የየካ ክፍለ ከተማ የቀድሞ ወረዳ 12 ነዋሪ የኢህአዴግ የልማት ኮሚቴዎች የጠሩትን ስብሰባ ረግጠው ወጡ

ነዋሪው የስብሰባውን አዳራሽ ጥሎ ለመውጣት የተነሳሳው፤በአዲሱ የመሬት ሊዝ አዋጅና በመሬት ይዞታ ማረጋገጫ፣የክፍያ ስርዓትና ባለይዞታዎች በካሬ ሜትር እንዲከፍሉ በተተመነው ገንዘብ ጉዳይ ላይ ለመወያየት ጥያቄ አቅርበው ከመድረክ መላሽ በመነፈጉ ምክንያት ነው፡፡

ዕሁድ ሕዳር 3 ቀን 2004 ዓ.ም በየካ ክ/ ከተማ የቀድሞ ወረዳ 12 ነዋሪ፤ከፈረንሳይ ኤምባሲ ዝቅ ብሎ የሚገኘው ፈረንሳይ መናፈሻ የስብሰባ አዳራሽ ከጠዋቱ 2 ሰዓት ከ30 ጀምሮ በመንገድ ልማት ጉዳይ ላይ ለመወያየት የተደረገለትን ጥሪ አክብሮ የተገኘ ቢሆንም፤ከውይይቱ መጀመር በፊት ነዋሪው የመሬትና የሊዝ፣እንደዚሁም የይዞታማረጋገጫ ጉዳይ በአጀንዳ ተይዞ መክክር አንዲደረግበት ጥያቄ በማቅረቡ ውዝግብ ሊፈጠር ችሏል፡፡ የተፈጠረውን ውዝግብ ለመፍታት የመድረኩ መሪዎች ብርቱ ጠረት ቢያደርጉም ለውይይት የታደመው ነዋሪ ከልማት በፊት የመሬት፣የሊዝና የመሬት ክፍያ አፈፃፀም ጉዳይ ይቅደም . . . እያለ በማስቸገሩ ውዝግቡ ተካሮ ለስብሰባ ከተጠራው ሕዝብ መካከል አብዛኛው አዳራሹን በቁጣ ለቆ በመውጣት ቅያሜውን ገልጿል፡፡

ነዋሪውን ሕዝብ ለመንገድ ልማት መዋጮ አስፈላጊነት እንዲወያይ ጠርተውት የነበረው የየካ ክ/ከተማ የልማት ጉዳይ ድ/ቤት ተጠሪዎች በሁኔታው የተደናገጡ ቢሆን በአዳራሹ ከቀረው ነዋሪ ጋር ያካሄዱት ልማት ነክ ውይይትም “ሕዝቡ መዋጮ የመስጠት አቅም ላይ አይደለም . . .” የሚል ጠንካራ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል፡፡ “ሕዝቡ በአብዛኛው በጡረታና በድጎማ የሚኖር፣ባለፈው ሥርዓት በውትድርና ሙያ አገሩን ሲያገለግል የነበረና በአሁኑ ወቅት የተረሳ በመሆኑ የገዛ ኑሮውን እንኳን ለማቃናት የተቸገረ ነው፡፡ እንደዚሁም ሆኖ ከዚህ በፊት ጤና፣ለትምህርት፣ለኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋት፣ለዓባይ ግድብ ወዘተ እየተባለ የአቅሙን ያህል አዋጥቷል፡፡ የመንገድ ልማት ጉዳይንም በተመለከተ ያላዋጣበት ጊዜ የለም፡፡ ነገር ግን ይሰራል የተባለው መንገድ አልተሠራም፡፡ እንደገና ዛሬም ለመንገድ መዋጮ መክፈል ግዴታው መሆኑን ቢያውቅም የተሰራ መንገድ ግን የለም፡፡ እንደዚህም ሆኖ ለአካባቢ ልማት ያለውን ከመስጠት አልቦዘነም፡፡ ይሁን እንጂ አሁን ለመሬት ካርታ የተጠየቀውን ከፍተኛ ገንዘብ ለመክፈል
አቅም የለውምና በዚህ በኩል መንግሥት አስተያየት ሊያደርግለት ይገባል” በማለት አንደኛው ተሰብሳቢ የመድረክ መሪውን በመጠየቅ ነዋሪው ሕዝብ ያለበትን ችግር እግረ መንገዳቸውን አንጸባርቀዋል፡፡ዋናው የመሬት ጉዳይ ውዝግብ በፈጠረበት የሕዳር 3 ቀን 2004 ዓ.ም ስብሰባ ላይ፤የመሬት የዞታ ማረጋገጫ ደብተር ወጥቶላቸው እንዲወስዱ የስም ዝርዝራቸው በየቀበሌው ከተለጠፈ የየካ ክፍለ ከተማ 8ሺህ ነዋሪዎች መካከል 2ሺህ ሰዎች ብቻ ወደ የቀበሌው ጽ/ቤት በመቅረብ ስለተጠየቁት ገንዘብ ከፍተኛ መሆን አቤቱታ ማሰማታቸውን ከ 2 ሺዎቹ መሀከልም የተተመነላቸውን ክፍያ ለመፈጸም ፈቃደኛ የሆኑት በጣም ጥቂት እንደሆኑ፣የተቀሩት ክፍያው በጣም እንደበዛባቸውና ሊቀነስላቸው እንደሚገባ ጥያቄ ማቅረባቸውን፣ከነዚህ ውጪ የሆኑት 6 ሺህ የክ/ ከተማው ነዋሪዎች ግን ወደ የቀበሌው ዝር ለማለት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን . . . የክ/ከተማው ተወካይ በዕለቱ ለልማት ጉዳይ ለተሰበሰበው ሕዝብ ግልጽ አድርገዋል፡፡

ምንጭ