አሸባሪውና ኢህአዴግ መራሹ ዘረኛ የወያኔ አገዛዝ በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራር አካላትና አባላት ላይ እያደረሰ ያለውን ወከባ አጠናክሮ መቀጠሉ ተዘገበ
ኢትዮጵያዊያንን በጠመንጃ ሃይል ረግጦና በስልጣን ወምበር ላይ ተፈናጥጦ ለዘመናት መቆየት የሚፈልገው ዘረኛ የወያኔ አገዛዝ እድሜየን ያሳጥራሉ ብሎ የፈራቸውን የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራር አካላት፣ አባላት፣ አክቲቪስቶችና ጋዜጠኞች ሽብርተኞች ናችሁ የሚል ታፔላ እየለጠፈ ወደ ቃሊቲ እስር ቤት በግፍ ሲያጉር እንደቆየ የሚታወቅ ሲሆን ይህኑ ተግባሩን በማስፋፋት፣ በመድረክ አባላት ላይ የሚያደርገውን ማሳደድ አጠናክሮ መቀጠሉ ተዘገበ።
የኢትትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ኢሳት የደረሰው መረጃ ዋቢ በማድረግ እንደዘገበው፣ ኢህአዴግ መራሹ ዘራፊ የወያኔ አገዛዝ የአረና ትግራይ አባል የሆነው አማረ ተወልደ በሁመራ አካባቢ የድርጅቱን ወረቀት ሲበትን ተገኝቷል በሚል ሰበብ ለበርካታ ቀናት በቁጥጥር ስር ካዋለ በሁዋላ በመጨረሻም ንብረቱንና እቃዎቹን ተቀምቶ በሳምንቱ መጨረሳ መለቀቁን ገልጹአል። በተመሳሳይ ዜና የዚሁ የአረና ትግራይ አባል የሆኑት አቶ አያሌው በዬነ በሽሬ ከተማ የፓርቲውን ወረቀት ሲበትኑ ተገኝተዋል በሚል ሰበብ በቁጥጥር ስር መዋላቸውም የታወቀ ሲሆን መምህር ጎይቶም ጸጋየ የተባሉት ደግሞ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ናቸው ተብለው ከስራቸው እንዲባረሩ መደረጋቸው ተገልጹአል።
ባለፈው ሳምንት ፋሽስቱ መለስ ዜናዊ የወያኔ ስብስብ በሆነው ፓርላማ ውስጥ ተገኝቶ ባደረገው ንግግር የመድረክ በርካታ አመራሮች የአሸባሪ ድርጅት አባላት ናቸው ማለቱን ተከትሎ፣ ለሆዳቸው ያደሩ ካድሬዎች በመድረክ አባላት ላይ የሚያደርሱትን ወከባ አጠናክረው መቀጠላቸው ተዘግቦአል። አቶ አያል ጌታነህ የተባሉ በምስራቅ ጎጃም የሚኖሩ የአንድነት ፓርቲ አባልም እንዲሁ ከማንኛውም ማህበራዊ ግንኙነት ለአንድ አመት ታግደው እንዲቆዩ የወረዳው ፍርድ ቤት የወሰነባቸው መሆኑም ታውቁአል።
በተመሳሳይም መልኩ በዚሁ ዞን ውስጥ የሚኖሩት አቶ ሀብታሙ አያሌውና አቶ ዘመድያ አገዘ የተባሉት የፓርቲው አባሎች ካለፈው አንድ ወር ጀምሮ የደረሱበት ያልታወቀ ሲሆን አቶ ሻምበል የሽዋስ ይሁን የተባሉ የምእራብ ጎጃም ነዋሪም ካለፉት ሶስት ሳምንታት ጀመሮ አድራሻቸው መጥፋቱን ለኢሳት የደረሰው መረጃ ያመለከተ ሲሆን፣ መምህር ሙሳ ኢብራሂም የተባሉ የዚሁ ፓርቲ አባልም በድብደባ ህይወታቸው ማለፉ ታውቁአል።
ስልጣንን ያለማንም ተቀናቃኝ የሙጥኝ ያለው የዘረኛና አምባገነኑ መለስ አገዛዝ ከፍተኛ ስጋት እየሆነ የመጣውን ህዝባዊ እንቅስቃሴ ለማፈን እንደመድረክ ባሉ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራር አካላትና አባላይት ላይ ሰፊ ዘመቻ የጀመረ ሲሆን አንዱአለም አራጌ፣ ኦልባና ሌሊሳና በቀለ ነገአን የመሳሰሉት የመድረክ አመራሮች በአሸባሪነት ስም ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል።