የእኛኑ ገሀነብ ማን እንዲያፈርስልን?

የእኛኑ ገሀነብ ማን እንዲያፈርስልን?

እፉኝ ነኝ እንዴ

ወፍ ዘራሽ መደዴ

በንፋስ አቅጣጫ  ሚወሰን መንገዴ።

ብናኝ አቧራ ነኝ? ከጠጠር የከሳ

እፍ ባሉት ቁጥር በኖ የሚነሳ ።

ቆሻሻ ነኝ እንዴ? የምድር ላይ ጥራጊ

ከግም ከብስብሱ አንድ ላይ ታሻጊ።

አረም ነኝ ወይ እንዴ? ተመዝዤ እምጣል

የማበብ መብት ያጣሁ ከፍጥረታት መሃከል።

እንዴት ልገልጸው ነው ሰውነት የኔን

የክብር አቅል አጥቶ  የቀለለውን

መያዣው ጠፍቶበት እሚባክነውን

ንቀሉኝ፣ ጥረጉኝ፣ እፍ በሉኝ ብሎ  እጅ የሰጠውን።

በፈጣሪ ምስል ሁሉን ተከሽኖ

በአንድየው ሲቀመር  ፍጥረት በእኩል ገኖ

ድንገት ሸርተት ብሎ፣ አንዱ አሳሪ ሆኖ የቀረው ታሳሪ

አንዱ ተለጉሞ   ሌላው ተናጋሪ

ምንድነው ታምሩ? ያንዱ ሆዱ ሞልቶ ላይ ታቹ ሲያፈስ

አዋይ በሌላው ቤት ቦዶ ሌማት አቅፋ አምራ ምታለቅስ

አንዱ የመነመነ፣ በረሃብ ዋግምቶች ደሙ የተበጣ

ሌላው ጥጋብ ነፍቶት የሚሰራው ያጣ።

አንዱ አገር አልባ  የስደት ምርኮኛ

ሌላው ሳር ቅጠሉን፣ ምድርና ሰማዩን አቅፎ የሚተኛ

የከርሰ ምድሩ ሃብት፣ የወንዝ ሸንተረሩ፣ ባለቤት ቀማኛ

በእጽዋት በንስሳው፣ በሰው በፍጥረታት ላይ ፈላጭ ቆራጭ ዳኛ።

ምንድነው ሚስጥሩ አንዱ ሃር ለባሽ

ባልማዝ በፈርጥ አጊያጭ በሽቶ ተንበሽባሽ

ደረቱን ገልብጦ ባለም ፊት ጋላቢ

ሌላው  አንገት ደፊ፣ አሮጌ ነጠላ በእድፍ ላይ ደራቢ

ጠኔ እግር ነስቶት በደረት ተሳቢ

መዋያው ማደሪያው ከግማት ከእጣቢ።

ማነው ያመቻቸው እንዲህ አይነቱን ብልጠት

ለማሳኝ መከራን ለዘራፊ ግነት

ብትውቱን ከታች፣ ከላይ እብሪተኛን

ተንኮልን ከፍ ከፍ፣ ቁልቁል ንጽህናን

ለከሃዲ ሙልሙል፣ ለታማኝ ቅጥቃጭ

ጥቂቱ ተኮፋሽ፣ ብዙሃን ተረጋጭ።

ከቶ ማንን ይሆን የምናማርረው

ፈጣሪን እንዳንል፣ ይህ ክስ የሃሰት ነው

ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ ህሊና እማይፈቅደው።

በአምሳሉ ፈጥሮናል ብለን ተተብተን

እንኳን የሱን ክፋይ፣ ሰው መሆን ሲያቅተን

በገዛ ስራችን በየብጤታችን ባመጣነው ጣጣ

ሌባ ጣት ብንቀስር፣ የግዜር አይን እስቲወጣ

ማምለጫ የለውም ማን እንደሚጠየቅ

ለወደቅንበቱ የስቃይ የንግልት የውርደት መቀመቅ።

ያገር ውስጥ ገሃነብ የገነባን እኛ::

እሳት የሚጠብሳት ነፍሳችንም የእኛ::

መውጫን የዘጋነው ሰይጣኖቹም እኛ::


ሾፐንሃወር በሚባለው የጀርመን ፈላስፋ አባባል ኩርኮራ የተጻፈ

ቱፋ ጥቅምት 2003