ሞኙ ጠቅላይ ምኒስትራችን (በገብረ ክርስቶስ ዓባይ)
የጥንቱን የአስተዳደር ሁኔታ፤ የመሪነት ብቃትና ችሎታ ለጊዜው ወድጎን እንተወውና የዘመናዊውን አስተዳደርና የመሪነት ችሎታና ብቃት አሁን ባለንበት የ21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ሆነን ስንመለከተውና የእኛን አገር መሪ ከቀሪው የዓለም መሪዎች ጋር በንጽጽር ስናጤን ጠቅላይ ምኒስትራችን ሞኝ እንደሆኑ ለመረደት እንችላለን።
እኔም ይህንኑ መነሻ በማድረግ ነው የጽሑፌን አንኳር መልዕክት ለማስተላለፍ የምፈልገው። በቅድሚያ ግን ስለእራሴ አቋምና ማንነት በአጭሩ ለአንባቢያን ገልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ።
እኔ የፖለቲካ ሰው አይደለሁም። ይሁን እንጂ ፖለቲካን ጭራሹኑ አላውቅም ማለቴ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ። የአንድም የፖለቲካ ድርጅት ዓባልና ደጋፊም ስላልሆንኩ ፕሮፓጋንዳየን በኅብረተሰቡ ዘንድ ለማስረጽ የተነሳሁ እንዳይመስላችሁ ለማስረገጥ እንጂ። በአንፃሩም ፈሪሃ እግዚአብሔር ቢኖረኝም የሃይማኖት ሰው ግን እንዳልሆንኩ በወፍራሙ አሠምርበታለሁ። ስለሆነም ሰባኪ አይደለሁም ማለት ነው። ነገር ግን እንደማንኛውም አገር ወዳድና ወገን አክባሪ ማለትም ቀና አሳቢ ንጹሕ ሰው መሆኔ እንዲታወቅልኝ በትህትና መግለጽ እወዳለሁ።
እንግዲህ ይህንን ጭብጥ በአዕምሮአችሁ ከያዛችሁልኝ ወደተነሳሁበት ዋነኛ ዓላማና ለዚህ ጽሑፌ ምክንያት ስለሆነኝ ጉዳይ አመራለሁ።
ከላይ እንደገለጽኩት ዓለማችን የኮምፒውተር ዘመን ላይ እንዳለችና አልፎ ተርፎም የዲጅታል ቴክኖሎጂ ጊዜ ላይ ስለሆነች መረጃ ከድምፅ ፍጥነት ወደ ብርሃን ፍጥነት አልፎ ተርፎም ከዚያም በላይ የተሸጋገረበት ወቅት በመሆኑ በዓለም ዙሪያ የሚደረገው የመረጃ ልውውጥ ፍጥነቱ ከዛሬ ሠላሳ ዓመት በፊት ከነበረው ሁኔታ ጋር እንኳ ቢነፃፀር እጅግ በጣም የሚያስገርም ዕድገት እንደተደረገ ለማንም የተሰወረ አይሆንም።
ዛሬ ዕውቀትን ለመቅሰም የግድ ትምህርት ቤት መሔድ አስፈላጊ አይደለም። በቤት ውስጥ ቁጭ ብሎ ወይንም በቢሮ አለበለዚያም በሔዱበት ሁሉ በላፕ ቶፕ ኮምፒውተር አማካኝነት የፈለጉትን ዓይነት ዲሲፕሊን ማጥናት ይቻላል።
ግን ይህንን ቴክኖሎጂ ማንኛውም ሰው መጠቀም ይችላል የሚል አስተሳሰብ ይዤ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ። የጠቀስኩት ግን ዓለም የደረሰችበትን የዕድገት ደረጃ ላማስገንዘብ ሲሆን ቢያንስ በሠለጠኑ አገሮችና ዕድሉ ባላቸው ሰዎች ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል።
ኢሜል፤ኢንተርኔት፤ቴክስት ሜሴጅ፡ዩ ቲዩብ፤ ፌስ ቡክ እና ትዊተር የመሳሰሉት ተጠቃሾች ናቸው።
ወደ ታዳጊው አገር ስንጓዝ እስኪ የኛይቱን ምስኪን አገር በዓይነ ሕሊናችን እንቃኛት። ተወልደው ወደ አደጉበት አካባቢ በትዝታ ልውሰድዎና በዚያ የሚገኙትን የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ለአንድ አፍታ ያስታውሱ። እነዚህ ተማሪዎች ከጓደኞቻቸው ጋር ሆነው ስለወላጆቻቸው፤ስለወገናቸውና ስለ ገራቸው ሲወያዩ በምናብዎ ያስቡ። ምን ይሉ ይመስልዎታል? እንደ እኔ “እኔ አድጌ ፤ትምህርቴን ተምሬ ስጨርስ አገሬንና ወገኔን በጥሩ ሁኔታ አገለግላለሁ። በተለይ መሪ ብሆን ለአገሬና ለወገኔ ብዙ ብዙ ነገር አደርጋለሁ።” ይላሉ አይደል?
የውጭውን የሰለጠነ የዓለም ክፍል ሁኔታም ደግሞ እንቃኘው። በተለይ በምርጫ ሰሞን የሚደረገውን ሁኔታ ማስታወሱ ተገቢ ነው።
“እኔን ብትመርጡ የተረጋጋ ሕይወት ይኖራችኋል። የሥራ ዋስትናችሁ ይረጋገጣል። የጤና ጉዳይ አያሰጋችሁም፤ ሕክምና በነፃ አደርጋለሁ። ለወላጆች (ለእናቶች) የስድስት ወር የወሊድ ፈቃድ ከሙሉ ደመወዝ ጋር እሰጣለሁ። ለአባቶች ደግሞ የስድስት ሳምንት የአባትነት ፈቃድ ከሙሉ ደመወዝ ጋር እፈቅዳለሁ፡ወዘተ…ወዘተ..” ይባላል። መንገድ እሠራለሁ፤ትምህርት ቤት እከፍታለሁ፤ሆስፒታል እገነባለሁ የሚለው እንዳለ ሆኖ።
እንዲህ ብሎ የተመረጠ የአገር መሪ የገባውን ቃል ኪዳን ለመፈጸምና ለማስፈጸም ሌት ተቀን ይሠራል፤ ያሠራል። ነገር ግን የገባውን ቃል ኪዳን ሳይፈጽም ቀጣዩ የምርጫ ወቅት ቢደርስና እንደገና በተወዳዳሪነት ለምርጫ ቢቀርብ ሕዝብ ደግሞ አናውቅህም በማለት የምርጫ ካርዱን ለሌላ ይሰጥበታል።
ይህ እንዳይሆንና ቀድሞ ከእርሱ በፊት ከነበሩ መሪዎች የተሻለ ሆኖ ለመገኘት አገሪቱ እንድትበለጽግ የሚያበረታቱ ሕጎችን ያወጣል። ማነቆ የሆኑ ደንቦችን በአዋጅ ያሻሽላል፤ወይም ይቀይራል።
ሕዝቡ በነፃነት ከቦታ ቦታ እየተዘዋወረ የመሥራትም ሆነ የመኖር ዋስትናው እንዲረጋገጥ ያደርጋል። የጸጥታው ሁኔታ ለመንግሥት ባለሥልጣናትና ለመንግሥት ተቋማት ብቻ ሳይሆን ለማኅበረሰቡም ጭምር መሆኑን ያስተማምናል።
ሳምንቱን በሥራ ተወጥሮ የሰነበተው ሕዝብ በሳምንቱ መጨረሻ ከዘመዶቹ፤ ከጓደኞቹ፤ ከሥራ ባልደረቦቹና ወይም ከመሰለው ሰው ጋር እየተገናኘ በመገባበዝ ራሱን እያዝናና ይቆይና ለቀጣዩ የሥራ ሳምንት አዲስና ብሩህ አዕምሮ ይዞ ወደ ቢሮ ይመለሳል። እንዲህ የመሰለው የኅብረተሰብ ክፍል የፈጠራ ሥራ ለመሥራት ያለው ዕድል ከፍተኛ ነው። የምግብ፤ የልብስ፤ የመጠለያ ሁኔታዎችና የመዘዋወሪያም መኪና ጭምር እንደ መሠረታዊ ፍላጐት ስለሚቆጠሩ ኅብረተሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ የማግኘት ብቻ ሳይሆን በዓይነትም ሆነ በጥራት ደርጃው ከፍተኛ የሆነ አገልግሎት ማግኘቱን መንግሥት የዕለት ተዕለት ትኩረት ከሚሰጣቸው ጉዳዮች ዋነኞቹ ናቸው።
የትምህርትና የሕክምናም አገልግሎት ምንም ዓይነት ልዩነት ሳይፈጠር ለሁሉም ዜጋ በዕኩልነት መቅረባቸውን መንግሥት ይከታተላል፤ ይቆጣጠራል። በአጠቃላይ ሕዝቡ በአገሩ እንዲኰራ፤በመንግሥቱ እንዲተማመን የሚያደርግ ውስጣዊ ሥነ ልቡና እንዲፈጠርበት ያደርጋል።
እያንዳንዱ ዜጋ ከፍተኛና የተነቃቃ ሞራል እንዲሠርጽበትና በራሥ መተማመን እንዲኖረው፤ አልፎ ተርፎም ገሩ የሚፈልግበትን የድርሻውን በአግባቡ እንዲወጣ የሚገፋፋና አንገቱን ቀና አድርጎ እንዲኖር በተለያየ መንገድ ድጋፍ ይደረግለታል። ስለሆነም በአገሩ ጉዳይ ላይ ሐሳቡን የመግለጽ፤ የመጻፍ፤ የመናገርና የመደመጥም መብት እንዲኖረው በሕገመንግሥቱ ተቀርፆ በተግባር መተርጐሙንም መንግሥት ይቆጣጠራል።
ቢያንስ በሦስት ወር አንድ ጊዜ ወደ ሌላ ክፍለ ገር ሙሉ ቤተሰቡን ይዞ በመሔድ የዕረፍት ጊዜውን ማሳለፍ፡ በዓመት ወይንም ከሁለት ዓመት አንድ ጊዜ ደግሞ ወደ ውጭ ገር ሔዶ የመጐብኘት አቅም የሚፈጥር የኢኮኖሚ አቋም እንዲኖረው መንግሥት በፍጆታ ዕቃዎች ላይ አላስፈላጊ ታክስን አይጥልም። ቀደም ሲል ከነበረም እያጠና የመፍትሔ ርምጃ ይወስዳል።
የሕዝቡን ብዛት ዕድገት በማገናዘብም አዲስ ጎጆ ወጭ የሆኑ ወጣቶች የመኖሪያ ቤት የመግዛት ችግር እንዳይገጥማቸው በማሰብ የገንዘብ ድጎማ ከመንግሥት እንዲያገኙ ያደርጋል። ይሁንና ይህንና ሌሎች ተመሳሳይ አገልግሎቶችን መንግሥት ሲሰጥ መሪው ከግል አካውንቱ እያወጣ ሳይሆን አገሪቱ ያላትን ብት በአግባቡ ለሁሉም በዕኩልነት እንዲዳረስ ከሚደረግ ፍትሐዊ ከሆነ የአስትዳደር መርህ ነው።
ብዙ ብዙ ማለት ይቻላል ግን አንባቢን ማሰልቸት እንዳይሆንብኝ አንድ ሌላ ቁም ነገር ልጨምር። በበዓላት ቀን ሕዝቡ ጥሩ የመዝናኛ ጊዜ እንዲኖረው በማሰብም የኪነ ጥበባት መድረኮች ልዩ የሆነ እገዛና ድጋፍ ይሰጣቸዋል። የተለያዩ የእስፖርት ዓይነቶችም ከቀበሌ ታዳጊ ወጣቶች ምሮ እስከ ታዋቂ ክበቦች ድረስ ጥሩ የሆነ ማበረታቻና ድጐማ ይደረግላቸዋል።
ኅብረተሰቡም በዓባልነት የተመዘገበበትን ክበብ በገንዘብና በሞራል ይደግፋል። ከዚያም ውድድሩ የእኔ ክበብ ያሸንፋል የኔ ያሸንፋል በሚለው ሰላማዊ ፉክክር እንጂ በጠላትነት የሚተያይበት ልዩነት አይሆንም።
ጨዋታው ሲያልቅ አሽናፊው ደስ ሲለው ተሽናፊው ደግሞ በፈገግታ “ቆይ በሚቀጥለው ግጥሚያችን እናሽንፋችኋለን” በማለት የሚወያዩበት እንጂ “በቆምክበት አያቁመኝ፡ በዋልክበት አያውለኝ” በመባባል የሚረጋገሙበት መድረክ አይደለም።
እንግዲህ ከላይ እንደጠቀስናቸው ወጣት ተማሪዎች አንዱ የነበሩት የእኛው ጠቅላይ ምኒስትር በወቅቱ በነበራቸው የአገርና የወገን ፍቅር ተገፋፍተው ጫካ ከገቡ በኋላ ለረጅም ዓመታት ሲታገሉ ቆይተው ሲመኙት የነበረው ሥልጣን በእጃቸው ሲገባ ያ የወጣትነት ምኞታቸውና ሐሳባቸው ወዴት እንደተሰለበባቸው ሳይታወቅ ይባስ ብሎ እያደር ሲያወግዙትና ሲታገሉት ከነበረው የደርግ ሥርዓት በከፋ መልኩ አገራቸውንና ወገናቸውን ለከፍተኛ ውድቀት ዳርገዋል።
ጠቅላይ ምኒስትራችን ሞኝ ባይሆኑ ኖሮ ሕዝባቸውን እንዳይጽፍ እጁን አያስሩትም፤እንዳይናገር አፉን ደግሞ አይለጉሙትም፤እንዳያነብ በኅትመትና በተጓዳኝ የሥራ መስኰች ከፍተኛ የሆነ ጫና ባላሳደሩ ነበር።
የሚበላው ሳይጠፋና በየመጋዝኑ ተከዝኖ እያለ በመንግሥታቸው ጣልቃ ገብነት በተፈጠረው የዋጋ ንረት ሕዝቡ የመግዛት አቅሙ አልፈቅድ በማለቱ ዕንቁልጭህ አይሉትም ነበር። ወገናቸው መፈጠሩን እያማረረ አን ቱ በረሃብ ታጥፎ፤ ሞራሉ ተገፎ፤ አንገቱን ደፍቶ ሲቆዝም ማየት ግንነት ሳይሆን ውርደት መሆኑ በተሰማቸው ነበር።
ሌላው ቀርቶ ነገ ወደዱም ጠሉም ይህን ሙጥኝ ያሉትን ሥልጣን የሚለቁበት ሦስት መንገዶች አሉ። ከሦስቱ አንዱ ግን በምንም ዓይነት ከመሆን የሚገታው አንዳችም ኃይል ከቶ ሊኖር አይችልም።
) በቀጣዩ ምርጫ ሕዝብ እንደገና አሻፈርኝ ካለ የግድ መነሳታቸው አይቀርም።
ለ) በኃይል ደግሞ እርሳቸው ደርግን ባስወገዱበት መልክ በውጭ መንግሥት ድጋፍ በትጥቅና የፕሮፓጋንዳ ጦርነት የመሸነፍ ጽዋቸውን በግድ እንዲጠጡት የሚያደርግ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።
ሐ) በተፈጥሮ ሕግ ማለትም በሕመም ወይም ደግሞ ባልታሰበ በአደጋ ለምሳሌ እርሳቸው ሥልጣን ላይ የወጡት በጦርነት የበላይነት አግኝተው ሳይሆን ደርግ በአገር ውስጥ በኢሠፓ አውደልዳዮች በመሞላቱ በሕዝብ ስለተጠላ፤ በውጭ ደግሞ የሶሻልስቱ ጎራ በጎርቫቾብ ፐርስትሮይካ በመከለሱ ድጋፍ ስለተነፈጋቸውና ምዕራባዊያን አገሮች በበኩላቸው ኢትዮጵያ እየተከተለችው የነበረውን ፖሊሲ ይቃወሙ ስለነበር እንዲሁም ግብጽና ሊቢያን ጨምሮ ዓረባውያን አገሮች የሚሸርቡት ሴራ ከጦርነቱ በከፋ መልኩ የፕሮፓጋንዳው ዘመቻ ከፍተኛ በመሆኑና ሁኔታዎች በመመቻቸታቸው ያለምንም ውጣ ውረድ ሰተት ብለው የገቡትና ዙፋኑን የተቆናጠጡት።
በወቅቱ የደርግ ባለሥልጣናት (እነ ዶክተር አሻግሬ ይግለጡ) የተገኙበት በአሜሪካ የውጭ ቢሮ ዴስክ የአፍሪካ ጉዳይ ኃላፊ በነበሩት በኸርማን ኮኽን አደራዳሪነት ከወያኔና ከሻዕቢያ ተወካዮች ጋር ለመነጋገር በእንግሊዝ (ለንደን) እንዳሉ እኒሁ አሜሪካዊ ያለኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት ያገራቸውን ፖሊሲ ሲያስፈጽሙ “አገሪቱ መሪ የላትም፡ ሕዝቡ የእርስ በእርስ ጦርነት ሊ ምር ስለሚችል በአሁኑ ወቅት ተደራጅቶ ያለው ወያኔ ስለሆነ ወደ አዲስ አበባ ገብቶ የተሸበረውን ሕዝብ ማረጋጋትና ማስተዳደር መ መር አለበት” በማለት የሰጡትን አስተያየት መሰል ትዕዛዝ የሥልጣን ፍላጎት የነበራቸው የደኅንነቱ ሚኒስትር ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ በመቀበል ሁኔታዎቹን አመቻቹላቸው።
እንዲህ ያለው ከህደት ባይፈጠር ኖሮና በሰላማዊ መንገድ ትጥቁን የፈታው የደርግ ወታደር ቀርቶ ነዋሪው ሕዝብ እስከመጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ ቢዋጋ ኖሮ ሁኔታወች ሊቀየሩ ይችሉ እንደነበር መገመት አያቅትም።
ነገር ግን ለሕዝብ ነጻነትና እኩልነት እንዲሁም ለዲሞክራሲ ሲታገሉ የነበሩት ወጣት፤ የዛሬው ጎልማሳ፤ ዓላማቸው ግቡን መትቶ ምኞታቸው ተሳክቶ በትረ ሥልጣኑን ከጨበጡ በኋላ ሁሉም ነገር እንደጉም ተነነና በእጅ የያዙት ወርቅ እንደ መዳብ ይቆጠራል ሆነባቸው።
ይህንን ታላቅ ክብርና የአገርና የወገን ከባድ ኃላፊነት አቃለሉት። በፊት ሕይወታቸውን ለመስጠት ዝግጁ የነበሩት ወጣት ለገሠ ዜናዊ አሁን ኢትዮጵያን በመዳፋቸው ውስጥ አስገብተው ሲፈልጉ የሚጨምቋት፤ሲፈልጉ ደግሞ እንደ ሸክላ ሠሪ የተለየ ቅርጽ የሚያወጡላት፤ሌላ ጊዜም እንደ ሰም የሚያቀልጧት፤ እንደ ብረት የሚቀጠቅጧት ሲፈልጉ ደግሞ እንደ ሽቦ የሚመዘምዟት ስትሆንላቸው የፊቱን የወጣትነት ራዕያቸውን ስለዘነጉ እንኳን ሕይወታቸውን ሊሰጡ ይቅርና ዲሞክራሲን በጥርኝ ነፍገዋታል።
የዚያን ጊዜው ብልጡ ወጣት ለገሠ ዜናዊ የዛሬው ሞኝ ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ ሌላው ቀርቶ እንኳን ሥልጣን ይቅርና ሕይወትን ማትረፍ እንደማይቻል ጨርሶ እረስተዋል። ከላይ እንደጠቀስኩት ወይ በኃይል፤ ወይም ደግሞ በምርጫ አለበለዚያም በተፈጥሮ ሕግ ሁሉም ነገር ያከትማል። ብርሃኑ ይጨልማል፤ የሕይወት እስትንፋስ ይቋረጣል፤ልብ የደም ዝውውሩን ያቆማል፤ የሞቀው ሰውነት ይቀዘቅዛል፤ በዚህ ጊዜ ሰው የነበረው አካል ስሙ ይቀየርና በድን (ሬሳ) ይሆናል። ያኔ ፡የቅርብ ዘመድ፤ወዳጅ፤ሚስትና ልጅ ሳይቀሩ ይህንን ይዘው ለመቀመጥ ይጠየፋሉ። ሳይለውጥ እንቅበረው ይባላል። ከዚያ በኋላ አዱኛ ሁሉ ብላሽ!
ነገር ግን የሚቀር ነገር አለ። ያም ዘለዓለማዊ ነው። የታሪክ አሻራ! የሰማዩን እንተወውና በምድር የሚዘገበው ዜና መዋዕል ምን ዓይነት ይሆናል? (መቼም ይህችን ጽሑፍ ማየታቸው ስለማይቀር በቀጥታ ለእርሳቸው መጠቆም ፈለግሁ።) የሚያወድስ ወይስ የሚወቅስ? እንደጸሐፊው ምኞት ከሆነ እግዚአብሔር ለመወደስ እንጂ ለመወቀስ አይዳርግዎ። ጠቅላይ ሚንስትር አሁንም ዕድሉ ያለወት ይመስለኛል። ወደ ትክክለኛው ሕሊናዎ ከተመለሱ ዕድሜዎን ሙሉ ለታገሉለት ሕዝብና አገር፤ ተገቢውን ማለትም ትክክለኛውን ሕገ መንግሥት (Constitution) እንደገና በመመርመር፤ ሲሆን ዲሞክራት ነን ብለው ከሚመጻደቁ አገሮች በተሻለ መልኩ፤ አለበለዚያም መሠረታዊ የሆኑና የአንድን አገር ሉዓላዊነት በሚያረጋግጥና በሕዝበ ውሳኔ የሚደረግ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር የሚረጋገጥበት፤አንድ ግለሰብ ደግሞ ከአሥር ዓመት (ከሁለት የሥልጣን ዘመን) በላይ በኃላፊነት የማይቆይበት ሥርዓት ሠርተው ቢለቁ ታሪክዎ መልኩን ሊቀይር ይችል ይሆናል የሚል እምነት አለኝ።
ምክንያቱም ሕዝብ እንደ መንግሥት ጨካኝ ሳይሆን እንደ እግዚአብሔር መሐሪ ነው።
አሁን እኔ ለእርስዎ የመመኝልዎ እንደ ግብጹ ሆስኒ ሙባረክ፤እንደ ሊቢያው ጋዳፊ ወይም እንደ ኢራቁ ሳዳም ሁሴን እንዲሆኑ አይደለም። እንደዚያ ያለ ውርደትና ቅሌት ከእርስዎ እንዲርቅ የዘወትር ጸሎቴ መሆኑን ላረጋግጥልዎ እወዳለሁ።
እንዲሞቱም አልመኝም ምክንያቱም እኔም ሆን አገራችን የምትጎዳ ካልሆነ በስተቀር የሚጠቅመን ነገር የለም። በሕይወትዎ ላይ ምንም ዓይነት እንከን እንዲገጥምዎም አልፈልግም። እንደ ኡጋንዳው ኢዲ አሚን ወይም እንደ ቀድሞው የደርግ ሊቀመንበር ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም አገር ጥለው እንዲሰደዱም አይደለም። ምን እጠቀማለሁ ላጣች ለነጣችው አገራችንስ ሆነ በችጋር አለንጋ ለሚገረፈው ወገናችን ምን ይጠቅመዋል?
እንደ ዩጎዝላቪያው ስሎቮዳን ሚሎሶቪችም በውጭ አገር ፍርደ ገምድል ዳኞች ፊት ቀርበው ችሎት እንዲቆሙና አገሬ የዓለም መዘባበቻ እንድትሆንም አልናፍቅም። እንደ ቀድሞው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬገን በስትሮክና በደሜንሺያ እንዲሠቃዩም አልመኝም።
እኔ የምመኝልዎ ከሆነ ይህን ዓለም በቃኝ በማለት ዙፋናቸውን ጥለው ገዳም እንደገቡት (ከፖለቲካ ሥልጣን ውጭ) እንደ አፄ ካሌብ ወይም ደግሞ እንደ ትግራዩ ተወላጅ እንደ ሊቁ አለቃ ገብረ መድኅን ከተለያዬ የቤት ክርስቲያን ሹመታቸው በራሣቸው ፈቃድ እየለቀቁ ሌላ ሰው እንዲተካ ዕድል ሲሰጡ እንደነበሩት ፃድቅ ሰው፤ አለበለዚያም እንደደቡብ አፍሪካው የወቅታችን በዓለም የተከበሩ ታላቅ ሰው ኔልሰን ማንዴላ፤ ወይም ደግሞ እንደ አውስትራሊያው ኬቨን ራድ ሥልጣንዎን በፈቃድዎ ለቀው ዝንብዎን እሽ የሚል ጉዳይ ሳይደርስብዎ በማንኛውም የአገር ታላላቅ ጉዳዮች ላይ በክብር እንግድነት እየተገኙ በአገርዎ ውስጥ ሆነው እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በነፃነት ተከብረውና ተወደው እንዲኖሩ ነው።
ሰው ለክብሩ ካልተጨነቀ የሚሠራውን አያውቅም። እዚህ ላይ ለክብሩ ስል ስሙ በመጥፎ እንዳይነሣ ለማለት እንጂ እንደ ጣዖት እንዲፈራና እንዲመለክ ማለቴ አይደለም። ሕሊናው የሚገዛው ማለቴ ነው። ከንቱ ውዳሴንና አላግባብ ማጎብደድን የሚጠላ፤ ሁሉንም በኩል ዓይን የሚመለከት ለማለት ፈልጌ ነው።
አጎብዳጅ ከበዛ በዚህ ጊዜ ችግር እንዳለ መገንዘብ ይገባል። እነዚህ ሰዎች በሥርዓቱ ውስጥ በብዛት ካሉና በችሎታቸው የማይተማመኑ ከሆነ ከእነርሱ በላይ አዋቂ የሆኑትን ታታሪ ሠራተኞች ስማቸውን በማጥፋትና የማይገባቸውን ቀለም በመቀባት ሞራላቸውን ይነካሉ። ይህን በመሰለ ሥርዓት ደግሞ ሕሊና የሚባል ነገር ከቶ አይኖርም። ሕሊና ሲታወር ደግሞ የሕዝብ ኃላፊነት ይረሳል።
ኃላፊነት ከተረሳ ተገልጋዩ ሕዝብ መገልገያ ይሆንና በቢሮክራሲ መረብ ተተብትቦ እንዳይሠራና እንዳይንቀሳቀስ ይደረጋል። በዚህ ሁኔታ ፈጣን ዕድገት ሊኖር አይችልም። ይህን ሁሉ አያውቁትም የሚል እምነት የለኝም። እንዲያገናዝቡት ለመጠቆም ፈልጌ እንጂ። ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በሙስና ከኢንዶኔዥያና ከሕንድ ቀጥሎ በዓለም በሦስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ኬንያንና ሱዳንን በዳብል ፕሮሞሽን ረጋግጣቸው ሔዳለች።
እንግዲህ እርስዎ የሚያስተዳድሩት ኅብረተሰብ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ መገመት አይቸግርም። ጆሮ ለበለቤቱ ባዕድ ነው እንዲሉ እውነተኛውንና ሐቀኛውን ለማወቅ ከቅርብ ሰዎች ማግኘት እጅግ በጣም ከባድ ነው። ነገር ግን እውነቱ የሚወጣውና ፍንጭም የሚገኘው ከሕዝቡ ስለሆነ የሕዝቡን የልብ ትርታ በየወቅቱ እያዳመጡ በይፋ የሚያወጡት አንድም ተቃዋሚዎች በዋነኛ ደረጃ ደግሞ የነፃ ሜዲያ ጋዜጠኞች ናቸው።
አዋቂና ረጅም ራዕይ ያለው መንግሥት እነዚህን አካላት እያበረታታ በሚያቀርቡት ጥቆማ መሠረት ወዲያው ወዲያው ክፍተቱን እየደፈነ የጐደለውን እየሞላ ይጓዛል። ነገር ግን እነዚህን አካላት እያደነና እያሳደደ ዘብጥያ መክተቱ ዓይንን በገዛ እጅ ጓጉጦ እንደመታወር ወይም ደግሞ በጆሮው ሚስማር ቀብቅቦ ታምቡሩን በመንደል ወደ ጸማምነት እንደመቀየር ይቆጠራል። እንግዲህ ጽሑፌን ለማጠቃለል ከላይ በጠቀስኳቸው ነጥቦች ጠቅላይ ሚኒስትራችንን ብንመዝናቸው ሞኝ እንጂ ብልጥ እንዳልሆኑ እንገነዘባለን።