አጣሪ ኮሚቴው ወደ ሐዋሳ ተጉዟል


(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 22/2010፤ ጥቅምት 12/2003 ዓ.ም):- የሐዋሳውን ችግር ለመፍታት ቃል በተገባው መሠረት አጣሪ ኮሚቴው ዛሬ ሐዋሳ ከተማ ገብቷል። በ12 የሕዝብ ማመላለሻ አውቶብሶች እንዲሁም በሚኒ ባሶች እና የቤት መኪናዎች ተጭኖ የመጣው ቁጥሩ ከ700 በላይ የሚሆን የሐዋሳ እና አካባቢው ሕዝበ ክርስቲያን በብዙ ደጅ ጥናት መልስ ሊያገኝበት ያልቻለውን የአቡነ ፋኑኤልን ጉዳይ ለአንዴም ለመጨረሻውም ለማከናወን ወደ አዲስ አበባ መምጣቱን መዘገባችን ይታወሳል። በተደጋጋሚ ስንዘግብ እንደቆየነው ምእመናኑ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ይህ ለ4ኛ ጊዜያቸው መሆኑ ነው። ነገር ግን ጠቅላይ ቤተ ክህነቱም ሆነ ቅዱስነታቸው ችግሩን ሳይፈቱ ይልቁንም ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል በድንዳኔያቸው እንዲቀጥሉበት የበለጠ ዕድል ሲሰጣቸው ቆይተዋል። ሊቀ ጳጳሱ እንዲያገለግሉት የተሾሙለትን ሕዝበ በማስመረራቸው እየገፉ ከመሔዳቸውም ባሻገር ለሕዝቡ ያላቸውን ንቀት በአደባባይ ሳይቀር ማሳየታቸውን ቀጥለዋል። የሐዋሳ ምእመን በድጋሚ የመጣው ጉዳዩ መስመር ስቶ ወደ አላስፈላጊ መንገድ ከመግባቱ በፊት የመጨረሻ አቤቱታቸውን ለማሰማት ነበር።
 

ቅዱስነታቸውም “ነገ ጠዋት (ማለት ዛሬ አርብ) ወደ ሐዋሳ አጣሪ ኮሚቴው ይላካል” ያሉ ሲሆን ይኸው የአጣሪ ኮሚቴ ወደ ሐዋሳ የመሔድ ጉዳይ ከንግግር ባለፈ እስካሁን ተግባራዊ ሳይሆን መቆየቱን ሐዋሳውያኑ አስታውሰዋል። “ቅዱስ አባታችን፤ እውነተኛ አባት ይስጡን” ያለው የሐዋሳ ምእመን ችግሩን በዚሁ መፍታት ካልተቻለ “ከእንግዲህ ድጋሚ አንመጣም፤ በሰላም ይለያዩን (ከአቡኑ ጋር)፤ አሁን እርሶ ችግሩን መፍታት ስላልቻሉ መነጋገር የምንፈልገው ከቅ/ሲኖዶስ ጋር ነው” ማለቱም ተሰምቷል።  በመጨረሻም አጣሪውን ኮሚቴ ዛሬ አርብ ለመላክ በመስማማት ውይይቱ የተፈፀመ ሲሆን ሕዝበ ክርስቲያኑም ወደ ሐዋሳ በሰላም ተመልሷል። እንደተባለውም ኮሚቴው ዛሬ ወደ ሐዋሳ ለመንቀሳቀስ ችሏል።