አዲስ የሊዝ መመሪያ በአትክልት ተራ ትርምስ ፈጠረ

(Reporter) — የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲ በሚያስተዳድራቸው የንግድ ቤቶች ላይ ተፈጸሙ የተባሉ ሕገወጥ ተግባራትን ሥርዓት ለማስያዝ በሚል ያወጣውን መመርያ ተከትሎ አዲስ አበባ መሰንበቻውን ተተራምሳለች፡፡

በተለይ በከተማው ውስጥ ከሚገኙ የንግድ ስፍራዎች መካከል ዋነኛው የአትክልት መሸጫ ማዕከል የሆነው የፒያሳ አትክልት ተራ ባለው ልዩ ባህሪ ምክንያት ብጥብጥ እያስተናገደ ነው፡፡

ኤጀንሲው ጥቅምት 17 ቀን 2004 ዓ.ም. አዲስ መመርያ አውጥቶ ‹‹ሕግ ለማስከበር›› አትክልት ተራ የተጓዘው ጥቅምት 27 ቀን 2004 ዓ.ም. ነበር፡፡ የኤጀንሲው ግብረ ኃይል በፖሊስ ጥበቃ እየተደረገለት በአካባቢው የሚገኙ የገበያ ማዕከል ተከራዮች ውላቸው ከዚያኑ ቀን ጀምሮ እንደተቋረጠ የሚገልጹ ደብዳቤዎችን በየንግድ ማዕከሉ በር ላይ ለጥፏል፡፡

በኤጀንሲው የአካባቢው ቀጣና ኃላፊ አረጋሽ ቸኮል ፊርማ ወ/ሮ ፎዝያ ከድርና ወ/ሮ ሙሉ ገብረ ኪዳን ለተባሉ ግለሰቦች የተጻፈው ደብዳቤ እንደሚያመለክተው፣ ኤጀንሲው ከእነዚህ ግለሰቦች ጋር የነበረውን ውል ማቋረጡንና የእነርሱን ሱቅ የተከራዩት ግን ከኤጀንሲው ጋር እንደሚቀጥሉ ይገልጻል፡፡

ይህ ሁኔታ በአካባቢው ከፍተኛ አለመግባባት ፈጥሮ በርካታ ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር እንዲውሉ አድርጓል፡፡ ጣይቱ ሆቴል ፊት ለፊት በሚገኘው የፒያሳ ፖሊስ ጣቢያ ይህንኑ ትዕይንት ከትናንት በስትያ ለማየት ተችሏል፡፡

ቤቶቹን ከኤጀንሲው እንደተከራዩ የሚናገሩና ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ግለሰቦች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ወ/ሮ ሶፊያና ወ/ሮ ሙሉን ጨምሮ አራት ሰፋፊ የንግድ ቤቶች ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ተይዟል፡፡ መመርያው በፍርድ ቤት የተያዘን ጉዳይ እንደማይመለከት ቢገልጽም፣ ኤጀንሲው ውል እንደተቋረጠ መግለጹ አግባብነት የለውም ይላሉ፡፡ በእርግጥም በአዋጁ ተራ ቁጥር አሥር፣ መመርያው ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ያለ ከሆነ፣ መመርያው ተፈጻሚ እንደማይሆን ይደነግጋል፡፡

የአትክልት ተራ ከሌሎች ገበያዎች ለምሳሌ ከመርካቶና ከሾላ ገበያ የሚለየው ተከራዮቹ ለሰዓታት ብቻ በቦታው ላይ ተቀምጠው ከነገዱ በኋላ የሚነሱ፣ እነሱም ከተነሱ በኋላ ሌሎች ነጋዴዎች ቦታውን ይዘው ንግዳቸውን የሚቀጥሉ በመሆኑ ነው፡፡ በዚህ ሒደትም በአንድ ቦታ ብቻ አራት ነጋዴዎች ከዋናው አከራይ ውጭ ተከራይተው የሚነግዱ በመሆኑ፣ አለመግባባቱን ከፍ እንዳደረገው የአካባቢውን የንግድ እንቅስቃሴ በቅርብ የሚያውቁ ነጋዴዎች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹መመርያው ከወጣ በኋላ አትክልት ተራ ሰላም የለውም፡፡ ሰላሙንም በቅርብ ያገኛል ብዬ አላምንም፤›› ሲል በአካባቢው በጊዜያዊነት ቦታ እየተከራየ የሚሠራው ኡስማን መሐመድ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

የፒያሳው አትክልት ተራ ሥራ ከጀመረ ከ50 ዓመታት በላይ እንዳስቆጠረ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ የቀበሌ፣ የግልና የኤጀንሲው ይዞታ በሆኑ 386 ቤቶች ሥራ የሚካሄድበት ይህ አካባቢ፣ ከ54 ዓመታት በኋላም የንግድ ማዕከላትን ሳይጨምር ወይም ማስፋፊያ ሳያካሄድበት 10 ሺሕ ነጋዴዎች በየዕለቱ ይርመሰመሱበታል፡፡
በአትክልት ተራ በእያንዳንዱ ቦታ ገንዘብ በኪራይ የሚገኝበት ሲሆን፣ በርካታ ሚሊዮን የብር ኖቶች በየዕለቱ የሚንቀሳቀሱበትና በቤተሰባዊ ግንኙነት፣ በኃይልና በገንዘብ ‹‹ኔትወርክ›› የተሳሰረ ሥራ የሚሠራበት አካባቢ እንደሆነም ይነገራል፡፡

በዚህ አካባቢ ዘመናዊ የንግድ ማዕከል ለመገንባት የተቋቋመው ቢስ አትክልትና አግሮ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ማኅበር በቦታው ላይ ባካሄደው ጥናት መሠረት ‹‹በአምባገነናዊ ስሜት ተፅዕኖ ሥር የሚገኝ የገበያ ስፍራ›› ይለዋል፡፡

በፒያሳ አትክልት ተራ ሌሊት የገባ አንድ አትክልት የጫነ መኪና እስከ 1200 ብር ይከፍላል፡፡ ተከራይ ነጋዴዎችም እንዲሁ በውድ የሚከራዩ ሲሆን፣ ይህ ያንገፈገፋቸው ተከራይ ነጋዴዎች የኔትወርኩን ሰንሰለት ለመበጣጠስ ጊዜው አሁን ነው ቢሉም፣ ነባር የኤጀንሲው ተከራዮች ደግሞ ላለፉት 35 ዓመታት ሲተዳደሩበት የቆዩት ንብረት እንዲሁ እንደዘበት ሲሄድ የተዋጠላቸው አይመስሉም፡፡

ከእነዚህ ውጭም በዚሁ ቦታ ውክልና ይዘው የሚያከራዩ ወይም ጉዳይ በማስፈጸም ኮሚሽን የሚያገኙ መኖራቸው የአደባባይ ሚስጥር እንደሆነ ይነገራል፡፡ እነዚህ አካላትም የዚሁ ቦታ ጥቅም ተቋዳሽ ለመሆን የግብግቡ ተሳታፊ ሆነዋል፡፡ ከዋናው የኤጀንሲው ተከራይ በስተቀር የንግድ ፈቃድ ያለው ባለመኖሩና ከእነዚህ ተከራዮችም በቋሚነት የመከራየት ልማድም ባለመኖሩ በአካባቢው የተነሳውን አለመግባባት አክርሮታል፡፡

የመንግሥት ቤቶች ኤጀንሲም ሆነ የቀበሌ ቤቶችን ተከራይተው ሸንሽነው ለሌላ ነጋዴ ባከራዩ ላይ መንግሥት የወሰደውን ዕርምጃ በሁለት መልኩ የሚመለከቱ አካላት ተፈጥረዋል፡፡ ግማሾቹ የመንግሥትን ዕርምጃ በፅንሰ ሐሳብ ደረጃ ትክክል መሆኑን ቢያምኑም፣ ትክክለኛ የተከራይ ተከራይ ወይም ቀጣይ የቤቱ ባለቤት መሆን የሚችልበት ግልጽ አሠራር ስለመኖሩ ይጠራጠራሉ፡፡

እነዚህ ግለሰቦች በአትክልት ተራ ከኤጀንሲው ጋር ውል ለመፈጸም እየተሯሯጡ የሚገኙት በእርግጥ እነማን ናቸው? ሲሉ ውስጥ አዋቂ እንደሆኑ የሚጠቁም ጥርጣሬያቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ በእጅ አዙር ንግድ ቤቶቹን ሊቆጣጠሩ የሚችሉበት መንገድ እንዳለም ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡