የቤዱዊን ጎሳዎች የኢትዮጵያ፣ የኤርትራና የሱዳን ስደተኞችን የውስጥ አካል እያወጡ እንደሚሸጡ ታወቀ
ሲ ኤን ኤን እንደዘገበው የሳይናይ በረሀን በማቋረጥ ወደ እስረኤል ለመጓዝ ሙከራ የሚያደርጉ ኢትዮጵያውያን፣ ሱዳንያውያንና ኤርትራዊያን አስፈላጊውን ክፍያ መፈጸም ካልቻሉ፣ የሆድ እቃቸው ተከፍቶ ኩላሊታቸው ና ጉበታቸው ከወጣ በሁዋላ፣ በዚያው እንዲሞቱ እንደሚደረጉ ዘግቧል።
ዘ ኒው ጄኔሬሺን ፋውንዴሽን ፎር ሁማን ራይትስ እናዘ ኤቭሪዋን ግሩፕ የተሰኙትን ድርጅቶች በመጥቀስ ሲኤን ኤን እንደዘገበው፣ ስደተኞቹ የተጠየቁትን በብዙ ሺ የሚቆጠር ክፍያ ለመፈጸም ካልቻሉ ወደ ሳይናይ በረሀ ይወሰዱና በህይወት እያሉ የሆድ እቃቸው በግብጽ ዶክተሮች ይከፈታል።
ስደተኞቹ ጉበታቸውና ኩላሊታቸው ከወጣ በሁዋላ ወዲያዉኑ እንደሚሞቱ፣ የስደተኞቹን አስከሬን በመመርመር ማረጋገጣቸውን ድርጅቶቹ ማረጋገጣቸውን የሲኤን ኤን ዘገባ ያመለክታል።
በቅርቡ በሳይናይ በረሀ የታሰሩ ከ70 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የድረሱልን ጥሪ ማሰማታቸውን መዘገባችን ይታወሳል። ባልታወቀ ስፍራ ታስረው ከሚገኙት ስደተኞች መካከል በርካታ ሴቶችና ወንዶች መደፈራቸውን፣ አንዳንዶች ህጻን ልጆችን የያዙ መሆናቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
አንድ ስደተኛ የሳይናይ በረሀን በማቋረጥ ወደ እስራኤል ለመግባት እስከ 20 ሺ ዶላር የሚደርስ ገንዘብ እንደሚጠዬቅ ስደተኞቹ ገልጠዋል።