ትኩረት በሳይበር ለሚደረገው ትግል!!!

ባለንበት የመረጃ ዘመን፤ ሳይበር (ለምሳሌ ኢንተርኔት) ለፍትህ፣ ለነፃነትና ለዲሞክራሲ ትግል ከሚደረግባቸው አውድማዎች አንዱ ሆኗል። ለሰሜን አፍሪቃና መካከለኛ ምሥራቅ ህዝባዊ አብዮቶች ኢንተርኔት ስለተጫወተው ሚና ብዙ የተባለ ስለሆነ እዚህ ላይ ደግሞ ማንሳት አያስፈልግም። መረሳት የሌለበት ሃቅ ግን አምባገነኖችም ይህንን ስለሚያውቁ እነሱም የሚዘጋጁበት መሆኑ ነው። የዘመናችን አምባገነን መንግሥታት የምድር፣ የባህርና የአየር ኃይሎቻቸውን ከማፈርጠም ጎን ለጎን “የሳይበር ኃይላቸውን” ማጎልበት የሥራቸው አንድ አካል አድርገውታል። ሳይበር የስለላ ስራዎቻቸውን የሚያቀላጥፉበት መስክ ከሆነ ውሎ አድሯል።

የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝም “ለሳይበር ጦርነት” በርካታ ሠራዊትና በጀት እንደመደበ ለግንቦት 7 የሚደርሱት መረጃዎች ያረጋግጣሉ። መለስ፣ መደበኛ ሥራቸው የሬድዮና የቴሌቪዥን ሞገዶችን ማወክ፤ ለዲሞክራሲ ወገንተኛ የሆኑ ድረገፆችን መዝጋት፤ በግለሰቦች ኮምፒዩተሮች ውስጥ የተቀመጡ ፋይሎችን መስረቅ፤ የግለሰቦችንና የድርጅቶችን የኤሌክሮኒክስ ፓስታዎችን (ኢሜሎችን) መጥለፍ እና የመሳሰሉ እኩይ ተግባራትን ማከናወን የሆነ በርካታ “ባለሙያዎችን” አሰማርቷል።

ለዚህ ምላሻችን ምንድነው?

በውጭ አገራት ያሉ ኢትዮጵያዊያን በፓልቶክ የመወያያ ክፍሎች፣ በድረገፆች፣ በዩ ቱዩብ እና  ፌስ ቡክ አማካይነት ስለአገራቸው ጉዳዮች ሲወያዩና መልዕክቶችንም ሲያስተላልፉ ቆይተዋል፤ አሁንም በማስተላለፍ ላይ ናቸው። በዚህ ረገድ ሊወደሱና ሊበረታቱ የሚገባቸው ፓልቶኮች፣ ድረገፆችና ፌስ ቡኮች አሉ። ሆኖም ግን የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ከሚያደርስብን ጥቃት እና ለነፃነታችን ማድረግ ከሚገባን አንፃር ሲታይ እስካሁን  እየተደረገ ያለው ጥረት እጅግ አነስተኛ ሆኖ እናገኘዋለን።

ግንቦት 7፡ የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በሁለገብ ትግል የሚያምን በመሆኑ የሳይበሩን “አውድማ” በቸልታ አያይም። በሳይበር የሚደረገው ትግል የአጠቃላይ ትግላችን አንዱ አካል ነውና በተጠና እና በተደራጀ ሁኔታ መመራት አለበት ብሎ ያምናል።

እንደ ማንኛውም የትግል መስክ “የሳይበር ጦርነትም” የተጠና ስትራቴጂ፣ ሰውና ድርጊት ይፈልጋል። እናም ራሳችንን በእነዚህ ሶስት አቢይ ምሰሶዎች አንፃር መመርመር ይገባናል ብሎ ግንቦት 7 ያምናል።

የኢሌክትሮኒክስ፣ የኮምቲዩተርና የሶፍት ዌር እውቀት ያላቸው ለነፃነትና ለፍትህ የቆሙ ኢትዮጵያዊያን የሚከተሉትን ጥያቄዎች አንስተው፣ ተወያይተውባቸው ምላሽ ቢሰጧቸው እና ተግባራዊም ቢያደርጓቸው ትግላችን ጉልህ በሆነ መንገድ ያግዛሉ ብሎ ግንቦት 7 ያምናል።

ስትራቴጂን በተመለከተ

  • በሳይበር ከሚደረግ ትግል ማግኘት የምንችለው ውጤት  ምንድነው?
  • እምንፈልገው ግብ ለመድረስ ምን ዓይነት አማራጭ መንገዶች አሉን?
  • የሳይበር ትግል ከሌሎች የትግል ዓይነቶች ጋር እንዴት ይቀናጃል?
  • በሳይበር ዘርፍ የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ምንድናቸው?

ሰውን በተመለከተ

  • በሳይበር ትግል የሚሳተፉ ወገኖቻችን እንዴት ቢደራጁ ይሻላል?
  • እንደምን ያለ አደረጃጀት ነው ለዚህ የትግል ዘርፍ ይበልጥ ውጤታማ የሚሆነው?
  • ባለሙያዎችን ወደዚህ የትግል ዘርፍ ለመሳብና አዳዲስ ባለሙያዎችን ለመፍጠር ምን ማድረግ እንችላለን?

ድርጊትን  በተመለከት

  • በሳይበር ዓለም ውስጥ እንዲደረግ የምንፈልገው ተግባር ምንድነው?
  • እያንዳንዱ “የሳይበር አርበኛ” ጊዜውንና እውቀቱን ሰውቶ ውጤት በሚያመጣ የሳይበር ተግባር ላይ እንዲያተኩር ምን ማድረግ ያስፈልጋል?
  • እቅዶቻችን በሥራ ላይ መዋል አለመዋላቸው እንዲሁም የምንፈልገው ውጤት ማምጣት አለማምጣታቸው እንዴት መከታተል እንችላለን?
  • የተናጠል ሙከራዎችን እንደምን ማቀናጀት እንችላለን?

የሚሉና ተመሳሳይ ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽ ሊያገኙ ይገባል።

የመለስ ዜናዊ አገዛዝን የኢንተርኔት አፈናና ስለላ ከመቋቋም ጀምሮ የአፀፋ ምላሽ እስከመስጠት የዘለቀ በሳይበር ግንባር መከወን ያለባቸው በርካታ ተግባሮች አሉ። አደረጃጀቱ ይለይ እንደሆነ እንጂ እንደሌሎቹ የትግል ዘርፎች ሁሉ መደራጀት በዚህም ግንባር ወሳኝ ነው።

ስለሆነም የኤሌክትሮኒክስ፣ የኮምፒዩተርና የሶፍትዌር እውቀትና ዝንባሌ ያላቸው ወገኖቻችን ጊዜያችሁ እና እውቀታችሁ ትግሉን በሚያግዙ ተግባራት ላይ እንድታውሉ፤ ሥራዎችንም በተደራጀና በተቀናጀ  መንገድ እንድትሠሩ ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ጥሪ ያደርጋል። ለዚህ ተግባርም ባለሙያዎች ተሰባስባችሁ የምትመክሩበት መድረክ በአስቸኳይ እንድትፈጥሩ ግንቦት 7 ወገናዊ ጥሪ ያቀርብላችኋል።

እውቀታችንና ጊዜያችንን አስተባብረን ከተነሳን የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ የሚፈጽመፈውን የሳይበር አፈና ከመቋቋምም አልፈን የአፀፋ ምላሽ መስጠት እምንችልበት ደረጃ ላይ መድረስ እንችላለን ብሎ ግንቦት 7  ያምናል።

አፈና በተገኘበት መስክ ሁሉ እንዋጋዋለን፤ ትግላችን ሁለገብ ነው!!

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!