የጋዳፊ ልጅ ሳይፍ አል-እስላም በቁጥጥስ ስር ዋለ

የሊቢያዉ መሪ ሞአመር ጋዳፊ ከተገደሉ ከወር ግድም በኋላ የሰላሳ ዘጠኝ አመቱ ልጃቸዉ ሳይፍ አል-እስላም ጋዳፊ ዛሪ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለጸ። አለም አቀፉ ወንጀል መርማሪ ፍርድ ቤት ለፍርድ የሚፈልገዉ ሳይፍ አል-እስላም በደቡባዊ ሊቢያ ኦባሪ በተሰኝ ቦታ መያዙን የሊቢያ የሽግግር መንግስት አረጋግጦአል። በሮይተርስ ዘገባ መሰረት የጋዳፊ ሁለተኛ ልጅ ሳይፍ አል-እስላም በሙሉ ጤንነት ላይ ይገኛል። ሳይፍ አል-እስላም የዛሬ ወር ግድም ከኔቶ በወረደ ፈንጂ ቀኝ እጁ በመጎዳቱ እጁ በፋሻ መታሸጉን ዘገባዉ አያይዞ ይጠቅሳል። በሊቢያ የኮነሬል ጋዳፊን ስልጣን ይረከባል የተባለዉ እና በብሪታንያ ትምህርቱን የተከታተለዉ ሳይፍ አል-እስላም በሊቢያ ከፍተኛ ስልጣን የነበረዉ እንደነበር ይታወሳል። ኔዘርላንድ ዴንሃግ የሚገኘዉ አለማቀፍ ወንጀል መርማሪ ፍርድ ቤት ሳይፍ አል-እስላምን ህዝብን በጅምላ በመጨፍጨፍ፣ ሰላማዊ ሰልፈኞችን በመግደል ወንጀል ካለፈዉ ሰኔ ወር መጠናቀቅያ ጀምሮ ለፍርድ ሲፈልገው እንደ ነበር የሚታወቅ ነው። ሳይፍ አል-እስላም ጋዳፊ ዴንሃግ አለም አቀፍ ወንጀለኛ መርማሪ ፍርድ ቤት ከቀረበ እድሜ ይፍታህ እንደሚበየንበት፣ በአገሩ በሊቢያ ለፍርድ ከቀረበ ደግሞ የሞት ቅጣት እንደሚጠብቀዉ ይገመታል። ያዳምጡ