ይድርስ ግንቦት ሰባት ይድረስ
ከሎሬት ጸጋዬ ገብረመድን በጦቢያ መጽሄት ቅጽ 12 ቁጥር 10 ግንቦት ወር 1997 ወጥቶ ከነበረ የተወሰደ
ይድርስ ግንቦት ሰባት ይድረስ
እናት ዓለም ግንቦት ሰባት፣ ተራሮችሽ ተሰለፋ!
ግንቦት ሃያን አሳፈሩ! በድል ድባብ ተንሳፈፉ
የጥላቻን ዓይን ጥላ፣ በአንድነታቸው ገፈፉ
ትውልድሽ እምቦቀቅላሽ፣ በአገር ፍቅር ተቃቀፉ
የኢትዮጵያዊነትን ማተብ፣ በቁርጥ ቃል አበሰሩ
የምስራች ተቀዳጁ! የምስራች ተባበሩ።
እናት ዓለም ግንቦት ሰባት፣ ትውልድሽ ቆሞ በፅናት
መሰከሩ ሰማዕታት፣
የልጆችሽን ትንሳኤ፣ ከአፅናፍ አፅናፍ ፀሃይ ሞቀው
ዓለም አየው! ጠላት ለየው!
የአባቶቹ ወኔ ደሙን፣ ኢትዮጵያዊነቱን ጫረው
ማንም ሰው ሳያስገድደው፣ ህዝባዊነቱን ገለፀው
ማንነቱን መሰከረው
ሣር ቅጠሉን አለበሰው፣ አደባባዩን ሸፈነው
ሰማዩን አጥለቀለቀው፣ ዓለምን አስጠነቀረው፤
እሰይ! እሰይ! ሞት ፍርሃት! እሰይ! እሰይ! በራ ንጋት
የምስራች የኢትዮጵያ ሕዝብ! ክብሩ ሞቱ ለሰማእታት!
በድባብ ሂጅ የኢትይጵያ እናት፤ ክብርህ ይስፋ የኢትዮጵያ አባት
ተባረክ የኢትዮጵያ ወጣት፤ተመንደግ የኢትዮጵያ ህፃናት!
እንኳን! እንኳን የኢትዮጵያ አምላክ፣ አበቃን ለድል ብስራት!
ሕዝብ ሆይ ከግንቦት ስምንት፣ የባንዶች አዋጅ ተጠንቀቅ
በምርጫህ በድምፅህ ትግል፣ የያዝካትን ድል አትልቀቅ!
የሕዝባዊ ሥልጣንክን ግብ፣ የዴሞክራሲህን ብቅል
በአዋጅና በጠመንጃ፣ በማስፈራራት እንዳትጥል!
ይልቅንስ ሰልፍህን ቀጥል!
ባለቤቱ አንተ ነህና፣ ለባንዲራውም ለአገሩም
በሰልፍህ ላይ ዳግም ዘብ ቁም!
የህዝብ ሰልፍ! የህዝብ ቃል!
እንኳንስ የባንዳን አዋጅ፣ ተራሮችን ያነቃንቃል።
ሰማይ ምድር ያናውጣል።
የምስራች የኢትዮጵያ ሕዝብ! እልል! እልል! እልል! እልል!
ከእንግዲህ አንኳንስ አዋጅ፣ እንኳንስ የታንክ ቁልል
እንኳንስ የድምፅ ሌባ፣ እንኳንስ የእስታሊን ቅጥል
ማንም ሃያል አይገድብህም፣ ባንዳ ሺ ጊዜ ቢፏልል፣
በሰላም ጥሰሃልና፣ የምዕራፍ አንድን እክል
በመንፈስ ታጥቀሃልና፣ ለምዕራፍ ሁለት ድል
ማንም ሃይል አይገድብህም፣ መለስ የሞት ጣር ቢያቃጭል
እንኳንስ አዋጅ! ኡኡ! ቢል!…
ይድረስ ግንቦት ሰባት ይድረስ! በሕዝባችን ቆራጥ መንፈስ!
ዘረኛው ጎጥ አይኑ እስኪፈርስ!
የሠልፍ ድል ይንቀሳቀስ።
አዲስ አበባን ከአደጋ፣ ኢትዮጵያን ከጎጥ መንጋጋ
መንጭቆ ከጅብ አፍ ስጋ
ያወጣትን የሕዝብ ሠልፍ
መለስ በጠመንጃ እንዳይጠልፍ፣
የሰልፍ ድል ይንቀሳቀስ።
የምርጫ ሳጥን እንደ አይጥ፣ ቦርቡሮ እንዳይጨርስ በውስጥ
ጊዜ ገዝቶ በድለላ፣ ተቃዋሚውን እንዳይለውጥ፣
የሰልፍ ድል ይንቀሳቀስ።
የተቃማዊዎች ወገን፣ ተደጋግፈህ ተዋህደህ
እንደ አንድ አካል ፀንተህ ቆመህ፣
የሰልፍ ድል ይንቀሳቀስ።
ፅና! ተቃዋሚ ፅና! በሕዝባዊ ቃልህ ሚና፣
ሕብረቱ ከትግራይ ምርጫ፣ ሲባረር በአፈሙዝ ጫና
ያለአንዳች ተወዳዳሪ፣ ዓድዋ ላይ መለስ ሲቅናና
የትግራይ ወጣት ውርደቱን፣ አልቀበል ብሎ በቁርጥ
ድረስልኝ ሲልህ በግልጥ
ምርጫው በሰላም ዳግመኛ፣ እንዲካሄድ እንደገና
የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ፣ ጮሆ ጠይቆሃልና
ፅና! ተቃዋሚም ፅና! በህዝባዊ ቃልህ ሚና
ስበር የመለስን ጫና። ….
በራሱ ልሳን ነግረኸው፣ ካነቀው የራሱ ላንቃ
አትድከም ቋንቋ ሽምቀቃ
ንገረው በጭራቁ ቋንቋ፣ ንገረው በአባትህ ቋንቋ
ምከረው በአፋር በኢሣ፣ ድገመው በወላኢታ
ሰልሰው በኦሮሚፋ፣ አጥምቀው በኩሎ ኮንታ
አላ ሙድን እስኪረት! ካርተር ውሸቱ እስኪገታ!
ወያኔ ነፃ እስኪወጣ፣ ከዘረኝነተ እመቃ
ንገረው በአባትህ ቋንቋ። ንገረው በእናትህ ቋንቋ። ….
በዘውድም ሆነ በደርጉ፣ ዛሬም በወያኔው አገር
ሰምተነው አናውቅም ሕዝቡን፣ በአባቱ ቃል ሲነጋገር፣
ነፃ አወጣንህ እያልነው፣ ድምፁን ከመሸምቀቅ በቀር።
በአፍ ልማድ ማደንቆር ለምደን፣ ሥልጣን የህዝብ ነው ብለን
ዋሽተን በብልጠት ሕዝቡን ሸንግለን
ለጎምነው እንጅ ልሳኑን፣ አልሰጠነውም ስልጣኑን
አልሰማነውም የአባቱን፣…
ፅና! ተቃዋሚ ፅና! በሕዝባዊ ቃልህ ሚና
ስበር የመለስ ጫና።
እናት አለም ግንቦት ሰባት፣ ተራሮችሽ ተሰለፉ
ግንቦት ሃያን አሳፈሩ፣ በድል ድባብ ተንሳፈፉ
የጥላቻ ዓይነ ጥላ፣ በአንድነታቸው ገፈፉ
ትውልድሽ እምቦቀቅላሽ፣ በአገር ፍቅር ተቃቀፉ
የኢትዮጵያዊነትን ማተብ፣ በቁርጥ ቃል አበሰሩ
የምስራች ተቀናጁ! የምስራች ተባበሩ።