ቢቢሲዎች ለይቶላቸው አበዱ ልበል? በይሄስ አእምሮ
ከሁሉም በፊት በወያኔው ኢሰብኣዊ አገዛዝ ተንገሽግሾ ሰውነቱ ላይ ቤንዚን በማርከፍከፍ ይህችን የደም ምድር ኢትዮጵያ በገዛ ፈቃዱ የተሰናበተውን ወንድማችንና ልጃችንን መምህር የኔሰው ገብሬን የከፈለውን መስዋዕት ፈጣሪ እንደአቤል መስዋዕት ቆጥሮ መንግሥተ ሰማይን ያውርስልን ማለት እፈልጋለሁ፡፡ ካህናት እንዳይታዘቡኝ አንድ ሁለት ቃላትን ልናገር፡፡
‹የኔሰው ራሱን አጠፋ› ብዬ ለማመን ይከብደኛል፤ አልችልምም፡፡ እርግጥ ነው ራሱን አጥፍቷል፡፡ ግን ለምን? ይህ ወጣት አስተሳሰቡን እንደብዙ ወጣቶች ለሆዱና ለጠባብ ሥጋዊ ፍላጎቶቹ ለውጦ ኢትዮጵያን ቢክድ በአፍታ ሚሊዮነር ሊሆን በቻለ ነበር – ልማታዊ ነጋዴ፣ ልማታዊ ኢንቬስተር፣ ልማታዊ የሥራ ሂደት ባለቤት፣ ልማታዊ የኢሕአዴግ የወጣት ሊግ፣ ልማታዊ የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንዱስትሪ ባለቤት… ቢሆን ኖሮ ቢጠሩት የማይሰማ ዲታ በሆነ ነበር – እንኳን ቀረበት፡፡ የተሻለውን መረጠ፡፡ ከዚህ ሁሉ ግን የኅሊናው ታዛዥ ሆነና በደልንና ኢፍትሓዊነትን በሰላማዊ መንገድ ለመዋጋት ቆርጦ ተነሳ፤ ባዶ ዕጁን በፍቅር ሰባኪ አንደበቱ ብቻ ተዋጋቸው፡፡ ብዙ ጮኸ፡፡ ፍትህና ነጻነት እንዲኖር ታገለ፡፡ ለዜጎች መብት ተከራከረ፡፡ ነገር ግን የጠበቀው ሳይሆን ያልጠበቀው እየተከናወነ ከሥራም ከነጻነትም ከዲሞክራሲያዊ መብትም ሳይሆን ሰሚ አጥቶ ሜዳ ላይ ቀረ፡፡ እናም ለሀገሩና ለወገኖቹ አንድ አቅሙ የሚችለውን ነገር ማድረግ እንደሚኖርበት አመነ፡፡ በዚያም እምነቱ ለዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ምሥረታ አንዲት ጡብ – ከፕሮፌሰር አሥራት፣ ከአሰፋ ማሩ፣ ከፋንታሁን ወርቁና ከሌሎች ጥቂቶች በስተቀር እስካሁን ማንም በፈቃዳቸው ሊሰጧት ያልደፈሯትን አንዲት ጡብ በፅኑ መሠረት ላይ አኑሮ፣ የጀመረው የመብት ተሟጋችነትና የነጻነት ትግል ግን እንዳይቋረጥ ተማፅኖ ላይመለስ አልፏል፤ በኔ በኩል እንደኃጢያት እንዳይያዝበት ይልቁንም በየማነ አብ እንደተቀመጠው በክርስቶስ ደም የጸደቀ ፈያታይ አሁኑኑ በእግዚአብሔር ቀኝ እንዲቀመጥ እጸልያለሁ፡፡ እናም ይህ ወጣት አርአያ ሊሆነን ተነሳስቶ በወሰደው እርምጃ ራስን የማጥፋት ወንጀል እንደፈፀመ ቆጥሬ ልቃወመው የሚያስችለኝ የሞራል ድፍረት የለኝም፡፡ ስንፈራው የነበረው ነገር ድኾ ድኾ መምጣቱን ግን ልብ ይሏል፡፡ እንደቺንዋ አቼቤ የመጽሐፍ ርዕስ ”No Longer at Ease” ማለት ከአሁን ወዲህ ነው፡፡ ወያኔ ከእንግዲህ ባጭር ሊታጠቅ ይገባዋል፡፡ የዘራውን ለማጨድ፣ በሠፈረው ቁና ለመሠፈር ዐውድማውን ይለቅልቅ እንጂ የሀገር ሀብትና ንብረት ለፖለቲካ ሎቢስቶች(አሻሻጭ ደላሎች) እና ቢቢሲን ለመሳሰሉ ቅሌታም የዜና ማዕከላት በገፍ እየረጨ የበሬ ወለደ ነጭ ውሸቱን ቢነዛ ከአሁን በኋላ ፋይዳ የለውም፡፡ በሞተ ሰዓት ኢትዮጵያ በብርሃን ፍጥነት እያደጉ ከሚገኙ አራት የዓለም ሀገሮች ውስጥ አንዷ ሆናለች ብሎ መናገርና ማስነገር ቀርቶ ወያኔ ዛሬም ይሁን ነገ ሥነ ሕይወታዊ ቀመሩን በድንገት ለውጦ ከእባብነት ወደርግብነት ተቀይሮ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ማርና ወተት ከሰማይ ቢያዘንብ የሚያምነውም ሆነ የሚቀበለው የለም፡፡ የወያኔን ነጭ ውሸት ለለመድነው የዛሬው ውሸት ምንም ላይመስለን ይችላል፡፡ ነገር ግን ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያላቸውን እንደቢቢሲ ያሉ የዜና ተቋማትን ተንተርሶ እንዲህ እንደዛሬው ያለ ወራዳ ዜና ሲነገር መስማቱ በውነቱ ያሳዝናል፤ ሰው ሆኖ መፈጠርንም ያስጠላል፡፡ ሕግ የለም እንጂ ቢኖር ኖሮ ቢቢሲን ዘ ሄግ ፍርድ ቤት ወስዶ መገተር ነበር – ለነገሩ እሱስ የማን መሣሪያ ሆነና፡፡ የመጥረቢያ ልጅ መዘለፊያ አይደል ተረቱስ? አንደኛው አንባቢ አንደኛው ተርጓሚ!
እውነቱን ለመናገር ከማስታውሰው የቅርብ ጊዜ የፕሮፓጋንዳ ታሪክ እንደዛሬ ያዘንኩበት ጊዜ የለም፡፡ ቢቢሲን ያህል እንደመርግ የሚከብድ ታላቅ የዜና አውታር እንዲህ የመሰለ ውርደት ውስጥ ይገባል ብዬ በህልሜም ሆነ በዉኔ አስቤው አላውቅም፡፡ እርግጥ ነው በነጭና በጥቁር፣ ባደጉና ባላደጉ ሀገሮች መካከል አድልዖ እንደሚያደርግ ብዙ ጊዜ ታዝቤያለሁ፡፡ የምዕራባውያን ጥቅምና ፍላጎት ሲነካ ቀኑን ሙሉ ብቻ ሳይሆን ሣምንቱንና ወሩን በሞላ በዚያ ዜና ላይ ሲያላዝኑበት ይከርማሉ፡፡ በኢትዮጵያ የሚያልቅ የመቶ ሺህ ሰው ሕይወት በስዊድን በመኪና አደጋ ከሚሞት የአንድ አሟሟቱ ካልሆነ ሞቱ በፈጣሪ ዘንድ ብዙም ሀዘኔታን የማያስከትል ውሻ ሕይወት ይበልጥባቸዋል፡፡ ግነት አይደለም፡፡ ምንም እንኳን እንደዘይና በዳዊ ያሉ ታዋቂ ጥቁር ጋዜጠኞች በእስታፍነት አብረው ቢኖሩም – ቢቢሲዎች ጥቁር ሰው፣ ሰው መስሎ የሚታያቸው አይመስሉኝም ባጠቃላይ፡፡ በኢትዮጵያ የ97 ምርጫ ለምሳሌ ያ ሁሉ ሕዝብ ሲረግፍና የ85 ሚሊዮን ሕዝብ የዲሞክራሲ ሽል ሲጨነግፍ ከሴከንዶች ያለፈ ሽፋን አልጡትም፡፡ በወቅቱ አዝኛለሁ፤ ከአሁኑ ባይብስም፡፡ ሰዎቹ በሽተኞች ናቸው፡፡ በዘረኝነትም ይለከፉ በጥቅምና ፍላጎት ዋናው ባለጌና ደደቦች ናቸው – ልክ የሌለው ደደብነት፡፡ እነዚህ ሰዎች ሠልጥነናል የሚሉ ከሆነ፣ ሃይማኖት አለን የሚሉም ከሆነ በጣሙን ተሳስተዋል፡፡ የሠለጠነና ሃይማት ያለው ሰው፣ ሰው በጠቆረና በቀላ ወይም በኢኮኖሚ ባደገና ባላደገ ብሎ የዜና ሽፋን ቅድሚያና ትኩረት አይሰጥም፡፡ ስለዚህ መንገዱ ያላችሁ ንገሩዋቸው – ፈጣሪንም ኅሊናቸውንም እያሳዘኑ ነው፡፡ የኛስ ግዴለም፡፡ ነጻ በወጣን ጊዜ ነጻ እንወጣለን፡፡ ያኔም የነሱን እውነተኛ ማንነት እንነግራቸዋለን፤ የሚሰሙበት ጆሮ ካላቸው፡፡
የውሸቱ ንጉሥ ኢቲቪ ቢቢሲን ጠቅሶ ከደቂቃዎች በፊት እንደዘገበው፣‹ኢትዮጵያ፣ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ከሚገኙ አራት የዓለም ሀገራት አንደኛዋ ናት፡፡ ይህ ዓይነት ዕድገት የዛሬ ሃያ ዓመት ቻይና ያስመዘገበችው ዓይነት ዕድገት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በምታሳየው ፈጣን ዕድገት ሥራ አጥነት እየጠፋ፣ ሕዝብ ከርሀብና ችግር እየተላቀቀ፣ሀገሪቱ በከፍተኛ ደረጃ በዕድገት እየተመነደገች፣ የትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድ በታሰበው መንገድ እየገሠገሠ … ሊገኝ የቻለው መንግሥት ባመቻቸው የኢንቬስትመንት ዕድል ነው› ብሏል፡፡ በአግራሞትና በድንጋጤ ተውጬ ነው በትግስት የተከታተልኩት፡፡ ሰው ውሸታም መሆን ከፈለገና ኀሊናውን ለጥቅም ከሸጠ ለካንስ የማይዋሽ የውሸት ዓይነት የለም? እንዲህ ተዋሽቶ የሚበላ እንጀራ ደግሞ ገደል ይግባ፡፡ የፈረንጅ ሙሰኛን ታዘብኩ፤ በጣም ያስቀይማል፡፡ የታዳጊ ሀገር ጋዜጠኛ ቢሆን እናዝንለት ይሆናል – ደመወዙ ስለማይበቃው ሊሆን ይችላል ብለን፡፡ ቢቢሲ ግን መቼም በሀገሪቱ የኑሮ ደረጃ የሚበቃቸውን ያህል ሳይከፍሏቸው አይቀሩም – ሰዎች ስንባል በደምሳሳው እምብርት ባይኖረንም፡፡ ታዲያ ወደዚህ ቅሌት ውስጥ ምን አስገባቸው? የተነገራቸውን በጥሬው ምናልባትም ‹ተሞኝተው› አመኑ ብንልስ ከገለልተኛ ወገን ለማጣራት እንዴት አልሞከሩም? ስንት ቢከፈላቸውስ ይሆን ይህን ያህል ርቀት ተጉዘው አንዲት ድሃና በዴሞክራሲ ዕጦት ምክንያት በስደተኞች ብዛት ከመጀመሪያዎቹ አምስት ሀገራት ውስጥ ያለች ሀገር በዓለም በዕድገት ከአራቱ አንዷ ናት ብለው የመሠከሩት? አሁን እኔ ቢቢሲን ለመክሰስ አቅምም ሆነ ችሎታ የለኝም፤ መቼም የሚኖረኝም አይመስለኝም፡፡ ባለችኝ ብቸኛ የጸሎት መሣሪያ ግን ልታገላቸው መብትም ምክንያትና ፍላጎትም አለኝ፡፡ የአቡነ ዘበሰማያት ጦር ደግሞ ለተናቁ ዋና ፍላጻ ነው – ሲወረወር አይታይኝም ሲወጋ እንጂ ይላሉ አባቶች፡፡ በቅንነት ለምንለምነው ፈጣሪ ይስማንና እንደፈቃዱ ያድርግልን፡፡ ዱሮውንም ችግራችን እንዴትና ምን እንደምንጠይቀው በውል አለመረዳታችን እንጂ ‹የነገሩትን የማይረሳ የለመኑትን የማይነሣ› አምላከ ኢትዮጵያ አያሳፍረንም ነበር፡፡ አሁን ግን ግዴላችሁም በየቻልነው መንገድ በቡድንም በተናጠልም እንበርታና ይህችን የጨለማ ዘመን ተባብረን እናንጋት፡፡ የኔን አቅም ከተናገርኩ ዘንድ በውጭ ሀገር ያላችሁና ለሀገሬ እቆረቆራለሁ የምትሉ ወገኖች ይህን መርዘኛ የውሸት ዜና ቢያንስ ለታወቁ ዓለም አቀፍ ተቋማት በያላችሁበትና በተቻላችሁ መጠን አጋልጡ፡፡ ‹ተደጋግሞ የተነገረ ውሸት እንደእውነት ይቆጠራል› ‹አንድ ወሬኛ ያባረረውን ሺህ ፈረሰኛ ጦር አይመልሰውም› መባሉ የወሬን አደገኛነት ለማስገንዘብ ነው፡፡ ለጊዜው በወያኔ ተገዝግዛ በጣር በምትገኘው በእምዬ ኢትዮጵያ ፃዕረ-ሞት ይዣችኋለሁ፡፡ እንዴ? ልጆች የሏትም እንዳታስበሏት አደራችሁን፡፡ ውሸት ገደብ ሊኖረው ይገባል፡፡ ለውሸታቸው ለከት እንዲያበጁለት ንገሯቸው፡፡ የሚያሳፍር ነገር እየሠሩ መሆናቸውን ቢገባቸው አስረዷቸው፡፡
እንዲህ በሉልኝ፡- የሰብኣዊ መብት ተሟጋቹ የኔሰው ገብሬ ብሶቱን ለዓለም ሕዝብ ለማሰማት የገዛ ሕይወቱን ቤንዚን አርከፍክፎ በማቃጠል የተሰዋው፣ ጋዜጠኛ እስክንድንር ነጋና ሌሎች በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ጋዜጠኞች፣ የተቃውሞ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት፣ ተጠርጣሪ የፖለቲካና የኅሊና እሥረኞች በየዘብጥያው የታጎሩትና እየተሰቃዩ ያሉት ይሄን ዕድገት ተቃውመው ይሆን? በሉልኝ፡፡ እነዚያ የቢቢሲ ልማታዊ ‹ጋዜጠኞች› በኢሚግሬሽን ቢሮ አላለፉ ይሆን? በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ኢምግሬሽንን ያጥለቀለቁት ለቱሪስትነት ወደዱባይና ወደአካፑልኮ ቤይ ወደ ሆኖሉሉ ሊሄዱ ይሆን? በእግራቸውና በታንኳ፣ በበረሃና በባሕር ከመሞት መሰንበት ብለው ላያልፍላቸውና የዱር አውሬና የባሕር እንስሳት ቀለብ ሆነው ለመቅረት ከሀገራቸው በእግር አውጪኝ በያቅጣጫው የሚነጉዱትና በየደረሱበት ሞትን ጨምሮ የቁም መከራና ሥቃይ የሚቀበሉት ወገኖቻችን ይህን ‹ፈጣን ዕድገት› ጠልተው ይሆን? በሕዝብ የሚቀልድ ዋጋ ይከፍላል በሉልኝ፡፡ በእርግጠኝነትም ይከፍላሉ፡፡ ‹ቀበጥ አማት ሲሦ ብትር አላት› የሚለውን ብሂላችንን አስረዱልኝ፡፡ ከኢትዮጵያ ወደነሱ የሚተኮስ ምድራዊ አረር የለም፤ ከሰማይ ግን አይቀርላቸውም፡፡ ፍትሕን አስተካካዩ የብርሃን አምላክ የሥራቸውን እንደሚሰጣቸው መጠራጠር የሌለባቸው መሆኑን በሚገባቸው ቋንቋ ግለጹላቸው፡፡
እነዚያን ሌቦች የቢቢሲ ጋዜጠኞች ደግማችሁ እንዲህም በሏቸው፡- ሕንጻ የዕድገት መለኪያ አይደለም፤ ሕንጻ አይበላም፤ አይጠጣም፤ ለሠፊው ጦም አዳሪ ሕዝብ ልብስም መጠለያም አይሆንም፡፡ መንገድም አይበላም – በዕድገት ፍጥነት ከአራቶች ውስጥ የሚያስገባ በቂ መንገድም የለንም፡፡ የግለሰቦች ኩታንኩት ፋብሪካም የዕድገት መለኪያ ሊሆን አይችልም፡፡ አንድ ፋብሪካ ባለቤቱ ቢያንስ አንድ ነው፡፡ ቀጥሮ የሚያሠራቸው ግን ብዙ ድሆች ናቸው፡፡ ያም ቀጣሪ በአብዛኛው ሌባ ነው፡፡ የገዛ ሆዱን እየሞላና በየሣምንቱ ሶደሬና ላንጋኖ በየመንፈቁ አውሮፓና አሜሪካ እየተንሸራሸረ ሠራተኞቹ ግን የራስ ምታት አስፕሪን መግዣ እንኳን እያጡ ጭንቅላታቸውን በእራፊ ጨርቅ ጠምጥመው ነው የርሱን የማይሞላ ከርስ ለመሙላት በላብ እየተጠመቁ በሥራ ሲፈጉ የሚውሉትና የሚያድሩት፡፡ እነዚህ ዘመናዊ ባሪያ ፈንጋዮች የሚሰጡት የእማኝነት ቃል ደግሞ ባብዛኛው ‹የዐይጥ ምሥክር ድንቢጥ› እንዲሉ ዓይነት ነው፡፡ ‹ቦሃ ላይ ቆረቆር፡፡› የዘንድሮው ኢትዮጵያዊ ላይ ሀብታም ኢንቬስተርነት ተደርቦ ይታያችሁ፡፡ የቀን ጉዳይ ነው እንጂ ሁሉንም እናውቀዋለን፡፡ ወያኔን ማን ቀጥ አድርጎ እንደያዘውም ይታወቃል፡፡ ገንዘብ ብቻውን የማያድንበት ጊዜ ደግሞ እየመጣ ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን ሁሉም ዋጋውን ያገኛል፡፡ ዛቻ እንዳይመስላችሁ፡፡ ቀኑ ቀርቧል፡፡ እንዲህ የምንጮህ ወገኖች ደግሞ እንደዮሐንስ መጥምቁ የጽድቅ የክብር አክሊል ለማግኘት አልመን ወይ ተመኝተን አይደለም፤ በጭራሽ! ጨለምተኞች ሆነን ሕዝብን የማስበርገግ ዓላማ ኖሮንም አይደለም – አንዳንዶቻችን እንዲያውም ራሳችን በርጋጎች ነን – በየስርጓጉጡ ተደብቀን እንደዕንቁራት የምንጮህ፡፡ እንደምንም ሆነን እንጩህ – ጩኸታችን ግን ትክክለኛና ተፈጥሯዊ ጩኸት ነው፡፡ ደግሞም ይህን ዕወቁልን – የምንጮኸው የሚታየን ነገር በሉ በሉ እያለ ዕረፍት ስለሚያሳጣን ነው፡፡ አንዳንዶች በሟርተኝነት እስኪፈርጁን ድረስ እንዲህ ተጨንቀን የምናስጨንቃችሁ ለ‹በጎ› እንደሆነ ቁጠሩልን፡፡ አለዚያማ ነገር ዓለሙን ትቶ መተኛትን ማን ይጠላል? … እናም አትዘኑብን፡፡
‹ኢ(ይ)ድኅን ንጉሥ በብዝኃ ሠራዊቱ›፡፡ ንጉሥ በሠራዊቱ ብዛት አይድንም፡፡ ቀድሞ የተነገረ ወንጌላዊ ቃለ ግሣጼ ነው፡፡ በሠራዊት ብዛትና በሀብት ክምችት መዳን ቢቻል ኖሮ ሌሎቹ ሁሉ ቀርተው ‹የዓለምን የገንዘብ ልውውጥ በወርቅ ሣንቲም አድርጌ አውሮፓንና አሜሪካንን በእንትናቸው ቁጭ አደርጋቸዋለሁ!› ብሎ ከመዛቱ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ዋጋውን ያገኘው ሙኣማር ጋዳፊ እስከወዲያኛው በሊቢያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ እንደሸና በኖረ ነበር – እውነቴን ነው ፤ ከሌሎች ቃላት ይህኛው ይቀላል ከሚል ነው እንጂ የርሱ ነገር ከዚያም በላይ ነው፡፡ ጠንቁ ለኛም ደርሶ እንዲያውም ሲያስመልሰው ይደርና ዕድሜ ለመለስ የኛ ወገኖችም በፈላ ውኃ እስከመቀቀል የደረሱበት ዘግናኝ አገዛዝ መሥርቶ ነበር፡፡ ግን ምን ዋጋ አለው የክፉ መጨረሻ ያው ክፉና ክፉ ብቻ ነውና ብድር በምድሩን በውርደት አገኛት – ሲያንሰው ነው፡፡ ብዙዎቻችን ማገናዘብ እየተሳነን እንጂ የዚህች ዓለም እውነት አትለወጥም፡፡ በሠይፍ የገደለ በሠይፍ ይገደላል፡፡ ያሰቃዬ ይሰቃያል፡፡ የገፈፈና የቀማ ይገፈፋል ይቀማልም፡፡ ግና የዱባ ጥጋብ ካለስንቅ እንደሚያዘምት ሁሉ ለጥቂት ዓመታት የምናገኛትን አላፊ ጠፊ ‹ዕድል› ተጠቅመን ጥሩ ታሪክ መተው ስንችል ያችን አለመላው አበለሻሽተን እንዲያውም ዳፋችን ለብዙዎች ይተርፍና አይሆኑ ሆነን እንቀራለን፡፡ የመለስና የመሰሎቹ መጪው ዕድልም ከባሕርይ አባቶቻቸው ከነሣዳምና ከነጋዳፊ የሚዘል አይደለም፡፡ የቀንን ፍርድ የሚያውቅ አደብ ይገዛል – አሁንም ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡ ብዙ አልመሸም፡፡ የሚመለስ ይመለስ፡፡ ‹ጭራሽ ከመቅረት ዘግይቶም ቢሆን መድረስ›(እንደፈረንጆቹ ፈሊጣዊ ብሂል ‘Beter late than never.’) የተሻለ መሆኑን እንገንዘብ፡፡
ለነዚያ የቢቢሲ ጋዜጠኞች ግን አደራ ይህችን ደብዳቤ አድርሱልኝ፡፡ እንርገማቸው፡፡ ዘራቸው ብኑን ይሁን፡፡ ከኔ ደም ተነቅሮ የተሠጣቸውን የመዋሻ ገንዘብ ሳይበሉት ይቅሩ፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ ብድራታቸውን አሁኑኑ ይክፈላቸው፡፡ ጥቁር ውሻ ይውለዱ – እንደነወያኔዎቻችን( እነወያኔዎች ወልደዋልና!እመለስበታለሁ)፡፡ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡ ሕዝቧንም አንድ ያድርግ፡፡
የኢሜል ሣጥኔ ለስድብ ቦታ የለውም – ለገምቢ አስተያየት ግን እነሆ አድራሻየ፡ [email protected]