ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ
ከዮሐንስ እ፡ ተመስገን
ከሰሞኑ በአሜሪካ ውስጥ በሚገኘው የቻይና ኤምባሲ በጥቂት ኢትዮጵያውያን የተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ያለቦታው ጉልበት ግዜና መዋዕለ ንዋይ የማባከን ሁኔታ ሆኖ ነው የታየው::
ተቃውሞው ኢሳትን ለማፈን ቻይና ቴክኖሎጂ ለኢትዮጵያ መንግስት ሸጠች በሚል ሲሆን ያንን ጉልበትና ግዜ ያላቸው ወገኖች ተቃውሞአቸው ለትልቁ የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት ለሆነው አምባገነን መንግስት የደም ማዘዋወሪያ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር የአሜሪካ ግብር ከፋይ ብር በየአመቱ በሚለግሰው የአሜሪካ መንግስት ላይ የተነጣጠረ ቢሆን በተሻለ ነበር።
ይኄው የአሜሪካ መንግስት በአንድ በኩል ሰብዓዊ መብትና ዲሞክራሲ እያለ ሲለፍፍ ወደ ሰማኒያ ሚሊዮን የሚጠጋውን የኢትዮጵያ ህዝብ ስቃይ መከራና የሰብዓዊ መብት ረገጣ አይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ በመሆን እንደ መለስ አይነት በዓለም በዕኩይነታቸው ከተፈረጁት አምባገነን መሪዎችን የስልጣን እድሜ ለማራዘም አቅፎና ደግፎ ላይ ታች እያለ ነው። ጥቅም እንጂ ሰብዓዊ መብት፣ ዲሞክራሲ ወይም የሰው ልጅ ጣዕርና ዕልቂት ምኑም ያልሆነው የአሜሪካ የውጭ ፖሊሲና የዚሁ ፖሊሲ አራማጅ መሪዎቹ ወደ አንድ ሚሊዮን የተጠጋ ህይወት የጠፋበትን የሩዋንዳ የእርስ በርስ ፍጅት ዳር ሆነው ሲያዩ ዓለም እንዳልታዘበ በነዳጅ ክምችት ሃብቷ የምትታወቀውን ኢራቅ በሀሰት ውንጀላ መውረር ለሚለፍፉት ዲሞክራሲ ሰብዓዊ መብት ወይም ለሰው ልጅ ያላቸው ተቆርቋሪነት በወረቀታቸው ላይ እንደሰፈረው ሳይሆን ከጥቅም በኋላ ያለ እንደ አስፈላጊነቱ የሚነሳ እንደ ምክንያት የሚጠቀሙበት ገንዘብ መፍቀጃ ወይም ማዕቀብ መጣያ ከባሰም መውረሪያ ዱላ ነው::
ከአሜሪካ ህዝብ በግብር ከሚሰበሰብና ካቋቋሟቸው ተቀጥላ የገንዘብ ድርጅቶች አይ ኤም ኤፍና ዎርልድ ባንክ በየግዜው ገንዘብ በመላክ የኢትዮጵያን ህዝብ ስቃይ እንዲራዘም ምክንያት የሆነውን ትልቁን ባለጋራ ትቶ ቻይና ላይ መዝመት አህያውን ፈርቶ ዳውላውን ይመስላል::
ለቻይና ኤምባሲ በአሜሪካ የተደረገው የተቃውሞ ሰልፍም ቀዳሚና ክብደት ሊሰጠው የሚገባው አልነበረም:: ኤምባሲዋ ላይ በምናደርገው ተቃውሞ ሰልፍ የአሜሪካን ሚዲያ ስበን ፖለቲካ እንሰራበታለን ከሆነም አሜሪካ ከቻይና ባለባት የትየለሌ የብድር አረንቋ አፏ ስለተሸበበ እንደቀድሞ ድምጽ የምታሰማበት ሃይሏ የተወሰነ ነው:: ይልቁንም ለሌላ ሀገር ጥቅም ለማስጠበቅ የቆመው (የኛ) ሀገር ሻጭ መሪ ተብዬ አሜሪካንን ማስፈራሪያ ቻይናን እንደሽጉጥ እየተጠቀመ ገንዘብ ከናንተ ያለዚያ ቻይናን አምጥቼ ከናንተ እገላገላለሁ ሲል ነው አይ ኤም ኤፍና ዎርልድ ባንክ ይህን ያህል ገንዘብ ላኩለት እየተባለ የሚታዘዙት::
በሌላ በኩል ቻይና ዲሞክራሲና ሰብአዊ መብት ለዕድገት አሉታዊ ወይም አዎንታዊ ተጽዕኖ የላቸውም በሚል የተቀረጸው ፖሊሲያቸው የኛ ተቃውሞ ሰልፍ የድርጊት ማስተካከያ መነሻ ሊሆን የማይታሰብ ነው:: ቻይና ለተቃውሞ ሰልፍ ያላትን አቋም በቲያናንሜን ስኩዬር ላይ ለአለም ያሳየችውን አስከፊና አሳዛኝ ሁኔታ እስከዛሬ ትክክል ነው ብለው የሚሟገቱ መሪዎቿን ልብ ለማራራት ሰልፍ ከመውጣት የተዘበራረቀና የተከፋፈለ ኅይላችንን በማሰባሰብ የኢትዮጵያን ህዝብ ከስቃዩ ሊያላቅቁ በሚችሉ ቅድሚያና ክብደት በሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ ብንሰራ የተሻለ ነው እላለሁ። ለኛ ችግር መፍትሄ የምንሆነው እኛ እንጂ አሜሪካ አውሮፓ ወይም ቻይና አይሆኑም:: ሁሉም የየራሳቸው ችግሮች አሉአቸው።
የጠለቀ ጉድጓድ ውስጥ ተቀምጠን አይደለም አውጡን ብለን የምንጣራው:: ያለንን ዘዴ ጉልበት ፍላጎት ሃይልና ጥረት ደምረን ለመውጣት በምናደርገው ትንቅንቅ ላይ ወጥተን ለመቆም የቀረን ትንሽ ሲሆን የአጋዡ መበርከት በሰልፍ እስኪታይ መበርታት እንጂ እዚያው ጥልቅ ጉድጓድ ሆነን የሰው ያለህ ብንል ዛሬ እንደሚታየው ሀገሩ እየተቆረሰች ለምትሸጥበት ወገን በረሃብ ለሚታመሰውና የሰውነት መብቱ ተገፎ ከመኖር በታች ከሞት በላይ ላለው የኢትዮጵያ ህዝብ ማንም ሊደርስ አልቻለም:: የተማረውም በየውጭ ሀገሩ የሚባዝነውም በጋራ ሀገርን የመታደግ ሃሳቦችና ድርጊቶች ላይ ተስማምቶ ሊሰራ የሚችልበትን ሜዳ ለማመቻቸት እንኳን አልታደለም: ወደዋናው ርእስ ስንመለስ የኢሳት መታፈንን ከግምት ያለማስገባት ወይም በህብረተሰብ ውስጥ ሚዲያ ያለውን የጎላ ድርሻ ለማሳነስ ሳይሆን ቀዳሚ ነገሮችን የበለጠ ውጤት ሊያመጡ በሚችሉና ከስእሎቹ ትልቁን በማየት መስራት ይገባናል ለማለት ነው ሃሳቡን ያነሳሁት፡፡ ለመሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ከምንለው ሰማኒያ ሚሊዮን ውስጥ ስንቱ ነው ቴሌቪዥን ያለው? በቅርብ ባነበብኩት አንድ African Media Development Initiative ዘገባ ላይ 2% ህዝብ ነው የቴሌቪዥን ባለቤት:፡ ማለት 1.6 ሚሊዮን የተጠጉ ቴሌቪዥኖች ለሰማንያ ሚሊዮን ህዝብ :: ከዚህ ቁጥርስ ስንቱ ነው በሳተላይት ሪሲቨር በመታገዝ ኢሳትን የሚያየው? በዚሁ ዘገባ ላይ የአንድ ቴሌቪዥን አማካይ ዋጋ $420 ሲሆን 12 ሚሊዮኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ከውጭ በሚመጣ የእህል እርዳታ እየኖረ ሌላው 75 ሚሊዮን ህዝብ ከ ሁለት ዶላር በታች በቀን እየኖረ በ420 ዶላር ቴሌቪዥን ስለመግዛት ቀርቶ ስለ ማየት ማሰቡ እጅግ የሚያጠራጥር ነው:: ሰርቶ በልቶ መኖር ለተሳነው ህዝብ መብቱ ተረግጦ ለሚሰቃየው ህዝብ መሰረታዊ ችግሮች ስለሚወገዱበት መነሳትና ባለው መንገድ ሁሉ መታገል መሰለፍ ይበጃል ወይስ በሀገራችን ሁሉ ሞልቶ ተትረፍርፎ በየጓዳ ጎድጓዳው ቴሌቪዥን ለሁሉም ያለን ይመስል እንደ ትልቅ አጀንዳ ቴሌቪዥን እንዳናይ መንግስት አፈነን ማለትና ሰልፍ መውጣት? ይህስ የቀዳሚና ተከታይ ሁኔታዎችን ለመለየት የተሳነው አላዋቂ አያሰኘን ይሆን? ውስጣችንን ከኛ በላይ አሳምረው የሚያውቁት የአሜሪካ የአመራር ሰዎችስ በኛ የቴሌቪዥን ጥያቄ ሰልፍ ምን ያህል ተገርመው ይታዘቡን? የኢትዮጵያ ህዝብ ማለትስ በየከተማዎቹ ያለው እጅግ አናሳ ቁጥር ህዝብ ይሆን? ቻይናስ ያመረተችው ማፈኛ መሳሪያ ከተመረተበት ፋብሪካ መጋዘን እንዲቀመጥ ይሆን የተሰራው? እንደ መለስ ዓይነት ደንበኞች ከአሜሪካ ለእርዳታ በተሰጠው ገንዘብ ሊገዙ ቢፈልጉ ገዢውን ትተን ገንዘብ ሰጭውን ትተን ሻጩን መኮነን ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ የሚያሰኝ ድርጊት እንዳይሆን ማስተዋል ይበጃል::
ዮሐንስ እ፡ ተመስገን [email protected]
ኦገስት 04 -2010