“የሻዕቢያ ተላላኪ ኢህአዴግ ራሱ እንጂ መድረክ አይደለም” ሲል መድረክ ለአቶ መለስ የፓርላማ ፉከራ መልስ ሰጠ

“በሻዕቢያ ነጭ ለባሽነት የሚጠረጠሩትና ሀገር የሚያውቃቸው የኢህአዴግ መሪዎች ሆነው እያለ መድረክን በሻዕቢያ ነጭ ለባሽነት ከሰዋል” ሲል የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራስያዊ አንድነት መድረክ /መድረክ/ አስታወቀ፡፡ መድረክ ይህንን ያስታወቀው “በኢትዮጵያ ድርቅ አለ ! ረሀብ አለ! ኢኮኖሚውም መንግስት እንደሚለው እያደገ አይደለም! የፖለቲካ ምህዳሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠቧል” በማለት ሰሞኑን በላከልን መግለጫ ነው፡ ፡ መድረክ በመግለጫው እንደገለፀው “ኢህአዴግ ከሻዕቢያ ጋር ለመታረቅ እየተማፀነ ባለበት በአሁኑ ጊዜ የአልጀርሱ ስምምነት ይፍረስ የአሰብ ወደባችን ባለቤትነት በድርድር በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ይረጋገጥ እያለ የሚታገለውን ድርጅት የሻዕቢያ ተላላኪ አስመስሎ ማቅረብ የኢትዮጵያን ህዝብ በሻዕቢያ ላይ ያለውን ጥላቻ በመገንዘብ የሚሰራ ሥራ በመሆኑ አሳፋሪ ከመሆን ባለፈ ፋይዳ የለውም” ብሎአል፡፡

በመግለጫው “አገሪቱን በደመነፍስ እየመሩ በሀገሪቱ ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰ በኃላ “ሁኔታውን እያጣራን እርምጃ እንወስዳለን” ማለታቸውና “ተቃዋሚ ፓርቲዎች አማራጭ ፖሊሲ የላቸውም” የሚለው ፕሮፓጋንዳ “የግብርና መር ኢንዱስትሪያላይዜሽን” የሚለውን የኢህአዴግ የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተቃዋሚዎች ሲተቹና አማራጫቸውን ግብርናና ኢንዱስትሪው ጐን ለጐን እኩል ትኩረት ተሰጥቶአቸው ከአገልግሎት ዘርፉ ጭምር የሚስፋፋበት ፖሊሲ እንዲቀየስ ሲታገሉ እንዲቆዩ በዓለም ገንዘብ ድርጅትና በዓለም ባንክ አማካሪ መረጋገጡ የኢህአዴግ ፕሮፓጋንዳ እርቃኑን መቅረቱ ሊጤን ይገባል” ሲል ተችቷል፡፡

በመጨረሻም “ጠ/ሚኒስትሩ ወደ ፓርላማ በሚቀርብበትና ጋዜጣዊ መግለጫ በሚሰጡበት ጊዜ ሁሉ ተቃዋሚዎችን ለማሰርና ለማጥፋት እንደሚሹ ሳይገልጹ አያልፉም፡፡ ለኢህአዴግ ያላጐበደደ ተቃዋሚና ነፃ ጋዜጠኛን ይረግማሉ፣ ይዘልፉሉ ዛቻና ማስፈራሪያ ይሰጣሉ፡፡ ይህ ሁሉ ሙስናን መዋጋት ባለመፈለጋቸው መልካም አስተዳደርን ማስፈን ባለመቻላቸው ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብትን ማክበር ባለመቻላቸው ሲሆን ለዚህም ተጠያቂውና ኃላፊው አገዛዛቸው ነው” ብሎአል፡፡

ምንጭ