ጋዳፊ ተገደሉ፤ መለስ ይፎክራል፤ ህዝብ ተማሯል!!!

ጥቅምት ወር ሲመጣ … “በግንቦት 7 1997 የሰጠነው የምርጫ ድምፃችን ይቆጠርልን!” በማለታቸው በጥቅምት 1998 ዓ.ም. በአዲስ አበባና ሌሎችም ከተሞች ጎዳናዎች በአጋዚ ጥይት በግፍ  የተገደሉ፤ ለአካል ጉዳት የተዳረጉ፤ የተደበደቡ እና የተጋዙ ወገኖቻችንን በሃዘንና በቁጭት እናስታውሳለን።

ዘንድሮ የጥቅምት 98 ሰማዕታትን በምንዘክርበት ወቅት ሶስት አዳዲስ ኩነቶች ተደራርበው መጥተዋል። እነዚህ ኩነቶች የተለያዩ ቢመስሉም በአንድነት ሲጤኑ እየሄድንበት ያለውን መንገድ የሚያሳዩ በመሆናቸው አዛምደን ልናቀርባቸው ወሰነን።

1. የሊቢያው ጋዳፊ አብዝተው ፎክረው ነበር፤ ግን ተዋርደው ተገደሉ

የሊቢያው ኮሎኔል ሙዓመር ጋዳፊ አብዮተኖችን “አይጦች፣ በረሮች፣ ሃሽሻሞች፣ ዱሪየዎች በመሆናቸው ቤት ለቤት እየሄዳችሁ፣ እያሳደዳችሁ ግደሏቸው!” ሲሉ “ይወደኛል” ለሚሉት ህዝብ ትዕዛዝ ሰጥተው ነበር። ሆኖም ግን ይነሳልኛል ያሉት ህዝብ ተነስቶባቸው በያዝነው ጥቅምት ወር ታሪካቸው በአሳዛኝ አጨራረስ ተደመደመ። ጋዳፊ እጎርፍ መውረጃ ቱቦ ውስጥ ተያዙ፣ ቆሰሉ፣ ተጎተቱ፣ ተዋረዱ፣ ሞቱ። ልጆቻቸውም ከፊሉ ተገደሉ፤ ሌሎቹ ተሰደዱ። አልጋቸውን ይወርሳል ይባል የነበረው ሰይፍ አል-ኢስላም ሄይግ ለሚገኘው ዓለም ዓቀፍ ችሎት እጁን ለመስጠት እየተደራደረ  ነው የሚል  ወሬ እየነፈሰ ነው።

2. መለስ ዜናዊ አብዝቶ  እየፎከረ ነው

ሰሞኑን ዘረኛው መለስ ዜናዊ እንደ ጋዳፊ ሁሉ በትዕቢት፣ ድንፋታ፣ ዛቻና ማስፈራሪያ የታጀበ ንግግር አድርጓል። እሱም ልክ እንደጋዳፊ ጋዜጠኞችንና የተቃዋሚ ፓርቲዎች መሪዎችን “ጋጠ ወጦችና ወንጀለኞች” እያለ ሁሉም ሰብስቦ ማሰር እንደሚችል ዝቷል። “የሚንጣጡ ጋዜጠኞች” አርፈው እንዲቀመጡም አስጠንቅቋል። መለስ ዜናዊ ልክ እንደ ጋዳፊ ቃላት አይመርጥም። አረንጓዴውን መጽሃፍ ከማገላበጥ በስተቀር ጋዳፊን ለመሆን የቀረው ነገር የለም።

3. የህዝብ ምሬት መገንፈል ጀምሯል

በደቡብ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግሥት በዳውሮ ዞን የሚገኘው የዋካ ከተማ ህዝብ በአስተዳደር በደል፣ በኑሮ ውድነትና በወረዳ  አከላል መነሻነት ተቃውሞ ቀስቅሷል። የዞኑ ካድሬዎች “በእያንዳንዳችሁ በር ላይ ድንኳን ይተከላል፤ ሞት ይዘራባችኋል!” እያሉ ቢያስፈራሩም ህዝቡ ግን “የመብት ጥያቄዎችን ከመጠየቅ ወደኋላ አንልም” ብሎዓል።  ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፤ ዋካ በፌደራል ፓሊስ ተወራለች።  በአርባ ምንጭም ከወራት በፊት የተቀሰቀሰው ተቃውሞ እስካሁን አልበረደም። በየቦታው ዜጎች እየታሰሩና እየተደበደቡ ቢሆንም ትግሉ ቀጥሏል። በመላ ሃገሪቱ ቁጭትና ምሬት በዝቷል።

የመለስ ዜናዊ አገዛዝ በሃይማኖት ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ እየገባ ምዕመናንን ለማበጣበጥ የሚያደርገው ጥረት እጅግ መራር የሆነ ተቃውሞን እየፈጠረ ነው። በአሁኑ ሰዓት በተለይ በእስልምና እምነት ውስጥ የሚደረገው ጣልቃ ገብነትና ፍረጃ ሞስሊሙን ማኅበረሰብ በእጅጉ አስቆጥቷል።

ከላይ የሰፈሩት ሶስት ነገሮች – የጋዳፊ የውርደት ሞት፤ የመለስ ዜናዊ ፉከራ እና እየተጠናከረ የመጣው የህዝብ ተቃውሞ – ከጥቅምት 98 ሰማዕታት ዝክር ጋር በአንድነት ሲታዩ  የሚሰጠን አንድ አጠቃላይ ምስል አለ።

በመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ ለሃያ ዓመታት ተረግጠናል፤ ተዋርደናል፤ ተገድለናል። በሰላማዊ መንገድ መሪዎቻችንን ለመምረጥ የነበረን ህልም ተከርችሞ መዘጋቱ ካረጋገጥን እነሆ ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል። ሰማዕቶቻችንን የተሰውለት ዓላማ እስካሁን እግብ አለመድረሱ ይቆጨናል። ሆኖም ግን ሁኔታዎች እየተቀየሩ ነው።

ከመለስ ዜናዊ በላይ ያቅራሩና የፎከሩ አምባገነኖችም ተገርስሰዋል። ከሃያ አመታት በላይ ተቀጥቅጠው የተገዙ የቱኒዚያ፣ የግብጽና የሊቢያ ህዝቦች ዛሬ ነፃነታቸውን አረጋግጠዋል።

እኛም ዘንድ ፍንጮች እየታዩ  ነው።  “እኔ ምን አቅም አለኝ” የሚባልበት ወቅት አልፏል። የመለስ ዜናዊ የማስፈራሪያ “የፀረ-ሽብር” ህግ መሳለቂያ ሆኗል። “ለነፃነትና ለፍትህ መቆም ‘ሽብርተኛ’ የሚያስብል ከሆነ “እኔም ሽብርተኛ ነኝ” የሚሉ ድምፆች ከየአቅጣጫው እየተሰሙ ነው።  በመለስ “የፀረ-ሽብር” ህግ የተከሰሱ ዜጎች ህዝብ “የነፃነት አርበኞች” እያለ ይጠራቸዋል።

ሁላችንም አንዱዓለም አራጌዎች፣ ሁላችንም እስክንድር ነጋዎች፤ ሁላችንም ደበበ እሸቱዎች፤ ሁላችንም ውብሸት ታዬዎች፣ ሁላችንም ርዕዮት ዓለሙዎች፣ ሁላችንም ስለሺ ሀጎሶች፣ ሁላችንም በቀለ ድሪባዎች፤ ሁላችንም ኦልባና ሌሊሳዎች ነን። አሁን ሁላችንም እስረኞች ነን።  በቅርቡ ግን እስር ቤቶቻችንን ሰብረን ነፃ እንወጣለን!!!

የሚል ድምጽ ከየአቅጣጫው እየተሰማ ነው።

በአርባ ምንጭና በዋካ እንዳየነው የህዝባዊ እምቢተኝነት ፍንጮች እዚህም እዚያም እየታዩ ነው። ዛሬ እነዚህ  የተናጠል እርምጃዎች ቢመስሉም በአፋጣኝ መቀናጀታቸው አይቀርም። በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ እንዲመጣ የሚፈልግ ዜጋ ሁሉ “የኔ ተሳትፎ ኢምንት ነው” ሳይል በተቻለው ሁሉ ትግሉን የሚያግዝበት ወቅት ላይ ደርሰናል ብሎ  ግንቦት 7  የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ያምናል።

ትናንሽ ነውጦች ሲጠራቀሙ ታላቁን ማዕበል አስነስተው ለመለስ ዜናዊ ትዕቢት የመጨረሻውን እልባት ይሰጣሉ ብሎ ግንቦት 7 በጽኑ ያምናል። ማዕበሉ እየመጣ ነው!!!

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!!