ወያኔ ነባር የከተማ ቦታ ይዞታዎችን ወደ ሊዝ ለማዞር ያወጣው አዋጅ የከተማ ነዋሪዎችን ለፖለቲካ አላማ ጭሰኛ የማድረግ እቅድ እንዳለው ተገለጸ
የከተማ ቦታን በሊዝ ለማስያዝ በሚል ድንጋጌ የወያኔ ምክር ቤት በቅርቡ ያወጣው የከተማ ቦታ አዋጅ የዜጎችን ነባር ይዞታ ለመቀማት የታሰበና ባለንበርቶች ቤታቸውን ለልጅ ልጆቻቸው ለማውረስ ያላቸውን ህጋዊ መብት የሚያሳጣ እንደሆነ በተለያየ ደረጃ የሚገኙ የህግ ባለሙያዎች ገልጸዋል።
ኢ-ፍትሃዊ የነበረውን የአገራችንን የመሬት ይዞታ ስርዓት በ1967ቱ ስርነቀል የመሬት ላራሹ አዋጅ የለወጠው ደርግ ፤ የከተማ ቦታን በምሪት የመጠቀም መብት ሰጥቶ ዜጎች ያላንዳች ፍርሃትና መሸማቀቅ አቅማቸው የፈቀደውን መኖሪያቤትና ንግድ ድርጅት ሲገነቡበት እንደቆዩ የገለጹት የህግ ባለሙያዎች፤ ይህ የአሁኑ የወያኔ አዋጅ ቀደም ሲል በምሪት የተያዙ ቦታዎችን ጭምር በመቀማት ወደ ሊዝ ስምሪት የሚከትና በዚህም የተነሳ ነባር ይዞታዎች ላይ ዜጎች የነበራቸውን ዋስትና የሚያሳጣ ነው ብለዋል።
አዲሱ የከተማ ቦታ አዋጅ፤ ነባር ይዞታዎች ወደሊዝ እንዲዛወሩ በግልጽ ደንግጎ እያለ፤ አዋጁ በህብረተሰቡ ውስጥ የቀሰቀሰውን ተቃውሞ ለማብረድ ሲባል የወያኔ የከተማ ቦታና የኮንስትራክሺን ሚንስቴር መኩሪያው ሃይሉ በአለቃው መለስ ዜናዊ ታዞ፤ አዋጁን ሙሉ በሙሉ በሚቃረን መንገድ እርስ በርሱ የሚጣረስ መግለጫ መስጠቱ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው። አዋጁ እንደ ታወጀ ነባር ይዞታዎችን ወደሊዝ የማዛወሩ ተግባር እስከ 5 አመት ጊዜ ሊወስድ ይችላል ብሎ የነበረው መኩሪያው ሃይሉ ባለፈው ሳምንት በወያኔ ቁጥጥር ሥር ባለ የኤፍ ኤም ሬዲዮ ቀርቦ፤ ቀደም ሲል የሰጠውን ቃል ሙሉ በሙሉ በማጠፍ አዋጁ ነባር ይዞታን እንደማያካትት ለመናገር ሞክሮአል። የወያኔው ሹመኛ መኩሪያው ሃይሉ የሰጠው የተምታታ መግለጫ የሚያመለክተው፤ ከአቅም በላይ የሆነው የኑሮ ውድነትና የመልካም አስተዳደር ጉድለት በፈጠረው የውስጥ ለውስጥ ህዝባዊ ተቃውሞ ላይ ተጨማሪ ነዳጅ በመሆን የህዝብ ቁጣ ሊቀሰቅስ ይችላል ተብሎ ስለተሰጋ ህዝብን ለማረጋጋት የተዘየዴ እንደሆነ ውስጥ አዋቂ ምንጮች ይናገራሉ።
ወያኔ በመላው አገሪቱ የገጠር መሬት ላይ የሚኖሩትን ዜጎች የራሱ ጭሰኛ የሚያደርግ ፖሊሲ በማውጣት አገዛዙን የማይደግፉትን ለዘመናት ከኖሩበት ቄያቸውና የእርሻ ማሳቸው እያፈናቀለ፡ የፖለቲካ ድጋፍ ለሚሰጡትና በካድሬነት ለሚያገለግሉት ሲሰጥ እንደኖረ የሚናገሩ የፖለቲካ ተንታኞች፤ በዚያ እፍትሃዊ አሰራር የገጠሩን ህዝብ ምርኮኛ አድርጎ የፖለቲካ ድጋፊ ማግኘት የተሳነው የትግራይ ገዢ ጉጂሌ፤ ይባስ ብሎ ምንም አይነት የድጋፍ መሠረት በሌለው የከተማ ክልል ነዋሪዎች ላይ ይህንን አዲሱን አዋጅ በማወጅ በቀጥታ ጭሰኛው ለማድረግ ፈልጎና አቅዶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ያመለክትላ ይላሉ።
ወያኔ ስልጣን ከተቆጣጠረበት 1983 ጀምሮ እስከ ምርጫ 97 ድረስ በነበሩት አመታት አብረውት ከጫካ ለመጡት አብዛኛው የህወሃት ታጋዮች የከተማ ቦታን በነፍሰ ወከፍ ሸንሽኖ በስምሪት ያስያዘ እንደሆነ ሲታወቅ፤ በተለይ በወታደራዊ መኮንንነት ስልጣን ላይ ለመደባቸው የትግራይ ተወላጆች በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ 500 ካሬሜትርና ከዚያም በላይ ቦታ በስምሪት በማከፋፈል፤ የቤት መስሪያ ገንዘብና አሸዋ የሚያመላልስ የመንግሥት ጭነት መኪና በመመደብ አዳዲስ ባለሃብት እንዳደረጋቸው ይታወቃል። ይህ የአሁኑ አዋጅ አፈጻጸም እነዚህን አዳድስ ባለሃብቶች ያካትት አያካትት ለጊዜው የታወቀ ነገር ባይኖርም ፤ ባለፉት 20 አመታት በተደረገው የአገር ሃብት ዘረፋና በሙስና በተገኘ ሃብት አብዛኛው የወያኔ ሹሞች ተሳታፊ በመሆናቸው፡ ይፈጸምባቸዋል እንኳ ቢባል አሁን ከያዙት በተጨማሪ ሌሎች እጥፍ ቦታዎችን በሊዝ የራሳቸው ለማድረግ የሚያስችላቸው የገንዘብ አቅም አላቸው ተብሎ ይታመናል።
የዚህ የአዲሱ አዋጅ ዋናው አላማም በአገራችን የነበሩትን ነባር ሃብታሞችና የከተማ ቦታ ባለ ይዞታዎችን በአዳዲሶቹ የወያኔ ከበርቴዎችና ደጋፊዎቻቸው በመተካት ለዘመናት የፖለቲካውን ሥልጣን ለመቆጣጠር ያለው የረጂም ጊዜ ዕቅድ ወጤት አካል እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ።
የግንቦት 7 ድምጽ የአገር ሃብትን ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር በማዋል ዜጎችን በገዛ አገራቸው ለዘመናት ባሪያ አድርጎ ለመግዛት እያሰሬ ያለውን የወያኔ አገዛዝ በተባበረ ትግል ለመጣል የሚደረገውን ትግል ሁሉም የአገሪቱ ዜጋ እንዲቀላቀል ጥሪውን ያቀርባል።