ደግሞ አንዴ ተፈላልገው የተገናቹት ወዳጅ ዘመድ በድንገት አልያም በቀጠሮ ተገናኝነተው ያለምንም ወጪ በቀጥታ ሃሳብ ለሃሳብ የሚለዋወጡበትና የሚያወጉበት ገጽ ነው ስሙም “ፌስ ቡክ” ይሉታል። ፎቶ ግራፍ እያዩና ልባቸው ያረፈበትን ሰው እየመረጡ ብቻ “ጨምረኝ” በማለት ደጅ የሚጸኑ በቀንም በሌሊትም የማይጠፉ ወገኖችም የዚህ ገጽ ወነኛ ተዋናዮች መሆናቸው ስሰማ ስለ ገጹ መልካምና መጥፎ ገጽታውን ብዙ ከማለት ተቆጥቤ ወደ ቁምነገሬ አልፌ አለሁና መልካም ንባብ!
እግር ሲጥለኝ “አለሁ!” የምለው ገጽ ስሞኑ ብቅ ብዬ ነበርና አንድ በቅርብ ርቀት የምንገኘው ወዳጄ በኩል የአባ ጳውሎስ ምስል የያዘ በእንግሊዝኛ “Lost Kingdoms Of Africa – Ethiopia pt I www.youtube.com” በሚል ለ10ት ደቂቃዎች አከባቢ የሚጫወት በአንድ ለረጅም ጊዜያት የአፍሪካ ባህልና ታሪክ ባጠኑ የታሪክ አዋቂ ተቀናብሮ የቀረበ አገኛለሁ። በበኩሌ ከአባ ጳውሎስ አንደበት የሰማሁትን የተፋለሰ ትምህርት ታሪኩን በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፈና ከሰፈረ እውነት ፈጽሞ የሚቃረን ሆኖ ስላገኘሁት በንጽጽራዊ መልክ ፍርዱ ለአንባቢያን በመተው እንወያይበትና እናስብበት ዘንድ ስለ ወደድኩ እነሆይ ብያለሁ።
በኢትዮጵያ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የበላይ የአመራር ሰው የሆኑ አባ ጳውሎስ “ከእኛ ጋር ነው ያለው” ስላሉት የቃል ኪዳን ታቦት መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? መቼም ስለ የቃል-ኪዳን ታቦት ከመጽሐፍ ቅዱስ ይልቅ የሀገር ውስጥም ሆኑ የውጭ ዜጎች የታሪክ ተመራማሪዎችና ፀሐፊዎች ተአማኝነት አላቸው የሚል ባለ አእምሮ ይኖራል ብዬ አላምንም። እንግዲህ በዚህ እውነታ ከተስማማን የግለ ሰቦችን መላምት ወደ ጎን ትተን አንስተን ስለምንወያየበት ዓቢይ ርዕሰ ጉዳይ ታሪክ የመጀመሪያና መጨረሻ ስለ ሆነ መጽሐፍ ቅዱስን የሚለውን ቁልጭ ያለ ሃሳብ አብረን እንመልከት።
አባ ጳውሎስ ዓይናቸውን ሳያሹ “ከእኛ ጋር ነው ያለው” ሲሉ የተነገሩት የቃል-ኪዳን ታቦት ወደ ኢትዮጵያ የመጣው በንጉሥ ሰሎሞን ዘመነ መንግሥት እንደሆነም አክለው ገልጸዋል (ለዚህ የተፋለሰ አባባል አባ ጳውሎስ የመጀመሪያ ሰው ናቸው እያልኩ አይደለም)። እንግዲህ ውድ አንባቢ ሆይ! እርስዎ ምን እንደሚሉ ባላውቅም ይህ መንፈስ ቅዱስ የተለየው አባባል እጅግ ከተጻፈ ሐቅ (ከመጽሐፍ ቅዱስ ሃሳብ) የሚጻረር የስጋ ለባሽ ድምጽ ሆኖ በመገኘቱ አባ ጳውሎስን የተቀቡ ካህን ወይስ የተሳካላቸው ባንዳ? እንድል አስገድዶኛል ምን ነው? ቢሉ ካህን የክህነት ሥራ ይሰራል ነውና እሱም የእግዚአብሔር እውነት ላላወቁ ማሳወቅ፣ ማስተማር፣ መመገብ ነው። እውነቱ ይህ ሳለ አባ ጳውሎስ ምንጫቸው መጽሐፍ ቅዱስ መሆኑ ቀርቶ የግለሰቦች ማስታወሻ ታሪክ መሰል ስብስብ ትልቅ ስፍራ በመስጠት የተናገሩትም እናደሆነ አሳባቂነት እንጂ መንግፈሳዊነት አይደለም።
እስቲ የእኚህ (የአባ ጳውሎስ) አነጋገርን በመጽሐፍ ቅዱስ ሐቅ እንመዝነው። “ኢዮስያስም ለእግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ፋሲካ አደረገ በመጀመሪያውም ወር በአሥራ አራተኛው ቀን ፋሲካውን አረዱ። ካህናቱንም በየሥርዓታቸውም አቆመ፥ በእግዚአብሔርም ቤት ያገለግሉ ዘንድ አጸናቸው። እስራኤልንም ሁሉ ያስተምሩ ለነበሩት፥ ለእግዚአብሔርም ለተቀደሱት ሌዋውያን እንዲህ አለ፦ ቅዱሱን ታቦት የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት ልጅ ሰሎሞን በሠራው ቤት ውስጥ አኑሩት ከዚህም በኋላ በትከሻችሁ ላይ ሸክም አይሆንባችሁም
ወድ ዝርዝር ሐተታዬ ከመዝለቄ በፊት ስለ መጽሐፉ ጥቂት ልበል መጽሐፈ ዜና መዋዕል ማለት “የታሪክ መጽሐፍ” ማለት እንደሆነ በመጽሐፉ ውስጥ እናገኘዋለን። ጻሓፊው የተጻፈበት ጊዜና ምንጩም የተመለከትን እንደሆነ በብዙሐኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ዘንድ መጽሐፈ ዕዝራን የጻፈ ዕዝራ እንደሆነ ይናገራሉ። መጽሐፉ ተጻፈ የሚባለውም በ5ኛ ምእተ ዓመት ዓ.ቅ.ክ አጋማሽ እንደሆነ ነው ጻሐፊው ከተጠቀማቸው ምንጮችም በከፊል ያየን እንደሆነ መጽሐፈ ሳሙኤልና መጽሐፈ ነገሥት ተጠቃሾች ናቸው። አሁንም አምላካችሁን እግዚአብሔርንና ሕዝቡን እስራኤልን አገልግሉ የእስራኤልም ንጉሥ ዳዊት እንደ ጻፈው ልጁም ሰሎሞን እንደ ጻፈው በየሰሞናችሁና በየአባቶቻችሁ ቤቶች ተዘጋጁ እንደ ሕዝቡም ልጆች እንደ ወንድሞቻችሁ በየአባቶች ቤቶች ሆናችሁ በመቅደሱ ቁሙ የሌዋውያንም ነገድ በየወገናቸው እንደ ተከፈሉ እናንተ ተከፈሉ ፋሲካውንም እረዱ፥” (መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ 35፥1-5)።
በንጽጽራዊ መልክ ወደ ዋና ርዕሰ ሐተታ ስንመለስ ይህን ይመስላል ከላይ ከፍ ብለን ባነበብነው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል መሰረት ኢዮስያስ ማን ነው? የት? መቼ የነገሠና ካከናወናቸው ተግባራት መካከልስ ቀጥተኛ በሆነ መልኩ የዛሬው
ርዕሳችን በተመለከተ ምን ሥራ ሰርቶ አልፈዋል? የሚሉ ወደ ሐቁ የሚያደርሱን ወሳኝ ጥያቄዎች ናቸውና ጎልተው ሊታዩን የሚገቡና ልብ ልንላቸው የሚገቡ ማስተዋልን የሚሹ ናቸው
ኢዮስያስ ማን ነው? ኢዮስያስ ማለት የስሙ ትርጓሜ “እግዚአብሔር ይደግፋል” ማለት ሲሆን 16ኛው የይሁዳ ንጉሥ የንጉሥ አሞጽ ልጅ ነው። ኢዮስያስ የስምንት ዓመት ወጣት ልጅ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ 31 ዓመት ማለት ከ639-609 ከክ.በ የነገሠ ንጉሥ ነበር። ኢዮስያስ በቅን ፈራጅነቱ የተመሰከረለት ከይሁዳ ጀምሮ እስከ ገሊላ ድረስ አምልኮ ባዕድን ያስወገደ ንጉሥም ነበር። ለአርባ ዓመታት ያክል ከጥበቡ የተነሳ በእስራኤል ኢዮርሳሌም ምድር ተፈርቶ በሰላም የገዛ ንጉሥ ከንጉሥ ሰሎሞን ጅምሮ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ በርካታ ክፉና ደጋግ 16 ነገሥታት የነገሡ ሲሆን 16ኛው ንጉሥ ኢዮስያስ ነበረ። እንግዲህ አባ ጳውሎስ በንጉሥ ሰሎሞን ዘመነ መንግሥት ወደ እኛ መጠዋል ሲሉ የተናገሩለትን የቃል-ኪዳን ታቦት በዚህ ዘመን ነበር የ370 ልዩነት ባለው በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት በኢየሩሳሌም ከተማ ንጉሡ ሰሎሞን ባሰራው ቤተ-መቅደስ እንደቀመጥ የተደረገ።
።
እንደው አንድ ሁለት ማለቴ አይቀር በዚህ አጋጣሚ ምራቃቸው ለዋጡ አስተዋዮችና ለታጋሽ አንባቢዎች ትንሽ ጥያቄ ቢጤ ልወርውር። አባ ጳውሎስ በተለመደው አንደበታቸው አስረግጠው “የቃል-ኪዳኑ ታቦት ከእኛ ጋር ነው ያለው!” አክለውም የመጣበትን ዘመን በማብራራት እንደገለጹት በንጉሥ ሰሎሞን ዘመነ መንግሥት ከሆነ ኢዮስያስ “ቅዱሱን ታቦት የእስራኤል ንጉሥ የዳዊት ልጅ ሰሎሞን በሠራው ቤት ውስጥ አኑሩት ከዚህም በኋላ በትከሻችሁ ላይ ሸክም አይሆንባችሁም” ለማለት እኔ ነኝ ያለ ድግስ ደግሶ ንጉሣዊ ንግግርና ትዕዛዝ ያስተላለፈ የቃል-ኪዳን ታቦቱ ከየት ቢገኝ ነው? የሰውን ታሪክ ጥላሸት መቀባት ደጉን በክፉ እውነት በውሸት በመለወጥ ጊዜያዊ ጥቅም ያስገኝልን ይሆናል። ይህን የለመዱ አባም ሀፍረት ሳይሰማቸው በአቻዎቻቸው (በሰዎች) ላይ የለመዱትን ብናምንም ባናምንም የታሪክ ሁሉ ባለቤት በሆነው በእግዚአብሔር ላይ እንዲህ ዓይነት ቅጥፈት ሲፈጽሙ ሳይ እውነትም አባ ጳውሎስ ማለት የተቀቡ ካህን መሆናቸውን ሳይሆን ለፖለቲካ ጥቅም ብቻ የተቀመጡና የዋሁን ሕዝብ በያዙት መስቀል ለማደናገር የተሾሙ ምንደኛ “መንፈሳዊ” መሪ መሆናቸውን ነው ከአንዴም ሁለቴ በተደጋጋሚ ለማስተዋል የቻልኩ።
ቁምነገሩ ማን ይሁን እውነተኛ ነው? ለትምህርትና ለተግሳጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለ ደግሞ ምክርን የሚለግስ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ (መጽሐፍ ቅዱስ) ወይስ አባ ጳውሎስ? ይህን የተቀመጠ ሐቅ አለመቀበል ማለትስ ማንን ውሸታም ማድረግ ነው ሙሉጌታ ወይስ እግዚአብሔር?
እንግዲህ ሲወርድ ሲዋረድ የተዋረደ ገቢ የመሰባሰቢያ ታሪክ ምዕራፍ እዚህ እንዝጋውና “እኛጋ ነው ያለው” ሲሉ የተደመጡ “የኃይማኖት” መሪ አባ ጳውሎስ ዕቃው እውነትም በአክሱም ከተማ በሚገኘው ቤተ-ክርስትያን ያለ እንደሆነም ለባለቤቶቹ (ለእስራኤላውያን) በመመለስ እንዲሁም ደግሞ ለአንዴና ለመጨረሻ በሊቀ-ካህናችን በክርስቶስ ኢየሱስ እንደተቆጠረለት የዘነጋ ህዝብ አለኝ የሚለውን ሁሉ ሽጦና ተበድሮ ራሱን ለአላስፈላጊ ውጪ በመዳረግ በእግዚአብሔር ፊት ለማስቆጠር የሚንገላታውን ዜጋ እውነቱን በመናገር ዕረፍት በመስጠት ክርስቲያናዊ ግዴታቸውን ይወጡ ዘንድ ነው በዚህ አጋጣሚ አባ ጳውሎስ የምማጸነው (ካህን ከሆኑ)።
ሌላም እውነት የመጽሐፍ ቅዱስ አማኞች የሆንን እደሆነም መጽሐፉ የሚለው “የባለእንጀራህን አህያ አትመኝ” ነውና የአክሱም ሐወልት ባለ ቤት እኛ ነን ስንል ጩኸን ተጫጩኸን ወደ ሀገራችን እንዳስመለስን የቃል-ኪዳኑ ታቦት የተሰጠው ለኢትዮጵያውያን ሳይሆን ለእስራኤላውያን ነውና በስርቆት የመነተፍነው (ላይኖር አለ የምንለው) ዕቃም እንደሆነ ወደ ስፍራው (ወደ ባለቤቶቹ) እንመልሰው። አይመስሎትም ውድ አንባቢ!! በስርቆት መስዋዕት ደስ የሚሰኝ ዳጎን እንጂ እግዚአብሔር ሊሆን አይችልምና።
ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ተከታይ በሙሉ! “ኤፍሬም ከአሕዛብ ጋር ተደባለቀ፣ ኤፍሬም ያልተገለበጠ ቂጣ ነው የባዕድ አገር ሰዎችም ጉልበቱን በሉት እርሱም አላወቀም ነበር ሽበትንም ወጣበት እርሱም አላወቀም ነበረ” (ሆሴ 7፥8) እንደሚል እኛም እንደ ኤፍሬም ፖለቲኮኞች በባንዴራ ሥም ሥመ መንፈሳዊያን ሳይገባቸው በያዙት መስቀል ከድጡ ወደ ማጡ ሲያገለባብጡን ኖሮዋልና ካለማወቃችንና መንቃታችን የተነሳ አይታይም አይነካም እየተባልን ኑሮአችን አንድ እጅርምጃ በማይለውጥ ስንኮታኮት ጉልበታችን ተበልቶ ካለቀ ደክመንም ሽበት ካወጣን በኋላ ከምንበረግግ በተጨማሪም “ነፍስ እውቀት የሌላት ዘንድ መልካም አይደለም” ተብሎ ሐቁ ሲነገረን ፊታችን ከማዞር እግዚአብሔር ይርዳን!!
ዲ/ን ሙሉጌታ ወልደገብርኤል
E-mail [email protected]
USA