በአዲስ አበባ የየካ ክፍለ ከተማ ህዝብ ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ባወጣው አዲስ የሊዝ አዋጅ ላይ ማመፅ ጀመረ
መሬት የመንግስት ነው በሚል ሽፋን በገጠሩ የሚገኘው የኢትዮጵያ ህዝብ በአገዛዙ ላይ ምንም ተቃውሞ እንዳያነሳ ሌት ከቀን ሲሰራ የነበረው የዘራፊው ወያኔ አገዛዝ ፊቱን ወደከተማ ነዋሪዎች በማዞር ማንኛውንም የከተማ ቦታን በሊዝ እንዲቀየር አዲስ ህግ መደንገጉ የሚታወቀ ሲሆን የየካ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ድንጋጌው ፤ ንብረት አልባ አድርጎ የሚያስቀርና ለወያኔም ተገዥ እንድንሆን የማድረጊያ መሳሪያ ነው በማለት በጽኑ መቃወማቸውን ዘጋቢያችን ከአዲስ አበባ ባስተላለፈልን ዘገባ ገለጸ::
እንደዘጋቢያችን ሪፖርት የአረመኔው የወያኔ አገዛዝዝ አጫፋሪዎች በሆኑና ለሆዳቸው ባደሩ ባለስልጣናት አማካኝነት ነዋሪዎች የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ወረቀት እንዲወስዱ ጥሪ ቢያደርጉም በየካ ክፍለ-ከተማ ከሚገኙት 8 ሺህ ነዋሪዎች መካከል ለቀረበው ጥሪ ፤ ከ6 ሺህ የሚበልጠው ህዝብ አኩርፎና አምጾ ጥሪውን ሳይቀበል መቅረቱ ታውቋል።
ባለፈው እሁድ ህዳር 3 ቀን የወያኔ አገዛዝ ባለስልጣናት በግድ እንዲካሄድ አድርገውት በነበረ ስብሰባ ላይ የአዲሱ የሊዝ አዋጅ ውዝግብ የፈጠረ ሲሆን በሲሁ ስብሰባ ላይ፤የመሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ወጥቶላቸው እንዲወስዱ የስም ዝርዝራቸው በየቀበሌው ከተለጠፈ የየካ ክፍለ ከተማ 8ሺህ ነዋሪዎች መካከል 2ሺህ ሰዎች ብቻ ወደ የቀበሌው ጽ/ቤት መቅረባቸው ታውቁአል ይሁን እንጂ እነኝህም 2 ሺህ የሚገመቱት ነዋሪዎች ቢሆኑ ስለተጠየቁት ገንዘብ ከፍተኛ መሆን አቤቱታ ማሰማታቸውና፤ ከ2 ሺዎቹ መሀከልም የተተመነላቸውን ክፍያ ለመፈጸም ፈቃደኛ የሆኑት በጣም ጥቂት እንደሆኑ፣ የተቀሩትም ክፍያው በጣም እንደበዛባቸውና ሊቀነስላቸው እንደሚገባ ጥያቄ ማቅረባቸው ታውቁአል ከዚሁ ጋር በማያያዝ 6 ሺህ የክፍለ- ከተማው ነዋሪዎች ወደ የቀበሌው ዝር ለማለት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ራሱ የክፍለ-ከተማው የወያኔ ተወካይ በዕለቱ ለተሰበሰቡት ነዋሪዎች በግልጽ መናገሩን ዘጋቢያችን ባስተላለፈልን ዘገባ አክሎ ገልጹአል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዘገባ በሺህ የሚቆጠሩ የየካ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ስብሰባውን ረግጠውና የስብሰባውን አዳራሽ ጥለው ለውጣት የተገደዱት ፤በአዲሱ የመሬት ሊዝ አዋጅና በመሬት ይዞታ ማረጋገጫ፣ እንዲሁም በሊዝ የክፍያ ስርዓትና ባለይዞታዎች በካሬ ሜትር እንዲከፍሉ በተተመነው ገንዘብ ዙሪያ ጥያቄ አቅርበው ከእለቱ የስብሰባ መድረክ ምላሽ ስለተነፈጋቸው መሆኑን የደረሰን ዜና አመላክቶአል።
እንደዜና ዘገባ ምንጫችን ህዝቡ “ለልማት በሚል ሽፋን” ለመወያየት የተደረገለትን ጥሪ በማክበር ዕሁድ ሕዳር 3 ቀን 2004 ዓ.ም ከፈረንሳይ ኤምባሲ ዝቅ ብሎ የሚገኘው ፈረንሳይ መናፈሻ የስብሰባ አዳራሽ ከጠዋቱ 2 ሰዓት ከ30 ጀምሮ የተገኘ ቢሆንም፤ከውይይቱ መጀመር በፊት ነዋሪው የመሬትና የሊዝ፣እንደዚሁም የይዞታ ማረጋገጫ ጉዳይ በአጀንዳ እንዲያዙለት ጥያቄ ማቅረቡን ውዝግብ ሊፈጠር ችሏል ብሉአል፡፡ በመቀጠልም የተፈጠረውን ውዝግብ ለመፍታት የመድረኩ መሪዎች ብርቱ ጥረት ቢያደርጉም ፤ለውይይት የታደመው ነዋሪ፦ “ከልማት በፊት የመሬት፣የሊዝና የመሬት ክፍያ አፈፃፀም ጉዳይ ይቅደም! . . .” በሚል ጠንካራ አቋም መጽናቱንና በዚህም ሳቢያ ውዝግቡ ይበልጥ እየተካረረ ሄዶ ለስብሰባ ከተጠራው ሕዝብ መካከል አብዛኛው አዳራሹን በቁጣ ለቅቆ በመውጣት ቅያሜውን ገልጿል ብሏል፡፡
በተለይ ከተሰብሳቢዎቹ አንድ ግለሰብ ከመቀመጫቸው በመነሳትና በሀይለ ቃል፦ “ሕዝቡ በአብዛኛው በጡረታና በድጎማ የሚኖር፣ባለፈው ሥርዓት በውትድርና ሙያ አገሩን ሲያገለግል የነበረና በአሁኑ ወቅት የተረሳ በመሆኑ የገዛ ኑሮውን እንኳን ለማቃናት ተቸግሯል፡፡ እንደዚሁም ሆኖ ከዚህ በፊት ለጤና፣ለትምህርት፣ለኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋት፣ለዓባይ ግድብ ወዘተ እየተባለ የአቅሙን ያህል አዋጥቷል፡፡ ለመንገድ ልማት እየተባለም ያላዋጣበት ጊዜ የለም፡፡ ነገር ግን ይሰራል የተባለው መንገድ አልተሠራም፡፡ እንደገና ዛሬም ለመንገድ መዋጮ ክፈል ይባላል፡፡ እንደዚህም ሆኖ ለአካባቢ ልማት ያለውን ከመስጠት አልቦዘነም፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ለመሬት ካርታ የተጠየቀውን ከፍተኛ ገንዘብ ለመክፈል አቅም የለውም ” በማለት ነዋሪው ያለበትን ችግር ማንጸባረቃቸው ታውቁአል፡፡
አምባገነኑና ዘራፊው የወያኔ አገዛዝ በ 1997 ምርጫ ወቅት በኢትዮጵያዊያን በተለይም በአዲስ አበባ ህዝብ መተፋቱን ከተገነዘበ በሁአላ ተከታታይ የሆኑ የበቀል ርምጃዎችን የወሰደና እየወሰደ ያለ መሆኑ በስፋት ሲዘገብ ቆይቱአል አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ዘረኛው አገዛዝ በአዲስ መልክ ያወጣው የሊዝ አዋጅ እነኝህ ሁሉ ርምጃዎች ከገባበት የፍርሃት አረንቁዋ ውስጥ ሊያወጡት ባለመቻላቸው በከተሞች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለአገዛዙ ሰጥ ለጥ ብለው እንዲገዙለት ለማድረግ የቀየሰው ስልት እንደሆነ ይስማማሉ፡፡