ሸራተን ሆቴል ፊት ለፊት ሊደረግ የነበረው ሰላማዊ ምልጃ በመንግሥት የደኅንነት ሠራተኞች እና በፌዴራል ፖሊስ አባላት ተበተነ
(ሙሉ ገ)
ለሸራተን ሆቴል ማስፋፊያ ፕሮጀክት ከአካባቢያቸው የሚፈናቀሉ ከአምስት ሺሕ በላይ የሚኾኑ አባወራዎች ባለ ሀብቱን ሼህ ሑሴን ሙሐመድ አላሙዲንን እና መንግሥትን በምትክ የካሳ ክፍያ ጉዳይ ላይ ኢ-ፍትኀዊ አሠራር እንዳይኖር ለመለመን ከሸራተን ሆቴል ፊት ለፊት በሚገኘው አነስተኛ ሜዳ ላይ ሊያደርጉት የነበረው ሰላማዊ ምልጃ በመንግሥት የደኅንነት ሠራተኞች እና በፌዴራል ፖሊስ አባላት አስገዳጅነት ተበተነ።
እሁድ ጥቅምት 14 ቀን 2003 ዓ.ም ከጠዋቱ በ3፡00 ሰዓት ላይ ከአካባቢያቸው በመፈናቀል ላይ ያሉት በሸራተን ዙርያ የሚገኙ እነዚሁ ነዋሪዎች ከሕጻን እስከ አረጋውያን በመኾን በቦታው ላይ የተገኙት መፈክሮችን ይዘው ነበር። የጠቅላይ ሚስትሩን ፎቶ እና ከሥሩ “እኛ የልማት አደናቃፊዎች ሳንኾን በልማት ላይ ያሉ የአፈጻጸም ችግሮች የፈጠሩብንን ኢ-ፍትኀዊነት ለማሳወቅ መንግሥትን አና ባለ ሀብቱን ሼሕ ሙሐመድ አላሙዲንን ለመለመን የወጣን ምስኪኖች ነን” የሚሉ መፈክሮችን ይዘዋል። እነዚሁኑ መፈክሮች የፌዴራል ፖሊሶቹ በስፍራው ላይ ደርሰው ነጥቀዋቸዋል።
በሸራተን ሆቴል የ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ከአካባቢያቸው ከተፈናቀሉት አምስት ሺሕ በላይ አባወራዎች መካከል ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ አንድ አባወራ ይህን ሰላማዊ የኾነ የምልጃ ሰልፍ ለማድረግ የተነሳሱት ከዚህ ቀደም ከዚሁ ስፍራ ላይ የተነሱት አባዎራዎች የተሰጣቸውን የምትክ ቤት እና ተጨማሪ ጥቅማጥቅም ታሳቢ በማድረግ እንደኾነ ገልጸዋል። “የመጀመርያዎቹ ዙር ተፈናቃዮች ምትክ ቤት ተሠርቶላቸዋል፤ በቀበሌ ቤት ውስጥ ይኖሩ ለነበሩትም ተመጣጣኝ ቤት የተሠራላቸው ሲኾን የቤት ኪራዩም እንዲሁ ተመጣጣኝ ተደርጎላቸው ነበር። በእኛ እየተፈጸመ ያለው ግን መንግሥት ጉዳዩን እኔ አስፈጽማለኹ ብሎ መሬታችን በሊዝ ለባለ ሀብቱ በመሸጥ አውላላ ሜዳ ላይ እንደንውድቅ ማድረግ ነው። በዚሁ የመንግሥት ውሳኔ ተስፋ በመቁረጥ ከመካከላችን ያሉ አዛውንቶች ዕድሜያቸውን ሙሉ የለፉበትን ዕድርን የመሰለ የማኅበራዊ ተቋም ንብረት እስከመሸጥ ድረስ እንዲሄዱ ተደርገዋል” ይላሉ።
የአዲስ ነገር ሪፖርተር ከቦታው ኾኖ እንደታዘበው በደህንነት ሠራተኞቹ እና በፌዴራል ፖሊሶች ወከባ እና እንግልት የተበሳጩት የአካባቢው ነዋሪዎች እንደገና በሜዳው ላይ መሰባሰብ ጀምረው ነበር። ፖሊስ እንደገና ከተሰባበሰቡት መሀል ኅብረተሰቡን አነሳስተዋል ያላቸውን ዐሥራ አንድ አባወራዎች እና ሁለት እናቶችን በመኪና ጭኖ ወደ ፖሊስ ጣብያ ወስዷቸዋል። ይህን ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ታሳሪዎቹ እንዳልተፈቱ የፖሊስ ምንጮቻችንም ለአዲስ ነገር ገልጸዋል።
በሰላማዊ ምልጃው ላይ ሲሳተፉ ከነበሩት መካከል አንዱ የኾኑት አቶ መሳፍንት በቀለ (ስማቸውን ቀይረው ተናግረዋል) እንደገለጹት በቀበሌ እና በክፍለ ከተማ ያሉ ሐላፊዎች በግል ይዞታ የሚተዳደር ቤት ለነበራቸው ነዋሪዎች ከ 13 እስከ 18 ሺሕ ብር የሚገመት ገንዘብ ሰጥተዋቸዋል። “ይህ ታሳቢ ያደረገው ከከተማ ክልል ወጣ ብሎ ሚሰጠን የገበሬ ቦታ ላይ ቤት እንደንሠራ ነው። ነገር ግን ይህ ብር አይደለም ቤት ሊያሠራን ቀርቶ ለኮንደሚኒየሙ አነስተኛ ክፍል(ስቱዲዮ) የሚከፈለውን 56 ሺሕ ብር እንኳ የሚሸፍንልን አይደለም” ብለዋል።
መንግሥት ለችግሩ እውነተኛ እና ቀጥተኛ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ የልማት ተፈናቃዩን ኅብረተሰብ ባዶ ተስፋ በማስታቀፍ፣ በማታለል፣ በማጭበርብር እና በማሸማቀቅ ፖሊሲውን በግድ ተፈጻሚ እያደረገ ነው የሚሉት አቶ መሳፍንት ዛሬ ያደረግነው ሰላማዊ ሰልፍ ሳይኾን የደካሞች ምልጃ እና ልመና ስለኾነ ከአዲስ አበባ መስተዳደር ፈቃድ አልጠየቅንም። ስንጠይቅም አልተፈቀደም እንባላለን። በአንጻሩ ጥቂት የራሳቸው ሰዎችን እና ካድሬዎቻቸውን በመንግሥት ሚዲያ በማቅረብ በኹኔታው ደስተኛ የኾንን ለማስመሰል የአብዛኛውን ተፈናቃይ ምሬት እንዳልነበረና እና ምንም እንዳልተፈጠረ አድርገው ያቀርባሉ” ብለዋል።