አቶ መለስ እና በጨለማ መተኮስ (በሳ.ግ.)

ሰሞኑን በአንድ የአፍሪካ አገር በሚታተምና በዋናነት አፍሪካ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በሚያተኩር www.Africareview.com የተባለ ድረ ገጽ ላይ የወጣ ዜና ርዕስ ስቦኝ ከፍቼ ውስጡን አነበብኩት። ርዕሱ እንዲህ ይላል፦ “Is Ethiopian strongman Meles Zenawi shooting in the dark?”. [i]ማለፊያ ርዕስ ነው። አይነ ግቡ ነው፤ የጽሁፉንም የመከፈት እና የመነበብ ዕድል ከፍ እንደሚያደርገው ግልፅ ነው። ርዕሱ በአቀራረብ ለዛው ጠያቂ ቢሆንም ከምንም ነገር በላይ ግን በጣም ገላጭ እና እውነትነት ያለው ሆኖ አግኝቼዋለሁኝ።  አዎን አቶ መለስ ዜናዊ አሁን፣ አሁን ወደር በሌለው ጋጠወጥነት(hubris)ከፊት እየመሩ ራሳቸውንም፣ የሚመሩትንም ቡድን ሆነ አገሪቱን የከተቱበት የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ አዘቅት ሊወጡት የሚችሉት እንዳልሆነ  ዛሬ፣ ዛሬ ፍንትው እያለላቸው የመጣ ይመስላል።

 

ፖለቲካው በራሱ ለከት በሌለው ቁጥጥር እና በአድርባይ ሆድ አደሮች ሆይሆይታ ስልጣንን አረጋግቶ መግዛት ይቻል ይመስል በአብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ አዶ ከበሬ ዛሬ ላለበት ከአንድ ብሄር የበላይነት ወርዶ የቤተሰብ ጉባዔ ደረጃ ከደረሰ ሰነበተ። በሚመሩት ቡድን ውስጥም ቢሆን የባለቤታቸው የወ/ሮ አዜብ ጎላ ከልክ ያለፈ የስልጣን እና የኢኮኖሚ ስግብግብነት እና ስድነት ብዙ ነባር ታጋዮች ብለው የሚጠሯቸውን አባሎቻቸውን ደም እያፈላ ያለ እና ምን አልባትም ለሌላ የፖለቲካ ቀውስ መነሻ ከፍተኛ የመሆን እድል እንዳለው የሚደርሱን መረጃዎችም የሚወስዷቸውም ቅጥ ያጡ ተከታታይ እርምጃዎች ያሳብቃሉ። ከቡድናቸው ሰንሰለት ውጪም ቢሆን በአገሩ የስልጣን ባለቤት መሆን ሳይችል ይኸው ለዘመናት አንድ ባለብረት አምባገነን በሌላ ባለብረት አምባገነን እየተተካ ሲገፋ እና ሲረገጥ የኖረው አገር ወዳዱ እና ፍትህ ናፋቂው የሰርክ ህዝብ(Everyday Ethiopians) በሌሎች አገሮች በተደረጉ የመብትን ከጨቋኝ ጉልበተኞች  መዳፍ ላይ በአብዮታዊ ንቅናቄ መንጭቆ የመውሰድ ጥበብ ተነቃቅቶ እንደምን አድርጎ መብቱን እና ነጻነቱን ከአቶ መለስ እና ቤተሰቦቻቸው መውሰድ እንደሚችል እያሰላሰለ ያለበት ወቅት ላይ መሆኑ በራሱም ሌላ እንቅልፍ የሚነሳ ጉዳይ ነው።

 

ኢኮኖሚውም ቢሆን ለከት በሌለው የዱቤ ኢንቨስትመንት[ii](deficit spending) እና ሌሎች ተዛማች መዋቅራዊ(structural) ችግሮች ተተብትቦ መረን የለቀቀ የዋጋ ግሽበት አዙሪት ውስጥ ገብቶ ዛሬ፣ ዛሬ አቶ መለስም ቢሆኑ ሽምጥጥ አድርገው ይክዱት የነበረውን ገደብ የለሽ የገንዘብ ፍሰትን(Excessive Money Supply) ጨምሮ  ብዙ ነገሮችን እያመማቸውም ቢሆን ማመን የጀመሩበት ሁኔታ ላይ ነው ያለነው። ለከት ያጣው የዋጋ ግሽበት ከጥቂት አመታት በፊት በማዕከላዊው የገቢ መደብ ላይ ይቀመጡ የነበሩ ጥሩ ገቢ ያላቸውንም ዜጎች ጭምር የሰርክ ኑሮ ድባቅ ያስገባ እና ማቆሚያም ያጣ በሚመስል መልኩ ወር ከወር እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ ሲሄድ አልታይ ካለ ይኸው ብዙ ወራት አሊያም አመታት ተቆጠሩ። ያለልክ ለታይታ እና የፖለቲካ ታማኝ ሊሆን የሚችል ጥገኛ ሚድል ክላስ(middle class) ለመፍጠር ተብሎ በአብዛኛው ከባንክ በዘር እና በፖለቲካ ትሥሥር በተወሰደ ገንዘብ በየቦታው የተሰደሩት ብልጭልጭ ፎቆችም በቀጣይ ሊመጣ የሚችለውን ፈረንጆቹ የሪልስቴት አረፋ (realestate bubble)[iii] ብለው የሚጠሩትን የኢኮኖሚ ኹነትም አይቀሬነት አሳይ ናቸው። ምን አልባትም ከሰሞኑ መንግስት በድንገት ያወጣው የከተማ ቦታን የመሬት ስሪት ከስር መሰረቱ የሚቀይር አዋጅ የዚህ ትርምት መምጣን ለማዘግየት ታስቦ ይመስላል። እንደዚህ አይነት የኢኮኖሚ ውሳኔ ውጤቶችን እንዴት አድሮጎ ሊያዘገይ ወይም ሊያስቀር እንደሚችል ግልጽ ባይሆንልኝም።

 

በዲፕሎማሲው ዘርፍም ቢሆን  አቶ መለስ ያልቀፈሉት፣ቃል ገብተው ቃላቸውን ያላጠፉበት፣ ያልዋሹት እና ያልወሸዱት የውጪ አገር መንግስትም ሆነ የሲቪክ ቡድን የለም። እንደ ማሳያ በግልጽ በአደባባይ በራሳቸው ሚዲያ ጨምሮ እንዲሁም በዊኪሊክስ በዝግ ስብሰባ እንዼት ቃል እየገቡ እነደሚቀጥፉ ማየት ለፈለገ ሰው ዛሬ፣ ዛሬ የሚቸግር ጉዳይ ስላይደለ ዝርዝሩን ለአንባቢ ልተወው። ነጭ ካፒታሊዝም ነው የምንከተለው፣ ዲሞክራሲ እና መድበለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርዓት አማራጭ ሳይሆን እንደ ህዝብ ለመቀጠል ብቸኛው ዋስትናችን ነው፤ እንከን የለሽ ምርጫ አደርጋለሁ ፤ስልጣኔን በዚህኛው የምርጫ ዘመን መጨረሻ እለቃለሁ፤ ተቀናቃኞቻቸውን በግፍ አስረው በአንድ አንድ መንግስታት እና የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ቡድኖች ሲጠየቁ ደግም በቶን የሚለካ መረጃ አለን ፤ በሰዓታት ሊለኩ የሚችሉ የምስል እና የድምጽ ማስረጃዎች አሉን፤ ኋላ ላይ ሁሉም ቢከፍቱት ተልባ እንደሆነ እኛም አየን ሌሎችም አዩት። አቶ መለስ ያልዋሹት እና ያልሸወዱት ሰው ዛሬ፣ ዛሬ ያለ አይመስለኝም። በዚህ ላይ ግን በአንድ ወቅት እውቁ አሜሪካዊው ምሁር [iv]ፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን በአንድ ወቅት አቶ መለስ ከአጭበረበሯቸው በኋላ በጻፉት ጽሁፍ ላይ መጠቆማቸውን በአግራሞት ማንበቤን አልዘነጋም። ማንበብ ለፈለገ የጽሁፉን አገናኝ ሊንክ ከታች አስቀምጬዋለሁኝ ። በኢትዮጵያ ላይ ሊመጣ በሚችል ለውጥ ላይ በዋናነት ገንቢ ሚና ይጫወታሉ የሚል የዋህ እምነት ባይኖረኝም ምዕራባዊ መንግስታትም ቢሆኑ አሁን፣ አሁን አቶ መለስ ቀን ከቀን እያሳፈሯቸው በመምጣታቸው እሳቸውን መከላከል የቀነሱ ይመስላል። ለዚህም ነው አቶ መለስ የቻይናን ቀሚስ አጥበቀው እየያዙ ያሉት። ይህም እርምጃ ቢሆን በምዕራባዊያን የስልጣን ኮሪደሮች ላይ ከራሳቸው ራስወዳድ ጥቅመኝነት አንጻር መዝነውት ሊሆን ይችላል እንደወትሮው በቸልታ ሊታይ የማይችል ጉዳይ መሆኑን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በወጡ የተለያዩ ጽሁፎች እና ሰሞኑን በዋሽንግተን ዲሲ የተደረገው የሴኔት ውይይት ላይ አይተናል።

 

በቡሃ ላይ ቆረቆር እንዲሉ ዘመን አመጣሽ የመረጃ መለዋወጫ ቴክኖሎጂዎች ምንም እንኳን እስካሁን በተደራጀ መልኩ በስፋት ጥቅም ላይ ባይውሉም ጋዝ፣ ጋዝ በሚል ባዶ ፕሮፖጋንዳ ሲታሽ ለሰነበተው ኢትዮጵያዊ ዜጋ የዶሮ ቤት መስኮት ብታህልም አማራጭ መረጃዎችን ማየት የሚችልበት እድል ያገኘበት ጊዜ ነው። ይህ መረጃ የማግኘት፣ መረጃን የመሰብሰብ፣ የማስተላለፍ እና የማሰራጨት እድልም እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ ሊሄድ እንደማይችል በየወሩ በሚገርም ፍጥነት እየጨመረ ያለውን የኢትዮጵያውያን የፌስቡክ እና ሌሎች የማህበራዊ ድረገጾች ተጠቃሚነት ቁጥር በማመሳከር መገንዘብ ይቻላል። (ይህ እውነታ በቀጣይ ስልጣን ላይ እንጠላጠላለሁ ለሚሉ ሌሎች የዋሆችም  ጭምር በማስጠንቀቂያነት ሊታይ ይገባዋል።) በሌላም በኩል ለድሮው በጣም ተበጣጥቆ በተናጠል ይደረግ የነበረውን የፖለቲካ ተሳትፎ እና የዲሞክራሲ ጥያቄ እንቅስቃሴ አያስኬደንም ብለው ያመኑ በቁጥር ጥቂት ሊባሉ የሚችሉ ትጉህ ኢትዮጵያውያን የብዙሃኑን አቅም በማስተባበር የሳተላይት ቴሌቪዥን እና ሃያ አራት ሰዓት የሚሰራ የሬዲዮ ስርጭት እንዲሁም የአጭር ሞገድ የሬዲዮ ስርጭት በመክፈት የመረጃ ፍሰቱን እና ውይይቱን እያሳለጡ መሆኑ የአቶ መለስን የመረጃ ፍሰት ሞኖፖሊ ወትሮም በተዳከመበት በውጪው አለም በዋናነት፤ በኢትዮጵያ እና በአካባቢው ደግሞ በፍጥነት በሚያድግ የስርጭት ተደራሽነት ክፉኛ ማዳከሙ እና አሁን ካለበትም በላይ የሳቸውን የፕሮፖጋንዳ ሚዲያዎች ተደማጭነት ድባቅ ሊከት በሚችል ፍጥነት እድገት ማሳየቱ አቶ መለስንም ሆነ እሳቸው እራሳቸው በጋዜጣዊ መግለጫ  እንዳመኑት በራሳቸው የቀጥታ ትዕዛዝ የሚሰራው የአፈና እና የፕሮፖጋንዳ መዋቅር መሃንዲሶችን ሳያስደነግጥ የቀረ አይመስልም። የመረጃ መፍሰሻ አማራጮቹም አይነት እና ብዛት መጨመር እንዲሁም በተከታታይ አፈና እና የስርጭት ሞገድ አፈና የተፈጸመባቸው የሚዲያ ተቋማት በእጅ አልሰጥም ባይነት አማራጭ መንግዶችን በቁርጠኝነት እየቀየሱ መቀጠል መቻላቸው በራሱ ሌላ የስጋት እና የጭንቀት መሰረት የሆነ ይመስላል። አማራጮቹ ሲበዙም የማፈን አቅም ስለሚገደብ ለአፈና እጅግ አስቸጋሪ እየሆነ መሄዱም አይቀርም።

 

ከላይ ያሉትን አንቀጻት የጻፍኩት ለዚህ ዋንኛ እና ለዛሬው ጽሁፌ መነሻ ለሆነኝ አንቀጽ መንደረደሪያ እንዲሆነኝ ነው። የጽሁፌ መነሻ ምክንያት ደግሞ በዕለተ ሃሙስ በንጹሃን ጋዜጠኞች፣ በሰላማዊ የተቃውሞ ፖለቲከኞች እና በራሳቸው በአቶ መለስ ግፊት በስደት በሚኖሩ ጋዜጠኞች እና የተቃውሞ ፖለቲካ መሪዎች ላይ ያወረዱት የመደበኛ የክስ ሂደት መልክ ያለው በይዘት ግን ሰውየው ለየለት ወይ የሚያሰኙ የክስ አንቀጾችን የያዘውን የክስ ቻርጅ ከአነበብኩ በኋላ ገርሞኝ ነው። ልብ ብሎ ላስተዋለ በእለተ ሃሙስ ያዥግደጎዱት የክስ መዓት በአብዛኛው መጀመሪያው አንቀጽ ላይ እንደጠቀስኩት ጽሁፍ ርዕስ የእውር ድንብር በጭለማ የመተኮስ ያህል ነው:: አቶ መለስ ነገሮች ተደራርበው እንቅልፍ  የነሷቸው ይመስላል። በቀጥታ አስረው የሰላም እንቅልፍ መተኛት ይችሉ ዘንድ እንቅልፍ የነሳቸውን ነገር ማወቅ ይፈልጋሉ። ግን ነገሮችን ከአጭሯ አፍንጫቸው አርቀው ማሰብ አይችሉም እና የችግራቸውን ውስብስብነት እና ጥልቀት የተገነዘቡት አልመስለኝም። ጥቂት በአገር ቤት ያሉ ፍጹም ሰላማዊ የፖለቲካ ተቀናቃኞችን እና ጋዜጠኞችን በማሰር ይቅርና የአይኑ ቀለም አላማረኝም የሚሉትን እና ከርሳቸው ጋር በፍጹም ሊስማማ አይችልም የሚሉትን አብዛኛውን የሰርክ ኢትዮጵያዊ ማዕከላዊ እና ቃሊቲ ግዞት ቢሰዱትም ችግራቸው እንዲህ በቀላሉ ሊሸፈን ወይም ሊታለፍ የማይችል ስር የሰደደ ነው። ለጊዜው ግን እንደ አማራጭ የወሰዱት በጭለማ መተኮሱን ነው:: ከፊት ለፊታቸው ያገኙትን ማሰር፣ ማዋከብ እና ማሰቃየት።

 

እነኚሁ አዳዲስ ብቅ ብቅ ባሉት ጋዜጠኞችና የሚዲያ ተቋማት የሚያቀርቧቸው የዜና፣ የምርመራ ዘገባ እና የ ቃለመጠይቅ ስራዎች አፍ የሚያስከፍቱ እና ይበል የሚያሰኙ መሆናቸው በባዶ ፕሮፖጋንዳ እና የውሸት ካባ ታጅሎ ላለው የመለስ መንግስት መደንገጥ ምክንያት ቢሆን አይገርምም። የኢያሱ በርሄ አሟሟት ላይ የተሰራው የምርመራ ጋዜጠኝነት ስራ የብዙሃንን ቀልብ ስቧል። የወ/ሮ አዜብ ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚችል ከተራ ጥርጣሬ በዘለለ መልኩ በምስል፣ በድምጽ እና በመረጃ ተቀናብሮ መቅረቡ ለአመታት በተከመሩ ወንጀሎች እና የዘረፋ ታሪክ ሸክም ስር ለሚኖረው የአቶ መለስ መንግስት በጣም ከፍተኛ ስጋት ሆኖ ቢገኝ አይደንቅም። ሌሎችም እስከ ዛሬ ድምጻቸውን ያልሰማናቸው ግሩም ኢትዮጵያውያን ከያሉበት በቃለ መጠይቅ ታሪካቸውን እና ሃሳባቸውን በአየር ሞገድ እና በቴሌቪዢን መስኮት ማካፈል መቻላቸው በባዶ ሜዳ ሁሉን አዋቂ ነኝ ለሚሉት ችኮው አቶ መለስ ከፍተኛ የቅናት ምንጭ እና እንደውም በሳቸው ላይ እንደተሰነዘረ የግል ጥቃት አድርገው ሊያዩት እንደሚችሉ የሰውየውን የኋላ ታሪክ በማየት መገንዘብ ይቻላል። አቶ መለስ በጣም በሚገርም ደረጃ ቂመኛ እና በቀለኛ ግለሰብ ነው። አቶ አበበ ገላውን እና አቶ ፋሲል የኔ አለምን ስለምን መክሰስ አስፈለጋቸው። አበበ በሆድ አደርነት ለአቶ መለስ አገልጋይ ከሆነ ሁለት አስርተ አመታትን ያስቆጠረውን [v]አቶ ተስፋዬ ሃቢሶን ሞላጫ ሌብነት ጀምሮ የዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሜሪላንድ የሽብርተነት ዳታ ቤዝን በርብሮ የአቶ መለስ አባት ድርጅት ህወሃት የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያውያን ንጹሃን ዜጎች ላይ ባደረሰው የሽብር ጥቃት በተደጋጋሚ በሽብርተኝነት የተመዘገበ ድርጅት መሆኑን አሳወቀን፤ ፋሲል ደግሞ ወ/ሮ አዜብ መስፍን በጥቅም ግጭት ወይም በፖለቲካ ምክንያት በታዋቂው የትግሪኛ ዘፋኝ እና በኋላም ቱባ ነጋዴ በነበረው [vi]አቶ ኢያሱ በርሄ ሞት ላይ እጃቸው ሊኖርበት እንደሚችል ጠቋሚ የሆነ ግሩም የምርመራ ጋዜጠኝነት ስራ መስራቱ ፎቶዋቸውን በትልልቅ ፖስተር ለጥፈው አምልኩን እያሉ ላሉት አቶ መለስ በጣም ሊያሸብራቸው ቢችል ሊገርም አይገባም። አቶ ኦባንግ ሜቶስ ቢሆን እንዴት አድርጎ ይሆን አሸባሪ የሆነው?? ይኸው ለአመታት ሳውቀው ከአገር አገር ያለመታከት እየተጓዘ በዋናነት በነ አቶ መለስ እና መሰሎቻቸው ባመጡት የዘር፣ የፖለቲካ እና ሌሎችም ውስብስብ ምክንያቶች ተራርቆ ያለውን ኢትዮጵያዊ ዜጋ ለማሰባሰብ መስራቱ ይሆን በአሸባሪነት ያስፈረጀው።

 

የአዋጆችእና መመሪያዎችን መንጋጋት፤ የሚከሰሱትን ሰዎች አይነት እና ስብጥር፤ የአንዳንዶቹ ተከሳሾችም ሙያም ሆነ የህይወት አካሄድ ምንም ሊገናኙ የማይችሉ መሆን እንዲሁ ሲቀጥልም ሶስቱ ተከሳሾች(እኔ በግል እስከማስታውሰው ድረስ አቶ ብርሃኑ ነጋ፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ እና አቶ መስፍን አማን) ከዚህ በፊት ሞት የተፈረደባቸው መሆኑ ነገሩን ሁሉ ግብታዊ እና በጭለማ መተኮስ  ያስመስለዋል። የነገሮችን ሂደት(trend) በቅጡ ላስተዋለ አቶ መለስ በቀጣይነት በብዛት በጨለማ መተኮስ መቀጠላቸው አይቀሬ ነው። በጨለማ በግብታዊነት የሚተኩስ ሰው ደግሞ ለሚተኮስበት ሰው ብቻ ሳይሆን በተኳሹ ዙሪያ ላሉትም ቢሆን በጣም አደገኛ ስለሆነ በጊዜ ግብታዊ ተኩሱን እንዲያቆም ሊመከር እና ሊነገረው ይገባል። የጨለማ ተኩሱ በጊዜ ካልተገታ ግን ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ጠንቋይ መቀለብ የሚያስፈልገው አይመስለኝም።

 


[i] http://www.africareview.com/Special+Reports/Ethiopia+prime+minister+Zenawi+on+edge/-/979182/1265358/-/6jek9bz/-/

[ii] http://cablesearch.org/cable/view.php?id=09ADDISABABA2763&hl=%27ethiopia+deficit+spending%22

[iii] http://cablesearch.org/cable/view.php?id=07ADDISABABA3483&hl=real+estate+bubble+ethiopia

[iv] http://www.ethiopianreview.com/content/444

[v] http://www.ethiomedia.com/andnen/2576.html

[vi] http://www.youtube.com/watch?v=FQ5EolNsx5Y