የኢትዮጵያ ሰማይ ምን አርገዟል? (ተሻለ መንግሥቱ)

አጭር መልእክት መጻፍ አሰኘኝ – ደካክሞኝ ልተኛ ስል። ከበፊትም የነሱና የኛ ታሪኮች መመሳሰል በጣሙን ያስደንቀኝ ነበር። የነሱና የኛ ችግር ተቀራራቢ እንደሆነ በተለይ ካለፉት ስምንትና ዘጠኝ ወራት ወዲህ እነሱ እየደረሰባቸው በሚገኘው የጭፍጨፋና የግድያ የሰቆቃ ኑሮ  መገንዘብ ችያለሁ – የሁለታችንም አሳዳሪ ጌቶች ክፉኛ ጨካኞች ናቸው – ተወዳዳሪ የማይገኝላቸው። እነሱ እንደሕዝብ በጣም ጠንካሮች ናቸው። እኛ ግን የነሱን የብቃት ደረጃ ለማግኘት ገና በውል ያልተገለጠልኝ  የጊዜ ርዝማኔ የሚያስፈልገን ይመስለኛል። እነሱ የማይቀርላቸውን የታሪክ ዕዳ እየተወጡ ናቸው።

 

እኛ ግን ቋቱ አልሞላ ብሎ የተቸገርን ይመስል ሞልቶ መፍሰስ ከጀመረ ከሃያ ዓመታት ለበለጠው የመከራና የግፍ ዘመን ተመቻችተን እንደተቀመጥን አለን። ይሁን – ካመጣው ምን ይደረጋል? አንዳንዱ ቋት እንደሽንቁር በርሚል ሞላ ሲሉት እየጎደለ ለተወሰነ ጊዜ ማስቸገሩ ጥንትም ነበር። እንደተቀደደ ሳይበጅ ወይም ሳይጠገን የሚቀር የግፍ ቋት ግን ኖሮ አያውቅም። በሰባ ዓመትም፣ በዐርባ ዓመትም፣ በሠላሳ ዓመትም፣ በሃያ ዓመትም፣ እንደየሁኔታው ከነዚህ ከጠቀስናቸው የጊዜ አጥቆች በላይም ሆነ በታች ለሚረዝምና ለሚያጥር ጊዜ ብዙ ሕዝቦች የመከራ ገፈት ሲጋቱ ቆይተው በመጨረሻው ግን ነጻ መውጣታቸውን ታሪክ በተለያዩ አጋጣሚዎች አረጋግጦልናል – ሂትለር፣ ሙሶሊኖ፣ቻውቼስኮ፣ሣዳም፣ ጋዳፊ… ጥቂቶቹ ናቸው፡፡

 

ይህ ሲባል ግን እንደተኛን እንክረም የኛን ሥራ በኮንትራት ወይም በ‹ፓርታይም› ለውጪ ሠራተኞች እናሠራው(out source)  ለማlት እንዳልሆነ ልብ ይሏል። ‘አብናቶቼና ወንድምቶቼ’ ሆይ! – ባለቤት ካልጮኸ ጎረቤት አይረዳም። የጮኹ ተጠቀሙ – ያልጮኹ ወይም በቅጡና ሥርዓት ባለው አዋጭ መንገድ ያልጮኹ  በገዛ መንግሥቶቻቸው እንደእባብ ራስ ራሳቸውን ተቀጠቀጡ። ልዩ የታሪክ አንጓ! የመንን እንመልከት፤ ባሕሬንን እንመልከት፤ ሱዳንን እንመልከት፤ ኢራንን እንመልከት፤ ጆርዳንን እንመልከት፤ ኢራቅን፣አፍጋኒስታንን፣ፓኪስታንን፣በተለይ ግሪክንና ጣሊያንንና መላው አውሮጳን፣አሜሪካንን፣ ናይጄሪያን፣ ኢትዮጵያን … በእውኑ በአሁኑ ወቅት የመከራ ጥንስስ የማይንተከተክበት፣ የዕልቂት ድግስ ብፌ ያልተዘረጋበት የዓለም ሀገር አለን? እነመምሩ ‹ያድኅነነ እመዓቱ፣ ይሠውረነ በምሕረቱ በእንተ ማርያም ወላዲቱ…› የሚሏትን ጥዑመ ዜማ ማመልጠን አሁን ነበር። ክፉ ጊዜ እየመጣ ነው – በተለይ ለኢትዮጵያና በኢትዮጵያ!!!! (ብዙ ሰው ተስፋ ከመቁረጡ የተነሳ በተለይ አሁን አሁን ብቻውን እያወራ መሄድ ጀምሯል ብቻ ሳይሆን ብቻውን የማያወራ እንደበሽተኛ የሚቆጠርበት ጊዜ ላይ ሳንደርስ አልቀረንም፤ ያልተነካ ግልግል ያውቃል ነውና እንዳይፈረድባችሁ ውሸቱን ነው ብላችሁ አደራችሁን በኔ እንዳትፈርዱ። የማን ዓለመኛ ነው ሰው ሁሉ በኑሮና በፍትህ ዕጦት ዐብዶ እሱ ሳያብድ የሚቀር? ከእግዚአብሔር በስተቀር ሁሉም ስለሰላም የሚሰብክ በሀገርም ይሁን በውጭ ያለ ዜጋ አሸባሪ ከሆነ ከእንግዲህ ምን ቀረን? ኦባንግ ኦ. ሜቶ ሳይቀር አሸባሪ ሲሆን? ምን አለፋችሁ ለአቅመ-አሸባሪነት ካልደረሱ የጋንዲ ማዋለጃ ሆስፒታል ሕጻናት በስተቀር ቆሞ የሄደው ሁሉ አሸባሪ ሆኗል – አሁንስ መለስ እያሳዘነኝ ነው፡፡ በጤናው ነው ብላችሁ ነው? የቅንፉ ሃሳብ አባሪ እንጂ መነሻየ አይደለም።)

 

አዎ! ‹ባለቤት  ካልጮኸ ጎረቤት አይረዳም፡፡› ሦርያውን መጮኽ (መሞትም) ከጀመሩ ዓመት ሊጠጋቸው ነው። በይፋዊ ግምት እስካሁን ከ3600 በላይ ዜጎች በሥልጣን አልጠግብ ባዩ የአሲድ ማለቴ የአሳድ ጨፍጫፊ መንግሥት ተገድለዋል፤ ከሰባ ሺህ በላይ ዜጎች በዬእሥር ቤቶች ታጉረው ለሞትና ለእንግልት እንደተዳረጉ ይነገራል። ሰላማዊ ኑሮና ሥራ ብቻ ሳይሆኑ የዜጎች ሕይወትና የሀገር ኅልውናም አደጋ ላይ ወድቀዋል። በሠፈነው የአድልዖ አገዛዝ ምክንያት በእህህ የመከራና የቁጭት ሕይወት ሲገፉ የነበሩ የአንዲት ሀገር ዜጎች ወደባሰ የመቃቃር ሁኔታ እየገቡ ይመስላሉ። የሀገሪቱ የጦር ሠራዊት ከነበጀቱ የተሰለፈው የውጭ ጠላትን በታንክና በጀት ለመውጋት ሳይሆን የዴሞክራሲ መብቱን በሰላማዊ ሰልፍ  ሊጠይቅ አደባባይ የወጣን 88 ከመቶ የሚሆነውን የሀገሪቱን ሕዝብ ለማንበርከክ ነው እየተባለ ነው። የአፍሪካ ወያኔ በአፍሪካ ቀንድ – በኢትዮጵያ – የመካከለኛው ምሥራቅ ወያኔ ደግሞ በሦርያ። የሚገርም አጋጣሚ። የሠመረ የታሪክ መመሳሰል ይሏል ይህንን ነው። እርግጥ ነው የኛ ድህነትና መለኪያ በሌለው ሁኔታ መጠኑን ያለፈ ሀገራዊ ጉስቁልና ለዚህ ዓይነቱ ውድድር እንኳን አላበቃንም።  በቁንጅና ውድድር መሸነፍ አንድ ነገር ነው። በፉንጋነት ውድድር መሸነፍ ደግሞ ሌላና የሚቆጭም ነገር ነው። የሦርያ ሕዝብ እኮ ቢያንስ እንደኛ ሀገር አልባ ሆኖ አይደለም በአውሬው ሃፊዝ አላሳድ ልጅ በለግላጋው አውሬ በባሽር አላሳድ እየተመተረ ያለው። ተጨማሪ ነጻነት ለማግኘት መብቱን ጠየቀ – ልክ እንደኛው የጥይት መልስ ተሰጠው። በየቀኑ እያለቀ አንዳች ተስፋ ሳይቆርጥ የነጻነት ትግሉን ቀጠለ። አሁን ሰሚ እያገኘ ነው። የዐረብ ሊግ ወንድ ሊወጣው ነው – ሴትም ጭምር። ይሄ የ‹ጄንደር› ነገር ምን ይሻላል!

 

የዐራብ ሊግ ከሦርያ ሕዝብ ጎን መቆሙን በዛሬ ውሎ አስቸኳይ ስብሰባው ገልጾለታል። ደስ ይላል። ይህ ጅማሮ ፍሬ እንዲይዝ በበኩሌ ፈጣሪን ተማጥኛለሁ። የተጀመረ የማያልቅ፣ በርትቶ የታገለ የማያሸንፍ የለምና ይሄውና ‹የመጨረሻው መጀመሪያ› የነጻነት አብሪ ጥይት ዛሬ በካይሮ ተተኮሰች። …

 

በዚህ ስብሰባ ማጠናቀቂያ ከአንዲት ሴት የፖለቲካ ተንታኝ ትሁን ዜና ዘጋቢ ያዳመጥኩትና በፊትም የማውቀው ጉዳይ ግን ከነከነኝ – የሴቷን ማንነት አሁን ረስቼው ነው ይቅርታ። የችግራችን መመሳሰልም ፍንትው ብሎ የተገለጠልኝ ያኔ ነው – ለመጻፍም ያነሳሳኝ።

 

የሦሪያ መንግሥት ተቃዋሚ ወገኖች  ኮከባቸውና ክፍላቸው እንደኛዎቹ ተቃዋሚዎች የአንዳቸው ካንዳቸው አይገጥምም አሉ። ይህ ዓይነቱ የተቃዋሚዎች መረገም ደግሞ ለጨቋኞች ሠርግና ምላሽ ነው። ከጮማና ውስኪ በበለጠ የሚያጣጥሙት ምናባዊ የሥጋ ማድለቢያ ምግብ ቢኖር የተቃዋሚዎቻቸው መለያየት ነው። በተቀናቃኞቻቸው መካከል ሽብልቅ በመቀርቀብ ለመፈረካከስና እስከተቻለም ድምጥማጣቸውን ለማጥፋት የማያደርጉት ጥረት የለም። ይሄ ጉዳይ የአደባባይ ምሥጢር ነው፤ ተቃዋሚዎች ግን ለዚህ ዓይነቱ ሤራ በራቸውን የሚዘጉና የሚጠነቀቁ አይመስሉም። ሞኝነት ወይስ ፖለቲካዊ መርገምት? ምን ይሻላቸው ይሆን?

 

በመቶዎች የተቧደኑት የሦርያ ተቃዋሚዎች የአሳድን መንግሥት ከሚጠሉና ከሚፈሩ ይልቅ በበለጠ እርስ በርስ ይፈራራሉ፤ ይጠላላሉ፤ ይጠላለፋሉም ይባላል። በዓለም የፖለቲካ መድረክ ከበሬታን የሚያስነፍጋቸው ትልቁ የኪሣራቸው ምንጭ ይሄ ወጡ ሳይወጠወጥ ቂጢጥ የሚያደርጉት የሥልጣን ሽሚያ ወስከምቢያ ጉዳይ ነው እየተባሉ ክፉኛ ይተቻሉ። ለዝንጀሮዋ ተረት ቁብ ያላቸው አይመስሉም – ‹ቀድሞ የመቀመጫየን› ያለችውን። ሦርያን ለጨፍጫፊው አሳድ አሳልፎ ሰጥቶ፣ ራስን በግዞት ካይሮና በመላው የዐረብ ምድር በትኖ ገና ለገና – ዛር ወርዶ ተንቀጥቅጦ – ዘንቦ ተባርቆ – ለሚገኝ የሥልጣን ፍርፋሪ ከዋናው ጠላት በመረረ ሁኔታ የገዛ የትግል አጋርን መጥመድ የጤነኝነት ሳይሆን የወፈፌነት ምልክት መሆን አለበት ብቻ ሳይሆን በእርግጠኝነት ነው። ይህ ደዌ ሦርያን ብቻ ሳይሆን የኛዋን ኢትዮጵያን ጨምሮ የብዙ ሀገሮችም የታወቀ ግን መድሓኒቱ የጠፋለት የበሽታዎች ሁሉ ንጉሥ ኃያል ወረርሽኝ ነው።  በጠበል አይድን፤ በክኒን አይድን፤ በመርፌ አይድን፤ በመታሻ ቅባት አይድን፤ ዋገምት አይነቅለው፤ ወጌሻ አያገኘው፤ መጣፍ ገላጭና ድቤ መች አያውቁት… እንዲሁ በአሰለጦች የታወረ ልቦና ውስጥ ተሸጉጦ ሀገርና ሕዝብን ያምሳል፤ በ‹ላም አለኝ በሰማይ› የሕልም እንጀራ የአንዲት እናት ልጆችን እርስ በርስ ያባላል። እንዲያ ባይሆንማ ኖሮ አሁን ማ ይሙት የባሽር አላሳድ ማለትም የመለስ ዜናዊ ቅልብ የቁርጥ ቀን ጦር ሕዝብን ያለ አንዳች ርህራሄ ለመጨፍለቅ አነጥንጦ በሚገኝበት ሁኔታ የሥጋ ቅርጫ መደብ ወይም የዕድርና የሰንበቴ ማኅበር ይመስል በመቶና ከዚያ በላይ በሚቆጠር የተቃውሞ ጎራ ተሰልፎ መወራከብ እንደአዋጭ የትግል ሥልት መያዝ ነበረበት? በእውነቱ በየሀገሩ የሚታየው ይህን መሰሉ የጅልነት ሥራ በእጅጉ ይገርማል። ከዚህ ዓይነቱ የሞኞች አባዜ የሀገራችን የተቃውሞ ኃይላት ትልቅ ትምህርት እንደሚቀስሙ አምናለሁ። ዝንጀሮዋ ምን አለች? ‹ቀድሞ የመቀመጫየን›።

 

ማበጠሪያ የሚያስፈልገው ፀጉር ያለው ነው፤ መተኛት የሚችል ሃሳብ የሌለው ነው፤ ማንቀላፋት የሚችል እንቅልፉ የመጣ ነው፤ ማሰብ የሚችል አእምሮ ያለው ነው፤ ትናንትን ከነገ የሚያመዛዝን ትናንት ወዲያን ከነገ ወዲያ ማገናዘብ የሚችል አስተዋይ ነው። የሰውን ደምና ሕይወት በሥውርና በግልጽ እየገበሩ በሸርና በተንኮል የሚገኝ ሀብትና ሥልጣን ነገና ከነገ ወዲያ የገዛ ትውልድን አንገት እያስደፋና ዐፅምን  እያስወቀሰ ክፉ ስምን ከመቃብር በላይ የሚያኖር አደገኛ መርዝ ነው። ልብ ያለው ልብ ይበል። ‹ነገም ሌላ ቀን ነው›፤ እንደትናንቱ ሁሉ። የኢትዮጵያ ሰማይ ያረገዘውን በገደምዳሜ የተናገርሁ ይመስለኛልና ‹ሰንበትን እሑድ› ማለት እንደማያስፈልገኝ ለሚመለከተው ወገን ጠቁሜ ሃሳቤን ልቋጭ፤ ቋጨሁ።

 

መሰነባበቻ፡-

እዚያ ማዶ ሆኖ ክፉ ሰው ተጣራ፤

እዚህ ማዶ ሆኖ ክፉ ሰው ‹ወይ› አለው፤

ጎበዝ ተጠራጠር ይህ ነገር ለኛ ነው፡፡

ይሉ ነበር አባቶች።

 

(ውይ፣ ሞት ይርሳኝ፤ በበቀደሙ ጦማሬ አንዲት መናኛ ስህተት ሠርቻለሁ፡፡ ያቺውም በሠንጠረዡ ውስጥ የሽቦ(እስታፋ እሚሉት) ዋጋ አሁን 30ብር 10 ዓመት በፊት 3 ብር ማለት ሲገባኝ ሁለቱንም 30 ማለቴ ነበር፡፡ ለማንኛውም አሁን ከይቅርታ ጋር አረምኩት፡፡)