ሰበር ዜና፦ አባ ሰረቀ ብርሃን ደጀ ሰላምን እና ማ/ቅዱሳንን ሊከሱ ነው
(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 24/2010፤ ጥቅምት 14/2003 ዓ.ም):- የሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ዋና ኃላፊ ቆሞስ አባ ሠረቀ ብርሃን ወልደ ሳሙኤል “ደጀ ሰላም የተሰኘው ‘ድህረ ገጽ’ (ድረ ገጽ ለማለት መሆኑ ነው) … በማንነቴና በሃይማኖቴ ላይ ከባድ የግድያ ወንጀል” ስለፈፀመ “የሀገሪቱን ሕገ መንግሥት በመጠቀም ወደ ፍርድ ለማቅረብ ቅድመ ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ” መሆኑን ሰሞኑን በጻፉት ደብዳቤ ገልጸዋል።
በጥቅምት 11/2003 ዓ.ም “ለቅዱስ ሲኖዶስ፣ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ፣ ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ለሚመለከታቸው የቤተክርስቲያን ሊቃውንት” የተጻፈውና በግልባጭ በደፈናው “የዚህ ኮፒ ለሚመለከተው ሁሉ ይድረስ” የተባለለት ይህ ደብዳቤ ማ/ቅዱሳን እንዴት ሲያሳድዳቸው እንደኖረ በአራት ነጥቦች ከዘረዘሩ በኋላ በ5ኛነት “ደጀ ሰላም በተባለው በአባላቱ የሚመራው ድህረ ገጽ የስም ማጥፋት ዘመቻ” እያደረገባቸው መሆኑን ጠቅሰዋል። ስም ማጥፋቱ ምን እንደሆነ ዘግየት ብለው ሲያብራሩም ከሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ ጋር የተጻጻፉት እና በጡመራ መድረኩ ላይ የወጣው ፀረ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የምሥጢር ግንኙነታቸው (CLICK HERE TO READ) መሆኑን አብራርተዋል።
አባ ሰረቀ ስለ ደጀ ሰላም ማንነት ሲገልፁም “ፓትርያርኩን ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ከቅዱስ ፓትርያርኩ፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን ከመንግሥት፣ መንግስትም ከቤተ ክርስቲያን ለማጋጨት፣ ያልተደረገውን ተደረገ፣ ያልተባለውን ተባለ እያለ ራሱን በቤተ ክርስቲያኒቱ ታዛ ሥር ደብቆ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት እስከ ዋሽንግተን ዲሲ ሀገረ ስብከት መረቡን ዘርግቶ እየተንቀሳቀሰ” የሚገኘው “ደጀ ሰላም የተሰኘው ድህረ ገጽ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ያሳደረው ጫናና የፈጸመው በደል ቀላል አይደለም” ብለዋል።
ደጀ ሰላም “በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ያሳደረው ጫናና በደል ቀላል” አለመሆኑን ለማጠየቅ “በአውራምባ ታይምስ ላይ ከወጣ በኋላ አስተማሪነቱ ታምኖበት በጡመራ መድረካችን ላይ በድጋሚ ያወጣነውን፣ ነገር ግን በባሮክ ዘሣልሳይ ሺሕ የተዘጋጀውን “ቤተ ክህነቱ ያጣው የቤተ ክህነቱ ሰው” (Click HERE to Read) የሚለውን ጽሑፍ አባሪ አድርገው አቅርበዋል። ጽሑፉ የሚያስከስስ ከሆነ “አውራምባ ታይምስን”ም አብረው ይከሱት እንደሆነ ገና አልታወቀም።
አባ ሰረቀ በዚህ ወቅት ደብዳቤውን ለቅዱስ ፓትርያርኩ እና ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እንዲሁም በግልባጭ በደፈናው “የዚህ ኮፒ ለሚመለከተው ሁሉ ይድረስ” በማለት ያቀረቡት ቅዳሜ የተጀመረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ ላይ እንዲታይላቸው በመፈለግ፤ ለዚህም አስቀድመው የተወሰኑ ሊቃነ ጳጳሳትን በማናገር እና በማሳመን መሆኑን ምንጮቻችን ገለጸዋል። ከቅዱስ ፓትርያርኩ በተጨማሪ በገልባጭ ያሳወቋቸው እነማን መሆናቸው ባይዘረዘርም በከዚህ በፊት የደብዳቤ አጻጻፋቸው ምሳሌነት የሚኬድ ከሆነ ለመንግሥት የጸጥታ እና የደኅንነት አካላት ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። “ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት” እከሳለሁ ማለታቸውም ይህንኑ ሊጠቁም የገባ ሳይሆን እንደማይቀር ተገምቷል። ቆሞስ አባ ሰረቀ በዚህ የጥቅምት ወር 2003 ዓ.ም ማዕረገ ጵጵስና እንዲፈቀድላቸው “በአጭር ዝርዝር” ውስጥ (short list) ከገቡት በተለይም ብዙ ነቀፋ ካለባቸው እና ይህ ማዕረግ አይገባቸው ተብለው ከሚከሰሱት መካከል መሆናቸው ይታወቃል። ደጀ ሰላምም የኚህን እና ተመሳሳይ ግብር ያላቸው የሌሎች ጥቂት መነኮሳትን ወደ ጵጵስና መምጣት ለመቃወም ዝግጅት እያደረገች ነበር። አሁንም በዚሁ ትገፋበታለች። በደጀ ሰላም ሰበብ የክስ መዝገብ የተዘጋጀለት ማ/ቅዱሳን ስለጉዳዩ የሚያወጣው መግለጫ ካለ ወደፊት የሚታይ ይሆናል። ማኅበሩ ከዓመት አስቀድሞ “ደጀ ሰላም የእኔ አይደለችም” ሲል መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።
++++++++++++++++++
ከዚህ በፊት ስለ አባ ሰረቀ ምን ተዘግቧል?


