የዳውሮ ዋካ ህዝብ ከእንባ ወደ አመፅ

ዋካ (ከስዊድን)

ካለፈው አንድ ወር ጀምሮ በደቡብ ኢትዮጵያ በዳዉሮ ዞን በዋካ ከተማና አካባቢው ህዝብ የተቀሰቀሰው ህዝባዊ አመፅ አሁንም እንዳለ ነው። አሁንም ዋካ በወያኔ የመከላከያ ሠራዊት ጊዚያዊ ቁጥጥር ሥር ናት። ይሁን እንጂ ዉጥረቱ አንድ አዲስ ክስተት አስከተለ።

አንድ ሰው እንደሃዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ድምጹን ከፍ አድርጎ እየተናገረ በዋካ አደባባይ ላይ ብቅ አለ። ከሁሉም በፊት ነፃነትና ዴሞክራሲ ለዜጎች!መልካም አስተዳደር ፍትህና እኩልነት በሃገሪቱ ይስፈን ፤ ህዝቡ በተለይ ወጣቱ የአባቶቹን አደራ ይጠብቅ እያለ እያወጀ እየለፈለፈ …. በመጨረሻ በቃኝ ! ፍትህ እኩልነትና ነጻነት በሌለበት ሀገር አልኖርም ሲል ተሰማ በራሱም ላይ ቤንዚል አርከፈከፈ ክብሪትም ለኮሰ ተቃጠለ ….. በሶስተኛውም ቀን ሞተ።

ይህ ስው የኔሰው ገብሬ ይባላል የ29 ዓመት ወጣት መምህር ነበር ። ለመሆኑ ይህ የነጻነት አርበኛ ለምን ሞተ? መነሻውስ ምን ነበር ? ህዝቡስ ለምን አመፀ?የአመጹ መነሻ ታሪክስ ምንድርነው? የህዝቡ ብሶትስ ምንድርነው? በህዝቡ በደልና እንባ ጀርባ የባለስልጣኖች ሚና ምን ነበር? ለመ/ር የኔሰው ገብሬ ህይወት ተጠያቂው ማነው? በሚሉ ጥያቄዎች ዙሪያ ክፍል አንድን በማስቀደም ተከታታይ ጽሁፎች ይዤ እቀርባለሁ።

ይህ ጽሁፌ ለዳዉሮ ዋካ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም በደቡብ ክልል ዞኖች ዉስጥ በተመሳሳይ ያለዉን የከፍተኛ አመራሮችና የመንደር ካድሬዎችን አገዛዝ ሁኔታ እንዲሁም በህዝቡ ላይ የሚያደርሱትን ግፍና በደል ያመላክታል ።ሌሎችም በተመሳሳይ የማጋለጡን ሥራ እንዲሰሩም ያበረታታል።

እንደ መነሻ

በተለያዩ የብዙኅን የህዝብ መገናኛ አውታሮች በሰፊው እንደተገለጸው የዳውሮ ዋካ ህዝብ በወያኔ የግፍ አገዛዝና በደል የተነሳ ታላቅ እንቅስቃሴና አመጽ አድርጎ ሰንብቷል።አመጹ የተቀሰቀሰበት ምክንያት አጋጣሚ የፈጠረው የእለት ክስተት ሳይሆን ። ህዝብ ውስጥ ቆይቶ ሲብላላ የኖረ ፤እንደውጋት ቀስፎ ይዞት ሲያመው የሰነበተ፤እያደረም ህመሙ እየበረታ ሄዶ ሲአስጮኸው ሲአሳዝነውና ሲያስለቅሰው የከረመ ብሶት ነበር ።ለዚህም ብቸኛ አማረጭ ሆኖ ያገኘው አመጽ ሆነ እናም አመጸ።

በደሉ ህዝቡን ተጠናክሮ ለአመጽ እንዲነሳሳ ያደረገው ለመሆኑ ከሚአስተጋባው መፈክር መረዳት ይቻላል።’’ይህ ሥርዓት በድሎናል ! የሚመሩን ግለሰቦች በሙስና በስብሰዋል!በደልን የሚአዳምጥ ጆሮ መንግስት የለውም !ነፃነት ለዳውሮ ዋካ ህዝብ !የበደሉን አመራሮች ይወገዱ !ሥርዓቱ ሥራ አጥ አድርጎናል!…ይህ የጥቂት ሰዎች ድምጽ አልነበረም በዳውሮ ዋካ ከዳር እስከዳር ሲያስተጋባ የከረመ እንጂ ።

ወደ ዝርዝር ጉዳዮች ከማምራቴ በፊት ዳውሮ ዋካ ወረዳ የት እንደሆን ፤ ከእለት ወደ እለት እየጎለበተ ስለመጣው የወረዳው ችግር በመልካም አስተዳደር እጦት የደረሰውን ውጣ ውረድ፣ በስልጣን ወንበራቸው ለመሰንበት ሲሉ ሆድ አደር ግለሰቦች በህዝብ ላይ ያደረሱትን በደል ላስቃኝ።

የዳውሮ ህዝብ የሚገኘው በቀድሞው አከላለል መሰረት በከፋ ጠ/ግዛት በኋላም ክ/ሀገር በኩሎ ኮንታ አውራጃ ውስጥ ሲሆን ጂኦግራፊና የኑሮ ሁኔታ በተመለከተ የዳዉሮ ዞን በ 60 36’ እስከ 7021’ ሰሚናዊ ዋልታ እስከ 36068’ እስከ 370 52’ ምስራቃዊ ዋልታ ዉስጥ የሚገኝ ነው። ዳዉሮ ዞን አብዛኛው የተከበበው በጎጀብና በኦሞ ወንዞች ነው። ከኮንታ ልዩ ወረዳ፣ከኦሮሚያ ጂማ ዞን፣ከከምባታና ሃዲያ እንዲሁም ጠምባሮ ጎፋ ጋር ይዋሰናል። የዞኑ ቆዳ ስፋት 5000 ስ.ኪሜ ነው። በአምስት ወረዳዎች የተከፈለ ሲሆን ወረዳዎችዋም ማረቃ፣ ቶጫ፣ሎማ፣ ጌና ቦሳና እሰራ ይባላሉ። የዞኑ ዋና ከተማ ተርጫ በመባል ይታወቃል። ከተማው በከተማ አስተዳደርና በማዘጋጃ ቤት ይተዳደራል።

የህዝቡ ነሮ የተመሰረተው በእርሻ ላይ ሲሆን ለሥራ ታታሪና በጣም ጠንካራ ህዝብ ነው።የአየሩ ሁኔታ ለኑሮ በጣም ተስማሚ ሲሆን ሁሉም የአየር ንብረቶች ይፈራረቁበታል ።ሁሉም የአዝርዕት አይነቶችም ይበቅሉበታል። እንሰት በአብዛኛው የሚለማበት ሲሆን የህዝቡ አይነተኛ ምግብም ነው።የዳዉሮ ዞን ከ500 ሜ-3000 ሜ ድረስ ከባህር ጠለል በላይ ይገኛል።

የቀድሞው የአውራጃው ዋና ከተማ ዋካ ይባላል።ዋካ ማለት በእግዕዝ ”ብርሃን” ማለት ሲሆን በሃገሬው ሲነገር እንደሚሰማው ለሊት ሲጓዙ ያደሩ መንገደኞች ዋካ ሲደርሱ ፀሐይ ስለፈነጠቀች ብርሃን (ዋካ) ብለው ስም አወጡለት ሲሉ ሌሎች ደግሞ የቀድሞ ገዢዎች የተሰጠ ስያሜ ነው ይላሉ አንዳንዶችም ይህ ስያሜ ከጠላት ወረራ በኋላ የወጣ መጠሪያ ነው በማለት ይገልጹታል ሆኖም የሁሉም አፈ ታሪክ እንጂ ማረጋገጫ አልተገኘለትም።ያም ሆነ ይህ ዋካ ዋካነቷን እንደያዘች ስትኖር የዳውሮ ህዝብም ዋካን ከቦ መኖሩን አላቋረጠም ዳውሮ የሚለው የዳውሮ ቃል ወደ አማርኛ ሲመለስ ጎበዝ ፤ጀግና ፣ አንበሳ ፣ አሸናፊ እንደማለት ነው።

አመፅና የአመፅ መነሻ

የዋካ ከተማ የተቆረቆረችው 1904 ዓ.ም ገደማ በወቅቱ የአውራጃው ገዢ ሆነው ያስተዳድሩ በነበሩት በደጃዝማች ይመኔ እንደነበር ይነገራል።ከተማዋ ስትመሰረት የኩሎ ኮንታ አውራጃ ዋና ከተማ ሆና እንድታገለግል ሲሆን በተለያዩ ጊዜአት ሲፈራረቁ የነበሩ ገዢዎች ከተማዋን በአውራጃነቷ እንድትቆይ አጠናክረዋታል።

ሌሎች 1942 ዓ.ም እና በ1953 ዓ.ም የአውራጃው አስተዳዳሪዎች ሆነው የተሾሙ ደግሞ ለግል ምቾታቸውና ጥቅማቸው ሲሉ ከተማውን ወደሌላ ወረዳና መንደርለማዛወር ሞክረው የህዝብ ተቃውሞ ስለገጠማቸው ዋካ በአውራጃው ርዕሰ ከተማነት እንድትቆይ በማጽናት የህዝብን ጥያቄ ተቀብለዋል።አሁን ግን ወያኔ የሚባል የህዝብን አቤቱታ እሮሮና ለቅሶ የማይሰማ ገዢ ጆሮውን ደፍኖ ህዝቡን በማባዘት ላይ ይገኝኛል።

ወያኔ ከተማዋን የመሰረቷት ነፍጠኞች ናቸው የሚል እምነቱን በማጠናከር አሁን በህይወት በሌሉት ሰዎች ሳቢያ በከተማዋ እና በህዝቡ ላይ የጥላቻ መረቡን በመዘርጋቱ ዋካ አሁንም ትሰቃያለች ህዝቧም የስቃዩ ገፈት ቀማሽ ሆኗል። እጅግ እንትቆረቁዝ ብሎም እንደ እያሪኮ እንድትከስም ነዋሪው በልማት በመልካም አስተዳደር በማህበርያዊ የመንግስት ተቋማት እጦት እንዲቸገር ተደርጓል።በቅርቡም በዋካ ከተማ እንዲሰራ የተፈቀደው ሆስፒታልና ሌሎች የአገልግሎት ተቋማት የዋካ ከተማ የሚለውን ስም እንደያዙ ግንባታቸው ወደሌላ አካባቢ ተዛውሮ እንዲሰራ በዞኑ ባለስልጣኖች በመወሰኑ ህዝቡ ከማእከላዊ መንግስት የተወሰነለትን እንኳን እንዳያግኝ ተደርጓል ዋካ በገዛ ልጆቿ የታነቀች ከተማ ሆናለች ጦሷ ለነዋሪ ልጆቿም ተርፏል።

የደርግ መንግስት ወደ መጨረሻው የአገዛዝ እድሜው በ1981 ዓ.ም ገደማ የሰሜን ኦሞ አስተዳደር አካባቢ የሚባል አዲስ የአስተዳደር ክለላ መዋቅር ዘረጋ የአስተዳደር ክልሉ ከከፋ ክ/ሀገር ኩሎ ኮንታ አውራጃን፤ከሲዳሞ ክ/ሀገር የወላይታ አውራጃንና የገሞጎፋን ክ/ሀገር አንድ ላይ በማካተትና በማዋቀር ዋና ከተማውን አርባ ምንጭ ላይ በማድረግ ተቋቋመ ይህ መዋቅር ለረጅም ጊዜ ሲሰራበት ከቆየ በኋላ የደርግ ስርዓት ሲወድቅ የወያኔ መንግስት ክልል ዘጠን የሚል ስያሜ አክሎበት ዋና ከተማውን ሳይለውጥ ሲሰራበት ቆየ።

በ 1984 ዓ.ም መጨረሻ ክልል ዘጠኝ የሚለው ስያሜ ተለውጦ ሰሜን ኦሞ ዞን ደቡብ ክልል ውስጥ እንዲዋቀር ተደረገ ።የሰሜን ኦሞ ዞን በዋናነት የዳውሮ ፣ የወላይታ ፣ የጋሞ፣ የጎፋ ፣የኮንታ ፣የባስኬቶ ህዝብና እንዲሁም ሌሎች ይገኑበታል። ዞኑ 28 ወረዳዎችን ያቀፈ ሲሆን የወረዳ አወቃቀሩ በ 1987 ዓ.ም በተደረገው የህዝብና የቤት ቆጠራን መሰረት ያደረገ ነው የሚል ማጭበርበሪያ ዘዴና ቅጥፈት በተሞላበት አኳኋን የተሰራ ነበር።

ዋና ዓላማውም ወረዳዎችን ለማጠፍ ሁለት የነበሩትን ወረዳዎች ወደ አንድ ወረዳ ለመከለል እንዲሁም አንዳንድ ወረዳዎችን ለሁለት አጎራባች ወረዳዎች አከፋፍሎ ለመደልደል እና ወረዳው እስከጭራሹ እስከስሙ እንዳይኖር ለማድረግ ነበር።(ለምሳሌ የጌና ቦሳ ወረዳ ለሁለት ተከፍሎ ወደ ሌሎች አጎራባች ወረዳዎች ተደልድሏል)

በዚህም መሰረት ዋካ ከተማን ጨምሮ ስድስት ከነበሩት ወረዳዎች መካከል የዋካ ከተማ በከተማነቱ ሲቀጥል ከአምስቱ ወረዳዎች ሁለቱ ታጥፈው የወረዳው ቁጥር ወደ ሶስት ዝቅ እንዲል ተደረገ ።ይህ ህግ ወጥ የሆነ የመንግስት ውሳኔ ለህዝቡ የማይበጀው በመሆኑ ነውሪውን አስቆጣው የውሳኔውን ጎጂነትና ኢ-ፍታዊነት በመግለጽ ያላግባብ የታጠፈው ወደሌሎች ወረዳዎች ተከፋፍሎ ስሙ የተደመሰሰውም ወረዳ ወደቀድሞው እንዲመለስ ህዝቡ ደረጃ በደረጃ አቤቱታውን አሰማ ።ሆኖም አቤቱታው ምንም አይነት ምላሽ ሳያገኝ ቀረ።

ምንም እንኳን በመላ ሀገሪቱ በሰፈነው በፍትህ እጦትና በመልካም አስተዳደር ብልሹነት ህዝብ እየተጎዳ ያለ መሆኑ ግልጽ ቢሆንም የዳውሮ ዋካ ህዝብ ተስፋ ባለመቁረጥ ጥያቄው ባካባቢው ባለስልጣናት ስላልተጤነለት ጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት ድረስ አበቱታውን አሰማ ። የጠቅላይ ሚንስቱርም ጽ/ቤት የአንድ ወረዳ ጉዳይ ለስልጣኑ ምንም የሚአሰጋ ስላልመሰለው መልስ ሳይሰጥበት ቀረ።

እዚህ ላይ አንባቢ እነሱ እንደከፋፈሉትና እንደአጠፉትስ ቢሆን ምን ጉዳት ያስከትላል የሚል ጥያቄ ስለሚያነሳ አወቃቀሩ የሚአስከትለውን ችግር በመጠኑ ማስረዳት አስፈላጊነት ያለው ይመስለኛል።ለምሳሌ ወደ ዞኑ ዋና ከተማ ወደ አርባምንጭ ለስራ ጉዳይ ለመሄድ ያሰበ አንድ ግለሰብ ከኮንታ ልዩ ወረዳ ርዕሰ ከተማ ከአመያ ተነስቶ ሲጓዝ በመዋል ጅማ ያድራል ከጅማ እንደገና ወደ አዲስ አበባ ተጉዞ እዛም ያድርና በማግስቱ አርባ ምንጭ ይደርሳል ።

ይህ ጉዞ በግምት ወደ 980 ኪሎ ሜትር ነው ይሄ እንግዲህ ሲኬድ ብቻ ነው መመለሱም ያንኑ ያህል ጉዞና አዳር አለው ይህ ሁሉ የሚሆነው ደግሞ በአንድ ዞን ውስጥ ነው ለግል አቤቱታ የሚሄደውንም ምን ያህል መጉላላትና ወጪ እንደሚደርስበት መገመት አያዳግትም በመንግስት የስራ ጉዳይ በመንግስት መኪና የሚጓጓዘውም ቢሆን መጉላላቱ እንኳን ባይታሰብ ያለው ወጪ ብዙ ነው የነዳጅ፣የባለስልጣኑና፤የሹፌሩ አበል ሌላም ተጨማሪ ወጪና ድካም …

ችግሩ በዚህ መልኩ አይን አውጥቶ እየታየ እያማረረና እያስለቀሰ እራስን ደልሎ በሚነገረው ሰበካና ውሸት ተሸፋፍኖ መቀመጡ የማይቻልና ፎቅ የማያሰኝ ሆነ ይልቅዬም በ1992 ዓ.ም አካባቢ የሰሜን ኦሞ ዞን ለአስተዳደር ከተማነት በፍጹም የማይቻልና የማያመች እንደሆነ በሁሉም ዘንድ ታመነበት ይሄን ጥያቄ ህዝብ አንስቶ አቤቱታውን በድጋሚ አሰማ አሁንም የአስተዳዳሪዎቹ መልስ የዞኑ የአስተዳደር ከተማነት ምንም አስቸጋሪነት የለውም፤አንድ ህዝብ ስለሆንን በዞን መከፋፈል አያስፈልግም! በጋራ ስትሆኑ ትለማላችሁ፣ በአስተዳደር አንድ መሆን የበለጠ ይጠቅማችኋል የሚል ደረቅ ስብከት ሆነ።

በአስተዳደር በደል ታፈኖ እንጀቱ እየቆሰለ ለቆየው ህዝብ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የአንደኛ ደረጃ የትምህርት ቋንቋ በአፍ መፍቻ ቋንቋ እንዲሆን የወጣው መመሪያ ደግሞይበልጥ ሆድ አስባሰው አስቆጣው ሊላ ቀውስም አስከተለ።ለመሆኑ ይሄ የታሰበው ሶስትና አራት ቋንቋዎችን በአንድ ላይ ቀጥቅጠው ወይስ አንድ ላይ በጥብጠው ሊያመጡት ይሆን ያሰቡት? ? ይህ የቋንቋ ፍብረካ ችግሩን እጅግ ከማወሳሰቡም በላይ የሰሜን ኦሞ ህዝብ የዞኑን ሹሞች ይቅርና ዋናውን የወያኔን መንግስት እያስጨነቀው እየወጠረው መጣ።

እራሳቸው በፈለጉበት ጊዜ እንደግል ቡሉኮቸው ዞንም ሆነ ወረዳን የሚአጥፉትና የሚዘረጉት የደቡብ ክልል መንግስት የበላይ ጠባቂ የሆኑት የክለላው መሃንዲስ ፈላጭ ቆራጩ የህወሀት ካድሬ ቢተው በላይ ጉዳዩን በፈለጋቸው መንገድ እንዳይፈቱት ድሮ የሰረቁበት ፋይል ይመዘዝ ወይም አዲስ ዝርፊያና ወንጀል ይስሩ አይታውቅም በሙስና ተዘፈቁ ተብለው ዘብጥያ ከወረዱ ከረሙ የሉም።

የህዝብ ጥያቄ ወደ ጎዳና ላይ ሰልፍ እየተቀየረ መጣ ተማሪዎች አንማርም አሉ መምህራን ይህ ቋንቋቸው አይደለም እንኳንና ተማሪዎች እኛም የጻፍነውን ማንበብ እያቃተን ነው ወጋጎዳ የሚባል ቋንቋ የለም አሉ። መመሪያ ሰጥተው እንዳያስቆሙ አሁንም አቶ ቢተው የሉም ወይኒ ቤቱን እያሞቁ ነው ችግር ሆነ።

የተቀጣጠለው የህዝብ አመጽ እንደተናቀው አልነበረም ትንሽ ውሃ ተደፍቶበት የሚጠፋ ሳይሆን ፣ጭሱ ሽቅብ ወጥቶ የመንግስትን ዓይን ወጋ ።በተለይ ወላይታ ላይ የተንቦለቦለው እሳት ወደ ሌሎቹም አካባቢዎች ተሸጋገረ ዋካ ታመሰች አርባምንጭ በጭንቅ ተወጠረች ሳውላ ዓይናቸው በደፈረሰ በተቆጡነ ዋሪዎቿ ተጥለቀለቀች ትምህርት ቤቶች ተዘጉ አድማ አስነስታችኋል የተባሉ ከየቦታው እየተመዘዙ ታሰሩ አመጹ በዚህም አልተገታም ህዝባዊ እምቢተኛነቱ እየቀጠለ ሄደ…

መከላከያ ሰራዊት እና ፍጥኖ ደራሽ በማሰማራት ማሰርና ማፈን ለህዝብ ጥያቄ መፍትሄ መስሎ እሚታየው የወያኔ መንግስት አመጹ በዚህ ሊገታለት አልቻለም ነገሩ ከቁጥጥሩ ውጪ ሆነበት የህዝቡን ጥያቄ የግድ የመመለስ እንደሚገባው የሚአምንበት ሰዓት ላይ ደረሰ እናም የተካነበትን የማጭበርበርበሪያ ካርድ መዘዘ …

ካድሬው ግጥሙን ዜማውንም ቀይሮ ብቅ አለ ….”መንግስታችን ከህዝብ ጥያቄ በመነሳት ከፍተኛ ጥናት አድርጎ በሰሜን ኦሞ ዞን የመዋቅር ለውጥ ለማድረግ ወስኗል …. ” ሌላው ማደናገሪያ ሃተታ ስንተወው የተጣራው የካድሬው ንግግር ይሄ ነበር ”ቢቸግራት ሞተች” ይሏችኋል ይሄ ነው ትምህርት ቤቶች ተዘግተው ህዝቡን እንዲነሳሳ ቀስቅሳችኋል የተባሉ መምህራንና ሌሎች ሰራተኞች ታስረው ስንት መስዋዕትነት የተከፈለበትን ጉዳይ ወያኔ መቋጭያ ሲያጥረው በጥናትና በህዝብ አበቱታ ፈቀድኩላችሁ ማለቱ እጅግ አስገራሚ ክስተት ነበር።

ያም ሆነ ይህ የሰሜን ኦሞ ህዝብ ትግልና ቆራጥነት የወያኔን መንግስት ስለአርበደበደው ውጥረቱን ለማለዘብና ከቁጥጥሩ ውጪ የሆነበትን ጉዳይ ለማርገብ ሳይወድ በግድ የህዝብን ጥያቄ ሊቀበል ችሏል።በዚህ እልህ አስጨራሽ ትግል ላይ የወላይታ ህዝብ የከፈለው መስዋዕትነት እጅግ የላቀ በመሆኑ ታልቅ ክብር ሊሰጠው ይገባል ።

የዞኑ ውጥረት በዚህ መልኩ ተረጋግቶ ሰሜን ኦሞ ዞን በሶስት ታታላቅ ዞኖች (ዳውሮ ፣ ወላይታ፣ጋሞ ጎፋ )በሁለት ልዩ ወረዳዎች ( ኮንታ፣ ባስኬቶ)ተከፈለ።በዚህ ሂደት የዳውሮ ዞን ከሰሜን ኦሞ ተለይቶ ራሱን ችሎ እንዲዋቀር ተደረገ።

እንግዲህ በዚህ ፅሁፍ ዳውሮ ዋካ የሚባለው አካባቢ የት እንደሚገኝ የዋካን ከተማ አመሰራረት በቀድሞ መንግስታትና በዘመነ ወያኔ የተከተለውን የአወቃቀር ሥርዓት እንዲሁም የሰሜን ኦሞን ዞን አወቃቀርና አከሳሰም ለማሳየት ሞክሬያለሁ ።

በሚቀጥለው ክፍል ሁለት ጽሁፌ ደግሞ የዳውሮ ዋካ ህዝብ ላይ የወረዳ አከላለልን ምክንያት በማድረግ ባለው ሥርዓት የደረሰበትን በደል ፤ ማህበራዊ ተቋማት ህዝቡ ካለበት ቦታ እንዲርቁ በመደረጋቸው የተከሰተውን ችግር እንዲሁም የቀድሞው የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የዛሬው ምክትል ጠ/ሚ/ር ተብዬ በህዝቡ ላይ ያደረሰውን ግልጽ ተፀዕኖ የሚያመለክት ፅሁፍ ይዤ እስክቀርብ በሰላም ያክርመን።