ማሃሙድ ጋ ጠብቂኝ! [ክፍል አንድ]
(መሀመድ ሰልማን)
ስብሓት “ትኩሳት” ብሎ በጠራው መጽሐፉ ጀርባ ላይ ምን አለ? “ወጣት ሁን” አለ፡፡ ቢመርህ “ሪቮሉሽን” ታስነሳለህ፣ እጅግ ቢመርህ ራስህን ታጠፋለህ…፡፡ ለማንኛውም ወጣት ሁን፡፡ እኔ ግን እልኻለሁ፣ ወጣት መሆኑን ሁን፣ ነገር ግን ራስህን ከማጥፋትህ በፊት ፒያሳ ሂድ፤ ሐሳብህን ልትቀይር ትችላለህና፡፡ ለመሞትም ቢሆን የፒያሳን ያህል መልካም ሰፈር የለም፡፡ ቀባሪ አታጣም፤ በፒያሳ ሰው ባያይህ ማዘጋጃ ያይኻል፡፡ ለመሞትም ለመኖርም ስታስብ ፒያሳ ሂድ፡፡
ፒያሳን ለሞትም ቢሆን የምመርጥልህ ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ሞት ሞት የሚሸት ስም በድፍን አዲስ አበባ የምታገኘውም ፒያሳ ነው፡፡ “ዶሮ ማነቂያ” ና “እሪ በከንቱ”ን እንደናሙና ውሰድ፡፡ ‹‹ተረት ሰፈር››ም አንተን ተረት ለማድረግ በሚያስችሉ ሕይወቶች የተሞላ መንደር ነው፤ ተረት መሆን ከፈለግህ፡፡ ፒያሳ ሥጋን ብቻ ሳይሆን ነፍስን ለማጥፋት ጭምር ምርጥ ሰፈር ናት፡፡ ካላመንክ ሙትና ሞክረው፡፡ ነግቶ ሳይመሽ ማዘጋጃ ይቀብርኻል፡፡ ስራ ለማቅለል ከፈለክ ደግሞ እዚያው ማዘጋጃ በር ላይ ጠጋ ብለህ ራስህን መድፋት ትችላለህ፡፡
ፒያሳ ወደ ሕይወትም ልትመልስህ ትችላለች፡፡ “እንዴት?” በለኝ፡፡ ወጣት ነህና ስብሓት በመከረህ መሰረት ራስህን የማጥፋት መብትህን ለመጠቀም ወደ ፒያሳ መጣህ እንበል፡፡ የት ጋር መሞት እንዳለብህ ለመምረጥ በፒያሳ ዞር ዞር ስትል እመነኝ ልብ የምታጠፋ ቆንጆ ታያለህ፡፡ ፀጉሯ የሚዘናፈል፣ ዳሌዋ የሚደንስ፣ ጡቶቿ የሚስቁ… መኖር የምታስመኝ ቆንጆ ልቅም ያለች ውብ 13 ቁጥር አውቶብስ ስትጠብቅ ታያታለህ፡፡ በዚህን ጊዜ ልብህ ይሸፍትና አንተም የተፈጥሮ ሞትህን መጠበቅ እንዳለብህ ትረዳለኽ፡፡ ከዚያች ቅፅበት ጀምሮ የ13 ቁጥር አውቶብስ ቋሚ ደንበኛ ሆነህ ታርፈዋለህ፡፡ አውቶብስና ሞት በራሳቸው ሰዓት እስኪመጡ ትጠብቃለህ። ፒያሳ ወደ ሕይወት መለሰችህ ማለት አይደል?
የፒያሳ ካፌዎች
ፒያሳ አንድ ሺህ አንድ መቶ ካፌዎች ያሉባት ቅመም የሆነች ሰፈር ናት፡፡ አንድ ሺህ አንድ መቶ ቆንጆ ልጃገረዶች ደግሞ በካፌዎቿ ውስጥ ተኮልኩለው ኮካ በ‹‹ስትሮ›› ይጠጣሉ፡፡ ‹‹ስትሮ›› ምን እንደሆነ ካላወቅክ የፒያሳ ልጅ አይደለህም ማለት ነው፡፡ ‹‹ስትሮ›› በቆንጆ ልጅ ከንፈርና በቆንጆ ብርጭቆ መሀል የተሰራ የላስቲክ ድልድይ ነው፡፡
ፒያሳ በካፌ ብዛት “ከምስራቅ አፍሪካ አንደኛ ናት፡፡” የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ነው እንዲህ ያለው ይባላል፡፡ እንደ ፒያሳ በካፌ የተጥለቀለቀ ሰፈር ከየት ይገኛል?! ከአምፒር እስከ ራስ መኮንን ድልድይ ብቻ በግራና በቀኝ የተሰለፉ ከ53 በላይ ካፌዎችን ልቆጥርልህ እችላለሁ፡፡ በእርግጥ ቆንጆ ልጃገረዶችና ወርቅ ቤቶች በመሀል በመሀል እየገቡ ቆጠራዬን አስተጓጉለዉት ይሆናል፡፡ ሆኖም ቁጥራቸው ከዚህ ቢልቅ እንጂ አያንስም፡፡
የፒያሳ ካፌዎች ልዩ ገፅታ ሁልጊዜ ሙሉ መሆናቸው ነው፡፡ አንዳንድ የፒያሳ ምሁራን ይህንን ጉዳይ ከመንግሥት የትምህርት ፖሊሲ ጋር ሊያይዙት ይሞክራሉ፡፡ እኔ ግን እላለሁ፤ ይህ የፒያሳ ልዩ ከራማ እንጂ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም፡፡
በፒያሳ ምርጥ ቡና ጠጥተህ ቀንህን ብሩህ ለማድረግ ካሻህ እነማንኪራ፣ እነ አፍሪካ፣ እነ ቶሞካ አሉልህ…፡፡ ቆንጆ ሻይ ከቆንጆ ልጃገረዶች ጋር ተፋጠህ ፉት ለማለት ካሻህ እነ ናምሩድ፣ እነ ራዜል፣ እነ ኢቪያን፣ እነ ሳሬም፣ እነ ኦስሎ፣ እነ አፕቪው፣ እነ ዲጄስ፣ እነ ሃርድኮር፣ እነ ጉድታይምስ አሉልህ፡፡ በተለይ በቅርቡ የተከፈተው ጉድ ታይምስ እንደ ደብልፌስ ጃኬት አይነት ተፈጥሮ ነበረው፡፡ ቀን ላይ ውብ ካፌ ኾኖ ይቆይና ማታ ላይ በፍጥነት ራሱን ቀይሮ ውብ ባር የመሆን ልዩ ጥበብ ነበረው፡፡ የጨርቆስ ልጆች ያለ ሰፈራቸው መጥተው በቡዳ በሉት መሰለኝ ሰሞኑን ተቃጠለ አሉ፡፡ ነፍስ ይማር!
ፎቅ ላይ ቂብ ብለህ ፒያሳንና ዜጎቿን ቁልቁል እየገረመምካቸው ለመዝናናት ካሻህ አራዳ ላይ የተሰቀሉ መዝናኛዎች አሉልህ፡፡ እነ አራዳ፣ እነ ሲድኒ፣ እነ ትዊንስ፣ እነ ቤስት በፒያሳ ከባህር ጠለል በላይ በምናምን ሺህ ጫማ ከፍታ የሚገኙ ካፌዎች ናቸው፡፡ አለልህ ደግሞ እንደ ዳሎል ተቀብሮ ያለ ካፌ፡፡ ቼንትሮ ይሰኛል፡፡
ልምከርህ! ፍቅረኛህ ፒዛ አማረኝ ካለችህ ፒያሳ ‹‹ፒዛ ኮርነር›› ውሰዳት፤ ከዚያ በኋላ ምን አለ በለኝ ፍቅሯ ካልጨመረ፡፡ ከዚህ ግብዣ በኋላ ካኮረፈችህ ግን ፒዛውን በልተህባታል ማለት ነው፡፡
ፒያሳ የኬክ አገር ናት፡፡ ዕድሜ ጠገቦቹን ….በዚህ አጋጣሚ ስማቸውን ማውሳት ግድ ይላል፡፡ በተለይ የ‹‹ኤንሪኮ›› ኬክ ይምጣብኝ፡፡ እስኪ በሞቴ ከዚህ ቤት ሂድና ኬክ እዘዝ፡፡ ኪኒን ኪኒን የሚያካክሉ ኬኮች ይቀርቡልኻል፡፡ የፒያሳ ልጅ ካልኾንክ ታኮርፋለህ፡፡ አንተ የለመድከው ድፎ ዳቦ የሚያካክሉ ኬኮችን ነዋ፡፡ እስኪ በሞቴ ቅመሰው፡፡ ከዚያ በአድናቆት ጭንቅላትህን ትወዘውዘዋለህ፡፡ ካልጣመህ ግን በኬክ አላደክም ማለት ነው፡፡ሂድና ሸዋ ዳቦ ተሰለፍ፡፡
ኤንሪኮ ውስጥ ዞር ዞር ብለህ ከጎንህ ያለውን ሰውዬ ገልመጥ ለማድረግ ሞክር፡፡ የሆነ ሰውዬ በትኩረት ኬክ ሲበላ ታየዋለህ፡፡ በእርግጠኝነት ስለሰውየው ብትጠይቅ ከተማዋ ውስጥ ካየኻቸው ሰማይ ጠቀስ ፎቆች የአንዱ ባለቤት ሆኖ ታገኘዋለህ፡፡ ፎቅ ባይኖረው እንኳ ፎቅ የሚሰራ ብር ያለው ለመሆኑ አትጠራጠር፡፡ ይህም ባይኖረው አንድ ቀን የማግኘት ተስፋ ያለው ነው። የኤንሪኮ የውስጥ ገፅታ አለመብለጭለጭ ተራ ቤት እንደሆነ ሊያስገምትህ ይችላል፡፡ አንድ ነገር ግን ላረጋግጥልህ፣ ይህ ቤት የሞጃዎች መናኸሪያ ነው፡፡ ስለዚህ አትንቀዥቀዥ፡፡

ከኤንሪኮ በኬክ መጋገር ጥበብ ተደንቀህ ስትወጣ ከፊት ለፊትህ የምታገኘው ‹‹እናት ህንፃ››ን ይሆናል፡፡ ይህ ህንጻ በቅርቡ ፒያሳን ከተቀላቀሉ ድንቅ ፎቆች አንዱና ዋንኛው ነው፡፡ በስነ -ህንፃ ታሪክ በምስራቅ አፍሪካ አንደኛ ከመሆኑም በላይ የሚመስለው የለም እየተባለ ነው፡፡ የፒያሳ ልጅ ካልኾንክ ይህን ህንፃ ተደግፈህ ፎቶ ብትነሳና ክፍለ ሀገር ላሉ ዘመዶችህ ብትልክላቸው ልጃችን አሜሪካ ገባ ብለው ድግስ እንደሚደግሱ አትጠራጠር፡፡ አዲስ አበባ ውብ ሕንጻ እንደሌለ የሚያስቡ ዲያስፖራዎችም ቢሆኑ እነሱ በማያውቁት አንድ የአውሮፓ ከተማ ያለ ሊመስላቸው ይችላል። (ካላመንከኝ ፎቶውን ተመልከት)
“ማሃሙድ ጋ ጠብቂኝ!”
አይበለውና ፒያሳ ሳለህ ድንገት ስሜትህ ቢመጣ እንደኔ የጨዋ ልጅ ከሆንክ ስልክህን በርበር አድርገህ ትደውልና እጩ ፍቅረኛህን ”ማሃሙድ ጋ ጠብቂኝ” ትላታለህ፡፡ “ኢንተር ላንጋኖ” ወስደህ፣ በድብቆቹ የስሞሽ ግርዶሽ ተጠልለህ፣ ልብ የሚሰልብ የስሞሽ ስነ ስርዓት ትፈፅማለህ፡፡ ከ”ማህሙድ ሙዚቃ ቤት” እስከ “ኢንተር ላንጋኖ” ለመሄድ የሦስት ደቂቃ ትእግስት ካጣኽ ፒያሳ ውላ ትግባ እንጂ ምን ጠፍቶ! በ”አምፒር” ወደ “ዶሮ ማነቂያ” ገባ እንዳልክ “ትሬይን ሀውስ” አለልህ፡፡ ይህ ቤት መሳሳሚያ ብቻ አይደለም ያዘጋጀልህ፡፡ አይበለውና ስሜትህ ከንፈር ብቻ የማያስታግሰው ከሆነብህ ይህ ቤት እጥር ምጥን ያለ ክፍል እጥር ምጥን ላለ ሰዓት ያከራይኻል፡፡ ፒያሳ ነው ያለኸው፡፡ ብታምነኝም ባታምነኝም ፒያሳ ከ10 በላይ መሳሳሚያ ቤቶችን በጉያዋ ይዛለች፡፡ ብዙዎቹ ስም አልባ ናቸው፡፡ ልብህ ከሚቆም አንድ አምስቱን ልጠቁምህ (ሊሞት የመጣን ሰው ወደ ሕይወት ለመመለስ አምስት መሳሳሚያ መቼ አነሰው?)፤ “ኢንተር ላንጋኖ”፣ “ትሬይን ሃውስ”፣ “ቢግ ትሪ”፣ “ጊቤ”፣ “ቬሮኒካ”…
“ማህሙድ ጋ” ቀጠሮ መያዝ እጅግ የሚመከር እንደሆነ በዚህ አጋጣሚ ሳልነግርህ አላልፍም፡፡ “ለምን?” በለኝ፡፡ አንደኛ ከማህሙድ ሙዚቃ ቤት የሚለቀቁ የማህሙድ ትዝታዎች በቀጠሮ ያስደገፈችህን ልጂትና ያደረሰችብህን ብስጭት የማስታገስ ኀይል አላቸው፡፡ አንዳንዴ ደግሞ የማህሙድ ወዳጅ የነበረው ጥላሁን ‹‹ቀጠሮ ይከበር›› ሲል ያንጎራጎረውን ዜማ ሊከፍቱልህ ይችላሉ፡፡ ሁለተኛ ‹‹ማሃሙድ ጋ›› አስተውለህ ከሆነ ብዙ ቆነጃጅት ብዙ ኮበሌዎችን ቆመው የሚጠብቁበት ስፍራ ነው፡፡ ዕድለኛ ከሆንክ ፍቅረኛዋ ቀርቶባት የተበሳጨችን ልጃገረድ ይዘህ እብስ ልትል ትችላለህ፡፡
ቀጠሮ ቦታ ሴቶች ቢያንስ ሰላሳ ደቂቃ አርፍደው እንደሚገኙ ሳታስተውል አልቀረህም፡፡ ማህሙድ ጋ ግን ለምን እንደሆነ ባላውቅም አረፈዱ ቢባል 20 ደቂቃ ነው፡፡ ቢያረፍዱብህም ከፊት ለፊትህ ብዙ የሚታይና የሚያዘናጋ ነገር አታጣም፡፡ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል ትልቁ የሀገራችን የህዝብ ሽንት ቤት የሚገኘው “ማህሙድ ሙዚቃ ቤት” ማዶ ነው፡፡ በቀን ሦስት ሺህ ሰዎች ይሳለሙታል፡፡ ሽንታቸው እንዳያመልጣቸው የሰጉ አዛውንት ምንትሳቸውን በእጃቸው ደግፈው ወደዚህ ሽንት ቤት እየተወላገዱ ሲገቡ እያየህ መሳቅ ትችላለህ፡፡ ከፈለክ “ሰው የተፈጥሮን ጥሪ ለመመለስ እንደሚጣደፈው ለቀጠሮም ምን አለ ተመሳሳይ ጥድፊያ ቢያሳይ” እያልክ ትፈላሰፋለህ፡፡
ሽንት ያጣደፋቸውን ምእመናን ማየት ከሰለቸህ ቀና በል፡፡ አይንህ ከሕዝብ ሽንት ቤት ወደ ሕዝብ ሶኒክ ስክሪን ይወረወራል፡፡ ፒያሳ በቅርቡ ራሷን ከእህት ከተሞች ጋር ለማስተካከል ያስተከለችው ይህ ትልቅ ዲጂታል ስክሪን የማያሳይህ ነገር የለም፡፡ ከቶሚና ጄሪ አባሮሽ ጀምሮ እስከ ሕገ መንግሥቱ አንቀጾች ይተነትንልኻል፡፡ ሕገ መንግሥቱ የብሔር ብሔረሰቦችን እኩልነት እንዴት እንዳስከበረ ካልገባህ አንቀጽ በአንቀጽ ያስረዳኻል፤ ትንሽ ከቆየህም የሴቶች እኩልነት በአገራችን በአያሌው እየሰፈነ እንደሆነ ያሳይኻል፤ ይሄኔ ከሴት ጓደኛህ ጋር የያዝከው ቀጠሮህ ትዝ ይልኻል፡፡ ሶኒክ ስክሪኑ ላይ በሚታየው የሕገ መንግስቱ አንቀጽ ውስጥ እንዲህ የሚል ነገር እንዲካተትልህ ትመኛለህ፡፡ ‹‹የሴቶች እኩልነት ቀጠሮ በማክበርም ጭምር ይረጋገጥ።››
አይንህን ከሶኒክ ስክሪኑ ስትነቅል የቀጠርካት ልጅ አበባ መስላ ከተፍ ትላለች፡፡ ጉንጮችህን ሳም ሳም፣ እቅፍ እቅፍ ስታደርግህ ንዴትህ ድራሹኑ ይጠፋል፡፡ ጭራሽ ቀጠሮ ማርፈዷ ተዘንግቶህ አንተው ራስህ “አረፈድኩብሽ አይደል” ልትል ይቃጣኻል፡፡ ፒያሳ! (ክፍል ሁለት ይቀጥላል)
