ጣዖቱን ተቃወሙት መሰዊያውንም አፍርሱት!
ወያኔ ብሶት የወለደው የህዝብ ልጅ ነበር። አሁን ያ የህዝብ ብሶት የወለደው ድርጅት ሙቶ በቀበሩ ላይም መለስ ዜናዊ የሚባል ጣኦት ቁሟል።ኢትዮጵያዊያንም ለዚህ ጣኦት መስዋእት ሁነው ቀርበውለታል። ጣኦቱም በፈለገው መንገድ የቀረበለትን መስዋእት እየበለተ ምሱን እየወሰደ ነው።
ይህ ጣኦት ይሁን ያለው እየሆነ አይሁን ያለው ደግሞ ሳይሆን እየቀረ እነሆ ሁለት አስርተ ዓመታት ተቆጠረ።
ይህ ክፉ ጣዖት አማራና ኤምፔሪያሊዝም የትግራይ ህዝብ ጠላቶች ናቸው ብሎ እኩይ ስብከቱን ጀመረ። ልቦናቸው ከባህር ዓለት በላይ የጠነከረው ካዳሚዎቹም ስብከቱን ሰምተው የወንድሞቻቸውን ደም በከንቱ እያፈሰሱ መኖርን ልማድ አድርገው ለሁለት አስርተ ዓመታት ዘለቁ። ድሃ አማራ እንደምን ሁኖ ጠላታችን ይሆናል? ኤምፔሪያሊዝምስ ማን ነው? ብለው የጠየቁ ደጋግ ትግሬዎችን አድሃሪ ብለው ብዙ መከራ አደረሱባቸው።አንዳንዶቹን በእሳት አቃጥለው ለጣዖቱ መስዋእት አቀረቡለት። አንዳንዶቹንም በደረግ ጥይት አስመትተው ደማቸውን አስፈሥሰው ሌላ መስዋእት አደረጓቸው። ሌሎችንም ከቀያቸው እንዲሰደዱ አድረገው ለመከራ ዳረጓቸው።
ይህ ክፉ ጣኦት የደስታው ምንጭ በወንድማማቾች መካከል የሚነሳው ግጭት ነው። እስከ አሁን ብዙ ግጭቶች ተፈጥረው ብዙ ደሙ ፈሷል።ጣኦቱም የወንድሞች ደም ሲፈስ ረክቶ ክፋቱን አጠናክሮ ቀጥሎበታል። ይሁን እንጂ ጣዖቱ መለስ ዜናዊ የትላልቆቹን ብሄረሰብ አባላትን ደም ለማፋሰስ የቋጠረው ሁሉ በሚፈልገው ሁኔታ አልያዘለትም። ይህ እኩይ ሙከራው በህዝቦች አርቆ አስተዋይነት እየመከነበት ነው። መለስ ዜናዊ ግን የማያባራ ጥፋት ሊያስከትሉ የሚችሉ ክሮችን መምዘዝ ጀምሯል። በአማራና በኦሮሞ መካከል ሊገነባ የሞከረው የጠብ ግድግዳ እየተናደ ሲመጣ ዓይኑን ወደ ሃይማኖቶች አዘንብሏል። በዚህ ወጥመድ ውስጥ የሚገቡ የዋሃን አማኞች እንደማይጠፉ ጣኦቱ መለስ ዜናዊ ጠንቅቆ ያውቃል።
ዛሬ በነጻው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የዘርን ግድግዳ ሰብረው በአንድ ጣሪያ ሥር ቁጭ ብለው ስለ ነጻነታቸው ማውራት መቻላቸው መለስ ዜናዊን አስደንግጦታል።እንደጠላት እንዲተያዩ ሲደረጉ የነበሩ ህዝቦች የለም እኛ ወንድማማች እንጂ ጠላት አይደለንም ብለው እጅ ለእጅ ተያይዘው መቆም መጀመራቸው ለጣኦቱ የሚቀርብለትን የደም መስዋእትነት ስለሚያቆመው መለስ ዜናዊ ክፉኛ ተሸብሮ የሃይማኖት ግጭቶችን እዚህና እዚያ እየፈጠረ ነው።
በአገራችን ታሪክ እስላምና ክርስትያን ተከባብሮ በክፉም በደጉም እየተገናኘ ለብዙ ዘመን አብሮ የኖረ ህዝብ ነው።ይህን አብሮነት ለማፍረስ መለስ ሆን ብሎ የሚያደርጋቸው ተንኮሎችን በተደጋጋሚ ተመለክተናል። አስቀደሞ በታሰበበት ሁኔታ በጎንደር ከተማ አንድን ቦታ ለመስኪድም ለቤተክርስትያንም መስሪያ እንዲሆን ለሃይማኖት ተቋማቱ በመስጠት ግጭት እንዲፈጠር አድርጎ የወንድማማቾች ደም እንዲፈስ አድርጓል። ወደ ደቡብም በመዝለቅ በአሰንዳቦ ከተማ በክርስትያኖችና በሙስሊሞች መካከል ግጭት ተፈጥሮ የብዙ ዜጎች ደም ፈሷል።ይህም በጣኦቱ መለስ ዜናዊ ካዳሚዎች አማካኝነት ሆን ተብሎ የተፈጠረ ግጭት መሆኑን መገንዘብ ተገቢ ነው።
የጎንደረም ሆነ የአሰንዳቦ ህዝብ ከመሬት ተነስቶ እርስ በርሱ የሚገዳደልበት ምንም ምክንያት የለውም። ጣኦቱ መለስ ዜናዊ ህዝቡ ተስማምቶ ሲኖር የደነግጣል ይሽበራል። ነፍሱም ሠላም ታጣለች። በአሰንዳቦ ከተማ ቅዱስ ቁርዓንን ቀዳድዶ በክርስትያኖች መንድር በመጣል ያንንም ራሱ ለፈጠራቸው ሙስሊም መሰል ካድሬዎች በማሳየት ጠብና አምባጓሮ እንዲነሳ አድርጎ የወንድማማቾችን ደም አፋሷል። ጣኦቱ ይሁን ያለውን ለማስፈጸም በየቦታው ያሉ ነውራቸው ክብራቸው የሆኑ የጣኦቱ ካዳሚዎችም የሚገነቡትን የጠብ ግድግዳና የሚያስከትለውን መዘዝ ሳይረዱ የዜጎችን ንጹህ ደም እያፈሰሱ መስዋእት ለማቅረብ ሌት ተቀን እየተጉ ነው።
የተከበራችሁ የአገራችን ዜጎች ዛሬ ሃይኖታችን የመለያያችን ምክንያት ሊሆን አይገባም። ሃይማኖት መገለጫው ፍቅር እንጂ የወንድምን ደም ማፍሰስ አይደለም። መለስ ዜናዊ ሆን ብሎ በሃይማኖቶች መካከል የሚፈጥረው ሰሃ በህዝቦች መካከል ሥር ሰዶ በቅሎና ፍሬ አፍርቶ ክፉ ዘር እንዳይፈጠር ከማስተዋል ጋር የመለስን ሰይጣናዊ እኩይ ሥራዎችን እንቃወም። የወንድሞቻችሁን ደምም መስዋእት አድረገው ለጣኦቱ እድሜ መርዘም በየግዜው ለማቅረብ የሚተጉትን በቃ እንበላቸው።
ኢትዮጵያችን ሁሉም ዓይነት ሃይማኖቶች ተከባብረው የሚኖሩባት የሁሉም አገር ነች። ኢትዮጵያዊያን በሃይማኖታቸው ምክንያት የመገዳደል ልማድ ኑሯቸው አያውቅም። በሃይማኖት ምክንያት ወደ ግጭት የሚወስዱን የሰው ልጆች ደም ምስ የሆናቸው እነ መለስ ዜናዊ ናቸውና አንድ ላይ ሁነን የዘመናችንን ይህን ክፉ ጣዖት እንቃወመው። የመሰውያውንም ሥርዓት ለማፍረስ በአንድ ላይ እንቁም።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !!!