ከፋፋዩ የወያኔ አገዛዝ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችን ማጋጨቱን ቀጥሉአል፣ ግጭቱን ወደ ከፋ ደረጃ ለማድረስ “አህባሽ” ለተባለው ቡድን ወታደራዊ ስልጠና እየሰጠ መሆኑ ታወቀ

ኢትዮጵያዊያንን በሰበብ አስባቡ በመከፋፈልና በማበጣበጥ ራሱን ስልጣን ላይ የማቆየት አባዜ የተጠናወተው ከፋፋዩ የወያኔ አገዛዝ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችን ማጋጨቱን እንደቀጠለ ሲሆን ግጭቱን ወደ ከፋ ደረጃ ለማድረስ “አህባሽ” ለተባለው ቡድን ወታደራዊ ስልጠና እየሰጠ መሆኑ ከአገር ውስጥ አልፎ በውጪ አገር የሚኖሩትንም ሙስሊም ህብረተሰብ  እጅግ እያሳሰበና እያስቆጣ መሆኑ ተገለጸ።

በተለያዩ የአውሮጳ፤ የሰሜን አመሪካና ኤዥያ ከሚኖሩ የሙስሊም ኮሚኒቲዎች ጋር የጋራ ህበረትና ትብብር እንዳለው የተገለጸው የሉቅማን ኢትዮጵያዊያን ቤልጄማውያን ሙስሊሞች ማህበር ሊቀመንበር የሆኑት አቶ አብዩ ያሲን እሁድ ጥቅምት 26 ቀን በብራስልስ ከተማ ለ1 ሺ 4 መቶ 33ኛው ጊዜ የተከበረውን የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል ምክንያት በማድረግ ለተሰበሰበው ምዕመንና ተጋባዥ እንግዶች ባደረጉት ንግግር ይህንን የሙስሊም  ህበረተሰብ ስጋት በማስረጃ አስደግፈው አቅርበዋል።

የሙስሊሙን ህበረተሰብ ለመከፋፈል “መንግሥት” ግልጽ የሆነ ዘመቻ እያካሄደ ነው  ያሉት አቶ አብዬ ፤ ክሳቸውን በማስረጃ በማስደገፍ ከባህር ማዶ የተላኩ የአህባሽ እምነት ተከታዮች የእምነታቸውን ዘርፍ አገር ውስጥ ለማስፋፋት እንዲችሉ 800 ለሚሆኑ ሰዎች ሀረር ውስጥ ቀናትን የፈጀ ስልጠና እንደተሰጠና ወደ ሌሎች ክልሎችም ተሰራጭተው ትምህርት ሊሰጡ የሚችሉ 200 ተጨማሪ ሰልጣኞች  በአሁኑ ሰዓት በሰንዳፋ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ውስጥ እየሰለጠኑ እንደሚገኝና ስልጠናውንም እንደጨረሱ እስከ 30 ሺ የሚጠጉ ሙስሊሞችን  በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማሰልጠን ብቃት ይኖራቸዋል የሚል  እቅድ መዘርጋቱን በመንግሥት ተወካዮች መነገሩን በማስረጃ አስደግፈው አስረድተዋል።

አቶ አብዩ ያሲን፣ በዚሁ ንግግራቸው አህባሽ የተባለው አስተምህሮ ለኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም አስጊ መሆኑን ገልጸው የወያኔው ኢህአዴግ አገዛዝ  የአገር አንድነትን አደጋ ላይ የሚጥል፣ የእርስ በርስ ግጭቶችን ሊፈጥር የሚችል እምነት ለመደገፍ ለምን እንደተነሳሳ ግራ እንደገባቸው አልሸሸጉም። አቶ አብዩ በማብራሪያቸው የወያኔው አገዛዝ በህገመንግስቱ የሰፈሩትን መብቶች መርገጡን ጠቅሰው፣ አሁን የሚታየው አንዱን አስተምህሮ ደግፎ ሌላውን የማውገዝ አካሄድ የአገርን ሉአላዊነት የሚጎዳ፣ ህዝቦች ለዘመናት ተቻችለው የኖሩበትን ስርአት የሚያጠፋ፣ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ያላቸውን ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት፣ የሙስሊሞችን እና የእስልምናን መልካም ምስል የሚያበላሽ በአጠቃለይ በአጼው ዘመን ወደ ነበረው ታሪክ መልሶ የሚወስድ መሆኑን ተናግረዋል። በመጨረሻም ሊቀመንበሩ በንግግራቸው አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ የሚታዬውን አደገኛ ሁኔታ መቀዬር የሚቻልባቸውን መንገዶችም ዘርዝረዋል።

በሌላ በኩል በበአሉ ላይ ከተገኙት ሙስሊሞች መካከል አቶ ገአዝ አህመድ የተባሉት የቤልጂየም ነዋሪ፣ የአህባሽ መሪዎች አስተምህሮውን በአገር ውስጥ እንደማንኛውም የእምነት ተቋም ለማስፋፋት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የመብት ጉዳይ በመሆኑ እንደማይቃወሙት ገልጠው፣ ይሁን እንጅ የወያኔ ኢህአዴግ ከፋፋይ አገዛዝ  በፖሊሲ ደረጃ ቀርጾ፣ በጀት መድቦና ሰዎችን አሰልጥኖ እምነቱን ለማስፋፋት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ እርሳቸውም ሆኑ ሌሎች ሙስሊሞች እንደማይቀበሉት ተናግረዋል።