በአሜሪካን አገር በሲያትል ክፈል ግዛት የግንቦት 7 የኦነግና የህብረት መሪዎች የተሳተፉበት ህዝባዊ የውይይት መድረክ እጅግ በተሳካ ሁኔታ መካሄዱ ታወቀ
በሰሜን አመሪካ በሲያትል ከተማ ከአመት በፊት የተቋቋመው የሲያትል ህዝባዊ ፎረም ከትናንትና በስቲያ እሁድ ህዳር 3 ቀን በአገራችን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ 3 የተለያዩ ፖለቲካ ፓርቲ ተጠሪዎችን ለማወያየት አዘጋጅቶት የነበረው ስብሰባ እጅግ በተሳካ ሁኔታ መካሄዱን የግንቦት7 ዘጋቢ ከሥፍራው በላከልን ዜና ገለጸ።
ፎረሙ በጠራው በዚህ የመጀመሪያ ስብሰባ ላይ ውይይት ለማድረግ የተጋበዙት የግንቦት 7 ንቅናቄ ፤ የኦሮሞ ነጻነት ግንባርና ህብረት መሆናቸውን የገለጸው ዘጋቢያችን፤ ቁጥሩ እጅግ በርካታ የሆነ የሲያትልና አካባቢዊ ኢትዮጵያዊ ነዋሪ መገኘቱንና ውይይቱን ሞቅ ባለ የአገር ፍቅር ስሜት መከታተሉን አረጋግጦአል።
ህዝባዊ መድረኩን በንግግር የከፈቱት የፎረሙ ሊቀመንበር ዶ/ር አሸናፊ ጎሳየ፤ ህዝባዊ ፎረሙ የተቋቋመለት ዓላማ በህዝቦች መካክለ የሚገነባውን የጥርጣሬና የጥላቻ ግድዳ አፍርሶ ሰላም ፍቅር እና አንድነት እንዲሰፍን ማድረግ ነው ካሉ ቦኋላ፤ ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት በአገራችን ውስጥ ለሰብዓዊ መብት መከበር፤ ለፍትህ፤ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ሲሉ ህይወታቸውን ላጡ፤ ያላሳዳጊ ለቀሩ ህጻናትና ያለጧሪ የቀሩ ወላጆችን ለማስታወስ የአንድ ደቂቃ የሂሊና ጸሎት እንዲደረግ ታዳሚውን በመጠይቅ በ ውይይቱ ላይ ለመሳተፍ የተጋበዙትን ፖለቲካ ፓርቲዎች ወክለው በአዳራሹ የተገኙትን እንግዶች አስተዋውቀዋል።
በዚህም መሠረት ግንቦት 7ን በመወከል ሊ/መንበሩ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፤ ኦነግን በመወከል ዋና ጸሃፊው አቶ አሚን ጁንዲን እንዲሁም ህብረትን በመወከል የከፍተኛ አመራር አካል የሆኑት ዶ/ር አረጋዊ በረሄ መገኘታቸው ታውቆአል።
ከተጋባዥ እንግዶች መካከል ቀድመው እንዲናገሩ የተጋበዙት ቀደም ሲል የህወሃት መሥራችና መሪ የነበሩት ዶ/ር አረጋዊ በረሄ ሲሆኑ ፎረሙ የተቋቋመለትን ዓላማ በማወደስ ለአላማው መሳካት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ቃል በመግባት፤ በኢትዮጵያችን ውስጥ የዴሞክራሲ ሥርዓት እንዲገነባ ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ለምን ማስተባበር እንዳልተቻለ? ከፖለቲካ ድርጅቶችና ከህዝባችን ምን እንደሚጠበቅ በማውሳት ሰፊ የሆነ ትንትናኔና ማብራሪያ መስጠታቸው ተገልጾአል።
ዶ/ር አረጋዊ በንግግራቸው ውስጥ በአገራችን ውስጥ በተለያየ ግዜ የተፈራረቁ አጼዎች የስልጣናቸው ምንጭ እግዚአብሄር ነው ብለው ያምኑ የነበሩ አምባገነኖች መሆናቸውን አስታውሰው በነርሱ እግር የተተኩት መንግስቱ ኃ/ማሪያምና መለስ ዜናዊ ግን የለየላቸው አሸባሪ አምባገነኖች ሆኖው ተገኝተዋል ብለዋል። መንግሥቱ ሃይለማሪያምንና መለስ ዜናዊንም ሲያነጻጽሩ መንግስቱ የቀን አሸባሪ የነበረ ሲሆን በርሱ እግር የተተካው መለስ ዜናዊ ደግሞ የጨለማ ውስጥ አሸባሪ ነው በማለት የመለስ ዜናዊን ጥልቅ ክፋትና እየፈጸማቸው ያሉትን ወንጀሎች ዘርዝረዋል:፡
ከዶር አረጋዊ ቀጥለው መድረኩን የተረከቡት የኦነግ ዋና ጸሃፊ አቶ አሚን ጁንዲ ሲሆኑ አስቀድመው በኦሮሚኛ ቋንቋ ከዚያም አስከተልው በአማርኛ ቋንቋ ንግግራቸውን አቅርበዋል።አቶ አሚን ኦነግ የህዝብ ጠላት የለውም የኦነግ ጠላት ወያኔ የገነባው የፖለቲካ ጭቆና መረብ፤የኢኮኖሚ ብዝበዛ መዋቅር እና ህዝብን በህዝብ ላይ ለማነሳሳት የሚደረግ ጥረት ነው ብለዋል።አስከትለውም አባቶቻችን ጣሊያንን የተዋጉትና ከአገሪቷ እንዲወጣ ያደረጉት ልማት አላመጣም ብለው ሳይሆን ነጻነታችንን አጣን ብለው ነው።ልማትማ ከመለስ ዜናዊ በላይ ጣሊያኖች ብዙ መንገዶችን ብዙ ህንጻዎችን ለመሥራት ሞክረዋል።ችግራችን የልማት አለምጣት ብቻ አይደለም ይልቁንስ ነጻነታችንን ማጣታችን ሲሆን ያጣነውን ነጻነታችንን ሳናስመልስ ትግላችንን አናቆምም።ነጻነታችን ሲመለስ ያገራችንን ደኖች የነጻነት ተዋጊዎች መሸገጊያ ሳይሆኑ የዱር እንስሳቶቻችን መናኽሪያ ይሆናሉ።ነጻነታችን የተረጋገጠ እለት ነጻኔቴን ብሎ ነፍጥ አንግቶ ለመሞትና ለመግደል የሚቆም ትውልድ አይኖርም።ያን ግዜ ሁሉም ለአገር ልማትና እድገት አብሮ የሚቆምበት ዘመን ስለሚሆን እጅ ለእጅ ተያይዘን በአገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ በሰላም አብረን እንኖራለን።ኦነግ የመገንጠል ዓላማ የለውም።የኦሮሞ ህዝብም ከአገሩ ተገንጥሎ የትም አይሄድም ሲሉ እድምተኛው ሞቅ ባለ ጭብጨባ ድጋፉን ገልጦላቸዋል።
ከአቶ አሚን ቀጥሎ ሦስተኛ ተናጋሪ የነበሩት የግንቦት ሰባት ሊ/መንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ሲሆኑ የአንድነታችን ፈተናዎች ምንድ ናቸው? በሚል ርዕስ ታዳሚውን የሚኮረኩር ሰፋ ያለ ትንታኔና ማብራሪያ አቅርበዋል።
ወድ አንባቢያን ዶር ብርሃኑ ነጋ በሲያትሉ ስብሰባ ላይ ያቀረቡት ንግግር ሙሉ ቃል በድህረገጻችን ላይ የወጣ መሆኑን እየገለጽን ታነቡት ዘንድ እናበረታታለን።