ይድረስ ለ‹ደኅንነት›ና ‹ፀጥታ› ባልደረቦች በይሄይስ አእምሮ

የደኅንነትና ፀጥታ መጠበቅ ለአንዲት ሀገር ያለው ፋይዳ መኖርንና አለመኖርን በሚወስን መልኩ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ለዚህም ሲባል ሁሉም የዓለም ሀገሮች ከውስጥም ሆነ ከውጭ ሊሠነዘሩ የሚችሉ የደኅንነትና የፀጥታ ሥጋቶችን ከወዲሁ ለመከላከልና የመከላከል ደረጃንም አልፈው በእውን ቢከሠቱ ትልቅ ጉዳት ሳያስከትሉ ለማምከን ብዙ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ ለዚህ ተግባር ስኬት ሲባልም የደኅንነት(ኢንተሊጀንስ)፣ የፀረ-ደኀንነት(ካውንተር ኢንተሊጀንስ)፣ የምጣኔ ሀብታዊ ደኅንነት (ኢኮኖሚክ ኢንተሊጀንስ) የመከላከያ፣ የፖሊስና ሌሎች የፀጥታ ተቋማትን ገምብተው ከፍተኛ በጀት በመመደብ የሀገርን ድንበርና የሕዝብን ደኅንነት ጥበቃ ያካሂዳሉ፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያም ከውስጥ ከሚመነጩ የፀጥታ ችግሮችና ከድንበር ዘለል ጥቃቶች ራስዋን ለመከላከል የእነዚሁ ተቋማት መኖርና የዘወትር ክትትልና ጥበቃ እንደሚያስፈልጋት የታመነ ነው፡፡ ይህን መሠረታዊ መነሻ በመመርኮዝም የተጠቀሱት መንግሥታዊ ተቋማት በሀገራችን ተመሥርተው በነገሥታቱም ሆነ በደርጉና በአሁኑ የጉግማንጉጉ የወያኔ ዘመነ መንግሥትም ‹አገልግሎት› በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡

ከፍ ሲል የጠቀስኩት ነባራዊ እውነታውን ነው – መሆን ያለበትንና ሊሆን የሚገባውን፡፡ የሀገራችንን ተጨባጭ እውነት ስንመለከት ግን የደኅንነትና ፀጥታ አካላትና አባላት በእርግጥ ወረቀት ላይ የሠፈረላቸውን ሀገራዊና ሕዝባዊ ዓላማና ግብ ለማሣካት ነው ወይ የሚሠሩት? ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው መልስ ቅስማችንን በሚሰብር ሁኔታ በእጅጉ አሣዛኝ ነው፡፡ ‹ዱባና ቅል አበቃቀሉ ለዬቅል› እንዲሉ በወረቀት ላይ የተቀለመው የነዚህ ተቋማት ዓላማ፣ በምርቃታቸው ወቅት የሚገቡት ቃል ኪዳን፣ ሲማሩ የሚቀስሟቸው ነቢባዊና ገቢራዊ ዕውቀቶች ሁሉ ወደሥራው ዓለም ሲሠማሩ በአብዛኛው ይረሱና መላ ትኩረታቸው አልጋና ወንበር በመጠበቅ ላይ ይወሰናል፤ ሕዝቡና ሀገሪቱ በጭራሽ ይዘነጋሉ፡፡ በንጉሡ ዘመን የደኅንነትና ፀጥታ ተቋማት ዋና ዓላማ ዙፋን መጠበቅ ነበር – ዐይኑ ወደዙፋናዊ ሥልጣን የሚያማትርን ወገን ለማጥፋትና ሕዝብን ፀጥ እረጭ አድርጎ ለመግዛት በሚያስችሉ የ‹ካሮትና ዱላ› ዘዴዎች በማድላት ሕዝቡ ከዕለት ኑሮው ባለፈ እንዳያስብ ኮድኩደው ይይዛሉ፡፡ ለግለሰባዊ ሥልጣን ትኩረት ተሰጥቶ ያለ የሌለ የሀገር ሀብት(ሪሶርስ) የሥልጣን ወንበር በማስጠበቅ ግዳጅ ላይ ከዋለ ሕዝብ ይረሳል፤ ሀገር ይቆረቁዛል፤ ድህነት ይስፋፋል፤ ድንቁርና ድንኳኑን እንደተከለ ዝንታለሙን ይነግሣል፡፡ በሀገራችን እየሆነ ያለው ይሄ እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ ከሕዝብ በግብርም ይሁን በሌላ መልክ የሚሰበሰብ ገንዘብ ለሀገር ዕድገትና ብልፅግና ሣይሆን እሚውለው ሕዝብን ራሱን አፍኖ ለመግዛት በሚረዱ የመሣሪያ ግዢና የሰው ኃይል ቅጥርና ሥልጠና ይሆናል፡፡ የሀገራችን አሣዛኝ ታሪክ ዋና መባቀያ የኃጢያት ግንድ እንግዲህ ይሄውና ይሄው ብቻ ነው – የደኅንነትና ፀጥታ ተቋማት ደመወዝ ለሚከፍላቸውና ለወጡበት ማኅበረሰብ ሣይሆን ለጉልበተኛና ወንበዴ ባለሥልጣናት ማጎብደድና ኅሊናቸውን በገንዘብ ወይም በአሁኑ ዐውድ(context) ለዘውገኝነት የዘረኝነት ልክፍት በመሸጥ ማቆሸሽ፡፡ ይህ ሂደት አንድ ወቅት መቆም ይገባዋል – ያ ወቅት ደግሞ አሁን ነው፡፡ ወደዋናው መልእክቴ ልግባ፡፡

የአሁኑ የዓለም ቅርፅ ከወትሮው የተለዬ ነው፡፡ በዱሮ በሬ ማረስም በከፍተኛ ደረጃ እዬቀረ ነው፡፡ በማዕምራን አካባቢ የሚጠበቅ ታላቅ ሚሌኒየማዊ ለውጥ እየመጣ መሆኑ በታሳቢነት እንዲያዝልኝ መፈለጌ እንዳለ ሆኖ ከዚያ በመለስ ግን እኛ ራሳችን በገዛ ፈቃዳችን ለመጠነኛ ለውጦች ዝግጁ ልንሆን ይጠበቅብናል፡፡ የመልእክቴ ማጠንጠኛ ይህች ነች፡፡ የአእምሯችንን ጓዳ ጎድጓዳ እንዳብስና አሮጌ አስተሳሰቦችን በአዲስና በዘመናዊ አስተሳሰብ ለመለወጥ እንዘጋጅ፡፡ የግል ፍላጎት መቼም አይሟላምና ያን ገታ አድርገን አካባቢያችንን በመቃኘት የእሳት ባሕር ወደየደጃችን ሳይመጣ በሩቁ እናስቀረው፡፡

ዓለም እየተቀየረች ነው ብለናል፡፡ ለውጥ ያስፈልገናል ብለናል፡፡ ለውጡ ደግሞ ከአንገት በላይና የተቀባባ ሣይሆን ከአንጀት ሊሆን ይገባል፡፡ ‹ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ፤ አለበለዚያ ድንጋይ ነው ብለው ይወረውሩሃል› ይባላል፡፡ ወጣቶች ደግሞ አንዲት ደስ የምትል አባባል አለቻቸው፡- ‹የአበራሽን ጠባሳ ያዬ በእሳት አይጫወትም› የምትል፡፡ ሁለቱም ማለፊያ ናቸው – ለሚገባው፡፡ ግን ማን ይገባዋል? ችግር ነው፡፡ ብዙዎቻችን ልባችን እንደናቡከደነፆር ልብ ድንጋይ ሆኗል – ጠጥሮ፡፡ በዓለም እየነፈሰ ያለውን የለውጥ ንፋስና በፍጥነት እየተዛመተ የሚገኘውን ሕዝባዊ ማዕበል ማጤን የማይችል ሰው፣ ሰው ሣይሆን ደንቁሮ እንደተወለደ ደንቁሮ የሚያረጅ ግዑዝ ነገር ነው፡፡ የሰው ልጅ ተፈጥሮ ግን ምን ዓይነት የሚገርም ነገር ነው እናንተዬ? እንዴት ነው በወንድሜ መሞት እኔም ልሞት እንደምችል የማልረዳው? ምን ዓይነት አደዳቢ ቃል ኪዳን በዓለም ላይ ቢረጭ ይሆን ሰዎች እስከዚህ ድረስ የማገናዘብ ችሎታችንን የተነጠቅነው?

በአሁኑ የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ሁሉም ለውጥን ይፈልጋል፡፡ ለውጥ የማይፈልግ ሰው ቢኖር የገዢው መደብ ተጠቃሚ አባላትና በተለይ የላይኛው እርከን ባለሥልጣናት ብቻ ናቸው፡፡ ማንኛውም ለውጥ ለነሱ የደኅንነት ሥጋት ምንጭ ነው፡፡ እንደ አሁኑ እንደፈለጉ የሚዘባነኑበትን ሀብትና ሥልጣን ማጣት አይፈልጉምና ለውጥን በቻሉት መንገድ ሁሉ ይዋጉታል፤ 80 ሚሊዮኑ የኢትዮጵያ ሕዝብም በአንዴ ቢያልቅ ደንታቸው አይደለም፡፡ ለነሱ ትልቁ ቁም ነገር ሥልጣንና ገንዘብ ነው፡፡ ለነዚህ ሲሉ ዓለምን እስከማሣለፍ የሚደርስ የጭካኔ ተግባር ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ፡፡ ምናልባት አይፈረድባቸውም፡፡ የነብርን ጅራት ይዞ ማን ይለቃል? ነብሩን ቢለቁት ወደኋላ ዞሮ አለመተናኮሉንስ በምን ማረጋገጥ ይቻላል? ለዚህ ነው የዴሞክረሲ አስፈላጊነት! ያኔ ነብሩም ጅራቱም ሁሉም ይሆንና ጎጂና ተጎጂ አይኖርም፡፡

የድኅንነትና የፀጥታው አባላት ሆይ!

በቃ፡፡ በቃችሁ፡፡ በቃን በሉ፡፡ ወደየኅሊናችሁ ተመለሱ፡፡ እኔ ራሴ ግድያና ማሰቀየት ባልነበረበት የሥራ ክፍል ውስጥ ለአሥር ዓመታት በፀጥታው መዋቅር ተቀጥሬ ሠርቻለሁ – ከ1968 እስከ 1978ዓ.ም፡፡ ወደኅሊናየ ስመለስ ግን ምንም እንኳን ሰውን በመግረፍና በማሰቃየት ባልሠማራም በዚያ ለወንበር ጥበቃ እንጂ ለሕዝብ ባልቆመ ተቋም ውስጥ ማገልገሉ በቁም የመሞት ያህል ተሰማኝ፡፡ እናም በህመም ምክንያትና (ዋሽቼ ማለት ነው – እሱ ይቅር ይበለኝ) እዚያው ይሠሩ በነበሩ የልብ ወዳጆቼ ተራዳኢነት ከመሥሪያ ቤቱ ተሰናበትኩ፤ ብዙም የማውቀው ምሥጢር ስላለነበር አልተወገድኩም – አሁን ድረስ አለሁ፡፡ ከዚያን ወዲህም የሰላም ዕንቅልፍ መተኛት ጀመርኩ፡፡ ይህን ማድረግ ደግሞ ከባድ አይደለም፡፡ በቁም ራስን እየዋሹና ለሥጋዊ መናኛ ጥቅም ሀገርንና ወገንን እየጎዱ ከመኖር ሥራ እንኳን ቢጠፋ ለምኖ መብላት ይሻላል፡፡ ስለዚህ – አዎ፣ ስለዚህ የደኅንነትና የፀጥታ ተቋማት ሠራተኞችና ባለሙያዎች ቀኑ ብዙም ሳይረፍድ በቶሎ ሚናችሁን ለዩ፡፡ ከሁሉም የማያሣፍሩ ነገሮች ውስጥ ትልቁ ወደኅሊና መመለስ ነው፡፡ ወደ ኅሊና መመለስ ወጪው ነፍስና ሥጋን እስከሚለያይ ቢደርስም እንኳን ማፈግፈግ አያስፈልግም – ይዘገይ እንደሁ እንጂ ማንስ ከሞት ሊተርፍ ይቻለዋል? ማንም! ከቆሸሸ ኅሊና ጋር ቢሊየነር ሆኖ በሀብትና በሥልጣን እየተንደላቀቁ ከመኖር ይልቅ ሙልጭ የወጣ ድሃ ሆኖ በደሳሳ ጎጆ ውስጥ ቆሎ እየቆረጠሙ መኖር ብዙ ዋጋ አለው፤ በታሪክም በሃይማኖትም፡፡ ስለሆነም ውድ ባልደረቦቼ – በኔ ይሁንባችሁ – ተመለሱ፤ ልምምጥ እንዳይመስላችሁ፤ ሁላችንንም ተጠቃሚ የሚያደርገን እሱና እሱ ብቻ ስለሆነ እንጂ፡፡ እስክትመለሱምና ባትመለሱም ደግሞ ክፉ ከመሥራት ተቆጠቡ – ሰውን መግረፍና ማሰቃየት፣ የማታውቀውን ሰው በጥርጣሬና ለእንጀራ በተሠለፈ አሳባቂ ሰው ያልተጣጣራ መረጃ ተመርኩዘህ በማሰር የቦካ ቂም እንዳለው ሰው ወፌላላ ሰቅለህ በእልህ መደብደብ ምን እሚሉት ፈሊጥ ነው? በዚህ የሚገኝ እርካታስ የጀግንነት ስሜት ይሰጥ ይሆን? ይህ ዓይነቱ አረመኔያዊ የአውሬ ድርጊት ይቅርባችሁ፡፡ ተፅዕኖ ማሳደር ከቻላችሁና ሠራዊታችሁ ትኩረቱን ከወንበር ጥበቃ ወደ ሕዝብ ካዞረ በዚሁ ሥራችሁ መቀጠሉ የበለጠ መልካም አማራጭ ነው፡፡ እናንተ ያልደገፋችሁት አምባገነን ወንበሩን በሰላም ከማስረከብ ያለፈ ሌላ አማራጭ አይኖረውም፡፡ አምባገነኖች የሚሞላፈጡት በሥራቸው በተኮለኮሉት የደኅንነትና ፀጥታ አካላትና አባላት እየተማመኑ እንጂ እነሱ በራሳቸው የመጨረሻ ፈሪዎችና ቦቅቧቃዎች ናቸው፡፡ አሳምረን እናውቃቸዋለን፡፡ ንግግራቸው አንድ፣ የመጨረሻ ቃላቸው አንድ፤ በሁሉም አንድ ዓይነት ናቸው፡፡ የሦርያውን አሣድ አታዩም? ሰሞኑን ምን አለ? ‹‹ምዕራባውያን ጣልቃ ከገቡ መካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ‹የመሬት መናወጥ› ይከሰታል አላለም?›› ጉረኛ በሉት፡፡ ምንም የመሬት መንቀጥቀጥም ሆነ እሳተ ገሞራ አይነሣም፡፡ እሱን የሚያቀልጥ የእሳት ድኝ ግን ከየትም ይመጣል፡፡ ሣዳምም ‹አሜሪካኖች ባግዳድ መቀበሪያቸው ትሆናለች›፣ ጋዳፊም ‹ትሪፖሊ የምዕራባውያን መርገፊያ ትሆናለች›፣ የኛው መንግሥቱም ‹በቅጽበት ተወርውሮ የሚያጠቃ አንድ ሚሊዮን ጦር በቅርቡ አሠልጥነን ስናበቃ… አንድ ዛፍ አንድ ሰው እስኪቀር ተዋግተን ስናበቃ…አንድ ጥይት እስክትቀር ከገንጣይ አስገንጣይ የወያኔ መንጋ ተፋልመን ስናበቃ…› አሉ፤ አስባሉ፣ ሰማናቸውም፡፡ ግን ሁሉም የዶግ አመድ ሆነው የክብር ቀብር እንኳን እንደተነፈጉ አልፈዋል – (የሞቱት አምባገነኖች)፡፡ ቀሪዎቹም ከዚህ የሚብስ እንጂ የተሻለ ዕድል እንደማይገጥማቸው እናውቃለን፡፡ የመለስ ደግሞ ከሁሉም የከፋ ነው፡፡ ቅጣቱ ከሰው እንዳይመስላችሁ፣ አይደለም፤ እርግጥ ነው ሰው የፈጣሪ መሣሪያ እንደመሆኑ ፍርዱን ለማስፈጸም የሚታዘዙ አሉ – ጊዜው ሲደርስ፡፡ የሰው ሀገር ውስጥ በማታለልና በማጭበርበር ሠርጎ ገብቶ አንዲት የተከበረች ሀገር ከነሕዝቧ መቀመቅ በማውረዱ በመለስ ላይ የሚሰነዘረው ሰማያዊ ቁጣ ማናችንም ከምንጠብቀው በላይ ነው፡፡ ያድርሰን እናየዋለን – ብዙ ሩቅም አይደለም፡፡ ቁናው ተስፈቶ አልቋል፡፡ የቀረው ብድራቱን መሥፈር ብቻ ነው፡፡ ወደላይ አልቅሶ ሳይካስ ቀረ ሕዝብ በዓለም ታይቶ አያውቅም፡፡ እኛም የተለየን አይደለንምና የእርሱው ፍጡራንም ነንና ኢሣይያስና መለስ እንደፈነጩብን አንቀርም፡፡ በሠፈሩት ልክ ይሠፈርላቸዋል፡፡ በቀለኝነትንና እንደሊቢያውያን(ሀሙራቢያውያን ልበላቸው ይሆን?) ጭፍንነትን ግን አደራችንን እንዳንኮርጅ! መጥፎ ነው፡፡ ልብንና ኩላሊትን የሚመረምር ፈጣሪ በቀለኝነትን ይጸየፋልና ብቀላን ለርሱው ለራሱ እንተው፡፡

የሠራዊቱና የደኅንነት አባላት ሆይ!

ለመሆኑ ስንት እንጀራ ነው ምሣችሁን የምትበሉት? ስንት ብርጭቆ ውኃስ ነው የምትጠጡት? ስንት ኪሎ ሥጋ ነው በአንዴ መብላት የምትችሉት? ስንት ጉንጭ መጠጥ ነው በየቀኑ ወይም ሲያሰኛችሁ የምትጎነጩት? ለዚህስ ስትሉ አይደለምን ይህን ሕዝብ በቁሙ ለመግደል የተነሣችሁት? አዎ፣ ሆድ መጥፎ መሆኑን እናውቃለን፤ ግን ለታሪካችሁ ስትሉ በቶሎ ተመለሱ፡፡ ዘር እንዲወጣላችሁ፣ የወለዳችሁም ልጆቻችሁ አንገታቸውን ሳይደፉ በሰው መሃል በኩራት ደረታቸውን ነፍተው እንዲሄዱ ከፈለጋችሁ አሁኑኑ ይህን አፋኝና ዘረኛ መንግሥት ተጠይፋችሁ ተውት – ከቻላችሁም በምትኩ የሕዝቡን ዕንባ የሚያብስ ኢትዮጵያዊ መንግሥት በሕዝብ ይሁንታ እንዲመሠረት የበኩላችሁን ጥረት አድርጉ፡፡ ሞት ሲዘገይ የቀረ ይመስላል እንዲሉ ሆኖ እንጂ የእግዚአብሔር ፍርድ ተጨናጉሎ አያውቅም፤ ቀኑን ጠብቆ ይመጣል፡፡ ጋዳፊን እዩ – ‹ሕዝቡን አነሁልዬ በእግሬ ሥር አድርጌያለሁ፤ የሀብት ምንጮችን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሬያለሁ፤ ተቃዋሚን አጥፍቼያለሁ፤ ከእንግዲህ ማን ሊነካኝ? ሥጋየ ሆይ በይ ያሻሽን አድርጊ፣ አንደበቴ ሆይ በል ያፈተተህን ዘርፍጥ › ብሎ አልነበር? ይገርማል – ጋዳፊ እኮ ከአላህ ቀጥሎ በተባበሩት መንግሥታት መድረክ ሣይቀር አፄ ነበር፡፡ የአፍሪካ መሪዎችንማ ደንበኛ ሎሌዎቹ አድርጓቸው ነበር፡፡ ግን ‹ጊዜ ገቢር ለእግዚአብሔር› እንዲሉ ነውና ይሄውና በናቃቸው ‹ዐይጦች› በዐይጦች መናኸሪያ የውኃ ቦይ ውስጥ ተያዘ – በኢፍትሓዊ መንገድም በሕግ ተላላፊዎች ተገደለ – መሞቱ ትክክል ሆኖ አሟሟቱ ስህተት ነበር፡፡ ለዚህ ነው ከፍ ሲል እኛን ለማስጠንቀቅ የደፈርኩት፡፡ ብድር ሲመላለሱ መኖር ማለት ሲሸኛኙ እንዳደሩት ሞኝ ተሸኛኚዎች መሆን ማለት ነው፡፡

ውድ የሥራ ባልደረቦቼ!

የኛን ሀገር ጉዳይ ከሌሎች ሀገሮች ለየት የሚያደረገው አንድ መሠረታዊ ነጥብ ይታየኛል፡፡ ከሞላ ጎደል ሁሉም የአመራር ቦታ የተያዘው በገዢው መደብ ታማኝ ባልደረቦች ነው፡፡ ይህ መፃጉዕ ሰውዬ ክፉኛ ተጫውቶብናል፡፡ ለያይቶናል – አልተለያየንም ብለን ብንዋሽ ኃጢያት ሠራን፡፡ በዚህ በተመሰቃቀለ ሁኔታ ውስጥ ምን ማድረግ ይጠበቅብናል? ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ለብዙ ትግርኛ ተናጋሪ ወንድሞችና እህቶች የኛ ሀገር ጉዳይ ላም እሳት ወለደች ዓይነት ነው፡፡ ማወቅ ያለብን እርግጠኛ ነገር ግን አንደኛ መለስ ኢትዮጵያዊ መሆኑን እኛ ሳንወድ በግዳችን ብናምንለትም እሱ ግን በአንደበቱም በምግባሩም ኢትዮጵያዊ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ አሳውቆናል (ለኢትዮጵያዊነት ይቆረቆሩ የነበሩ የትግራይ ልጆች የትግል አጋሮቹን እንዴት አድርጎ ከምድረ ገፅ እንዳጠፋቸው ማየት ይቻላል)፡፡ ስለዚህ ትግራይን ከእናት ሀገሯ ለለያት ሰው ያን ያህል መጨነቅ የሚኖርብን አይመስለኝም፤ የለብንምም፡፡ ሀገር ነዋሪ ነው ፣ ግለሰብ ግን ጠፊና ተተኪም ነው፡፡ ይህ ሀገራዊ ምሥል የዛሬ 30 ዓመት አልነበረም ወደፊት የዛሬ 20 ወይም 30 ዓመት ደግሞ ምን ዓይነት ምሥል ሊኖረን እንደሚችል ከመገመት ውጪ በውል ለይተን አናውቅም፤ በእርግጠኝነት መናገር የሚቻለን ግን እንዳሁኑ ሊሆን የማይችል መሆኑን ነው፡፡ ሞኝነትም ሆነ ብልጠት እንደሚወለዱ ሁሉ አርጅተውም ይሞታሉና፡፡ ‹የሞኝ ሰው ምንትስ ካለአንድ ቀን አይበልጥ› ትላለች የሀገሬ ጋለሞታ – ያጋጠማት ቢገጥማት፡፡ እኛ ከዚያ ደረጃ አልፈናል፡፡ የተፈረደብን የመከራ ዘመን ባያበቃ እንጂ አበቅቴው ሲብት ይህ ሁሉ ትርምስና ወጀብ በራሱ ጊዜ ይሰክናል፡፡ ስለዚህ ለማይሞተው የአንዲት ሀገር ዜጎች አንድነት ቅድሚያ መስጠት ይገባናል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ እንደማንኛውም የፖለቲካ ሰው ሁሉ መለስ ቋሚ ወዳጅ የለውም – ቋሚ ጠላት ግን አሉት ፤ ከነዚህም ውስጥ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ዋነኞቹ ናቸው፤ እነዚህ ተቀብረው የማይቀበሩ ኅላዌያት ካልቀበረ የኅሊና ዕረፍተና የሌት ዕንቅልፍ የሚወስደው አይመስልም፡፡ በየዋህነትም ይሁን በዘረኝነት አባዜ ተለክፎ ይህን ሰው አፍቅሮ የገጠጠ ሀገራዊ እውነትን ሸምጥጦ መካድና በሰው ደምና ሕይወት መቀለድ የኋላ ኋላ መዘዙ በቀላሉ የማይነቀል ነው፡፡ ትግራይ አትጎዳም-ኢትዮጵያም እንደታሰበውና እንደተደገሰላት አትሞትም፡፡ የሁሉም ስብራት የሚጠገንበት ዘመንም ይብታል – ሁሉም ከየገባበት ግላዊ የሕይወት አዙሪትና የአስተሳሰብ አረንቋ ሲወጣ፡፡ ስለዚህ ዛሬ ሕይወቱን የምታተርፉለት ይህ የሰይጣን ሥሪት መለስ ነገ በለመደው አክሮባቱ ተገልብጦ የሆነ ቀጭን ሰበብ በመፈለግ እናንተንም ጭዳ ከማድረግ አይመለስምና ከተጠመዳችሁበት ዘውጋዊ ቅምብብ በአስቸኳይ ወጥታችሁ ወደሕዝቡ ግቡ፤ የሚያዋጣችሁ እሱና እሱ ብቻ ነውና፡፡ ምክንያቱም የመለስ ግዛት በደም ግብር የተመሠረተ በመሆኑ ሰውን ካልቀላና ካላረደ መሠረቱ ይናጋል፡፡ አሁን በሥራ ላይ የምትገኙ የሠራዊቱና የደኅንነቱ አባላት ዙሪያችሁን ብትቃኙ መለስ ያሳረደው፣ በልዩ ሥልትም ወደመቃብር የሸኘው ሰው በቅጽበት በዐይነ ኅሊናችሁ ሊመጣ ይችላል፤ ከእናንተም ውስጥ የአንዳንዶቻችሁ ዕጣ ያው ነው፤ የፋሲካው በግ በገናው በግ እየሣቀ መቀጠሉ ጥፋት ነውና በቶሎ ተስተካከሉ፡፡ መለስ የዓዞ ዕንባ እያነባ ወረደ መቃብር የሰደደውን ታጋይ ቤቱ ይቁጠረው፡፡ (ስለኃየሎም አሟሟት በኢትዮሚዲያ የተዘገበውን ያላነበባችሁ እባካችሁ አንብቡት)

ፖለቲካ የሽርሙጥና ሥራ ነው፡፡ ሽርሙጥና አማራጭ ሲጠፋ የሚገባበት መተዳደሪያ ነው፡፡ ሕዝባዊ ሥልጣን ባልተረጋገጠባቸው ሀገሮች የሚገኝ ፖለቲካም ከዚሁ ቆሻሻ ሥራ ተለይቶ አይታይም፡፡ በሥውር ሰውን መግደል ወይም ማስገደል፣ የገደለው ሰው ምሥጢር እንዳያወጣ በሚል ኢሰብኣዊ ሰበብ ገዳዩንና በመስመሩ ያሉ ምሥጢር ዐዋቂዎችን በዘዴ ማጥፋት፣ ተፎካካሪን በሥልት መግደል፣ የምርጫ ኮሮጆን መስረቅ ወይም ቀድሞ በተዘጋጀ ሌላ ኮረጆ መተካት፣ ሕዝብን በጅምላ መግደልና ማሠር፣ ተቃዋሚን ያለፍርድ በጠራራ ፀሐይ አፍሶ ማሰርና እንዳስፈላጊነቱም መግደል፣ አስመሳይ ተቃዋሚ ፈጥሮ በተቃዋሚዎች ውስጥ መለደት*(ከልደቱ ያወጣሁት ግሳዊ ስም ነው)፣ ሕዝብን ማስራብና ሀገርን በትምህርት እንዳታድግ ትውልድን ከዕውቀት ማዕድ መገደብ፣ ሥራ አጥነት እንዲንሠራፋ ማድረግ፣ እውን በማይሆኑ ዕቅዶች ሕዝብን ለማሞኘት መሞከር፣ ማጭበርበርና መዋሸት… ይህ ሁሉ የፖለቲካ ቆሻሻነት የሚገለጥበት የደደቦች ተግባር ነው፡፡ ስለዚህ በፈረንጆቹ አንደበት ‘Politics is a dirty game’ መባሉ ሲያንሰው ነው፡፡ በዚህ የተግማማ ፖለቲካዊ ጉዞ በመግባት ወገንን መጨረስ የነፍስን ድነት ያሳጣል፤ በታሪክ ጥቁር መዝገብም ያጽፋል፡፡ ስለዚህ እስካሁን ለሠራችሁት የአመፃና የበደል ተግባር ተፀፅታችሁ ከአሁን ወዲያ ሕዝቡን ለመካስ ቆርጣችሁ ተነሱ፡፡ አንድ ነገር ደግሞ እንወቅ – እናንተ ከሕዝብ ጋር ወገናችሁም አልወገናችሁም የመለስን ውርደት ማንም ምድራዊ ኃይል አይመልሰውም፡፡ በርሱ የወንጀልና የኃጢያት ሥራ ሰማይ ምድር ተንቀጥቅጠዋል፡፡ እርግጥ ነው ከርሱ አይደለም – ከላከው ነው፡፡ የላከውም የጨለማው ንጉሥ የሠራዊተ አጋንንት አለቃ ሊቀ ሣጥናኤል ነው፡፡ መለስ የአጋንንት ተወካይ መሆኑን ለማጠየቅ ማይምና ጅላጅል ሰዎቹን ከዚያም ከዚህም አጠረቃቅሞ እንደሞሶሎኒ በከንቱ ትምክህት ተወጥሮ እንደአህያ የሚያናፋበትን፣ እንደጣቃም የሚቀደድበትን የፓርላማ ንግግሩንና የእስካሁኖቹን ዕኩይ ተግባራቱን ማጤን በቂ ነው፡፡ ጥጋቡና ትዕቢቱ ለመሆኑ ለከት አለው እንዴ ወገኖቼ? ግን ግን አንድ ነገር – እንዲያው ለመሆኑ ሠላሣ ስንገባ የልጅነትና የወጣትነት ላህያችን መክሰም ለሚጀምረው፣ ዐርባ ስንገባ ፀጉራችን ገብስማ መሆን ለሚጀምረው፣ ሃምሳ ስንገባ ፊታችን መሸብሽብ ለሚጀምረው፣ ስልሣ ስንገባ ትከሻችን መጉበጥና ዐይናችንም የዕይታ ኃይሉን መቀነስ ለሚጀምረው፣ ሰባ ስንገባ ዕጃችን የከዘራን ድጋፍ ለሚማጸነው፣ ሰማንያ ስንገባ አፈር አፈር ለሚሸተን፣ ዘጠና ስንገባ እንደክቡር ፕሬዚደንታችን – እንደሰው ቢያጡ አባባ ግርማ – በዊልቼይር እየሄድን አምባሳደሮችን መሸኘት ለምንጀምረው … ለዚህች አጭር ሰውኛ ሕይወት ይህን ያህል ለሀብት ማጋበስና ለሥልጣን ሽሚያ አቅላችንን ስተን የተራወጥን ዕድሜያችን እንደጥንት አባቶቻችን እንደነማቱሣላና አብርሃም ዘጠኝ መቶና አንድ ሺህ ቢሆን ምን እናሳይ ይሆን???????… ለዛሬ ቢበቃኝስ፡፡
ለገምቢ አስተያየትዎ፡- [email protected]

*በእንግሊዝኛ obama, obamize, obamization,… እንደሚባል በኛም ከልደቱ አያሌው የመጀመሪያውን ስም በመውሰድ፤ መለደት፣ ለድቶ፣ለድተን፣ሊለድቱ፣ ቢለድቱብን፣ ለድተው… ቢባል ለዚህ ‹የሀገር ባለውለታ› ጥሩ ማስታወሻ ይሆነዋል፡፡ ምሣሌ፤ 1. ወያኔ የተቃዋሚዎችን ምሥጢር ለመበሰስ(ለመሰለል) እነሱን መስለው የሚለድቱለትን ሰዎች አሠማርቷል፡፡ 2. አንተ ወደዚህ ፓርቲ የገባኸው ልትለድት እንጂ በፓርቲው አምነህበት አይደለም፡፡ 3. አሁን መንግሥት ቢለድትብን ምን ማድረግ እንችላለን? ቢያንስ እንደመዝናኛ ይሁናችሁ፡፡