ሰሞነኛ ወጋ-ወግ
ዘረኝነት ጥፋት ነው! ዘረኝነት በሽታ ነው! የቅርቡን የአለማችንን ታሪክ እንኳ ብንመለከት በዘረኝነት መሰረት ላይ የሐገራቸውን ስርኣት የገነቡ አገሮች ውድቅት: ታላቅ ከነበረችው ሶቭዬት ህብረት ይጀምራል። ዛሬ ሩሲያ ተብሎ በሚጠራው የቀድሞዋ ሶቭዬት ትልቁ አካል ውስጥ ተደብቆ የነበረው ዘረኝነት ቸችኒያና ታታርስታን ወስጥ መንግስቱንም ሆነ ህዝቡን ቁም ስቅሉን እያሳየው ይገኛል።
ተከባብሮና ተፋቅሮ እየኖረ ነው ይባል የነበረው የሶቭዬቱ ታላቅ ህዝብ ዛሬ እንደውሻ ሲናከስ ይስተዋላል። ጆርጂያ ወስጥ አብሐዚያ በሚባለው አጋማሽ ግዛት ውስጥ ከመፈረካከሱ ወዲህ የራሱን መንግስት መስርቶ ኤኮኖሚውን ከሩሲያ ጋር አስተሳስሮ የራሱን ጦር አቋቁሞ ዘራፍ እያለ ይገኛል::ቼኮዝሎቫኪያ ይባል የነበርው አገር ለሁለት ተሰንጥቆ ከታላቅ የኢንዱስትሪ ባለቤትነት ወደሁለት ራሱን እንኳ መመገብ ያቃተው ጥቃቅን አውሮፓዊ መንግስትነት ተለውጧል: ሌሎች ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል: ታዲያ ይህ ሁሉ ስር የሰደደ ድብቅ ዘረኝነት በየአገሮቹ ህዝቦች ላይ የየራሱን አሻራ ጥሎ እስከመበታተንና ህዝቻቸውን ለረሃብ አለንጋ እስከማጋለጥ አድርሶታል።
በሐገራችንም ወያኔያዊው ስርኣት በመንግስታዊ ፖሊሲ ቀርጾ ካስቀመጠው የዘረኝነት ፖሊሲው ውጪ:የአንድነት ሃይል ተብየው ውስጥ ጎጥኝነትን ያማከለ ፖለቲካ ለማራመድ ግንባር ቀደም የሆነ ሚና የሚጫወቱ እየተስተዋሉ ነው:: በተለያየ መንገድ ላለፉት ሃያ አመታት ቅርፅና ይዘቱ ይለዋወጥ እንጂ ዘረኝነት እንደ ኢንፍሉዌንዛ ካንዱ ወዳንዱ ሲተላለፍ ቆይቷል።
ዘረኝነት በትግሬነት:ዘረኝነት በኦሮሞነት:ዘረኝነት በጉራጌነት ወይም በአማራነት ከመጣ ቋንቋውንና ቦታውን ይለዋውጥ እንጂ ያው ዘረኝነት ነው:: ያንድነት ሃይል ሁሉ ሊዋጋው ይገባል።
በጓዳ ከመንደር ልጅ ጋር ተሰብስቦና ዶልቶ ሌላውን ኢትዮጵያዊ ገፍቶ በኢትዮጵያ ስም መማል ወያኔዎቹ የተጠቀሙበት ያለፈ ስልት ነው::ብርቱካን ሚደቅሳ በአባቷ ኦሮሞ ደሟ ፖለቲካዊ እይታዋን የምንለካ ከሆነና: ብርሃኑ ነጋን በጉራጌው አባቱ ደም ፖለቲካዊ ፓርቲውን የምንመዝን ወይም አኙዋኩን ኦባንግ ሜቶን ኢትዮጵያዊነቱን በዘር ሃረጉ መትረን ልንወስንለት የምናስብ ከሆነ በአንድነቱ ጎራ ቦታ የሚኖር አይመስለኝም:: ላፍታም ቢሆን ይህ አስተሳሰብ ያላችሁ ጊዜው ሳያልፍ ለይቶላችሁ ከዘረኛው ጎራ መቀላቀሉ ለአንድነቱም ጎራ ሆነ ለራሳችሁ እርፍት ይሆንላችኋልና ቢያስቡበት እንመክራለን።
“እዚህ ላይ አንድ ወግ ላውጋችሁ:- እንዼት እንደተፈጠረ እንኳ የማያውቅ ተፈጥሮ ኩሬ ያወረሰችው አንድ አይና እንቁራሪት (ጓጉንቸር) ነበር:: ከኩሬው ጫፍ ላይ አንድ ቋጥኝ አለና እዚያ ቋጥኝ ላይ ደሞ ጠዋት ጠዋት ከእንቅልፉ ሲነቃ ተጎልቶ ፅሃይ ይሞቅበታል: ይህቺ ኩሬው በአለም ላይ ያለች ብቸኛ ውሃም መስላ ትታየዋለች በዚህም ከፍተኛ ደስታ እየተሰማው ይኖራል:: አንድ ጊዜ የውቅያኖስ ማአበል ተነስቶ አንዲት የውቅያኖስ ዔሊን ተራራ አሻግሮ ከኩሬው አጠገብ ይወረወራታል: ታዲያ ያች ዔሊ ውሃ ሸቷት ወደ ኩሬው ስትቀርብ ባለበቱ አንድ አይናው ጓጉንቸር ጠጋ ይላትና አንቺ ለመሆኑ ማነሽ እንዲህ አይነት አፈጣጠር ያለሽ: ከወዴትስ መጣሽ ወደ ኩሬዬ?-ሲል በጥያቄ ያፋጥጣታል:: ረጋ ባለመንፈስ ዔሊዋም እንዲህ ስትል መለሰች “ወዳጄ ሆይ እኔ የውቅያኖስ ዔሊ ነኝ የምኖረውም እንዳንተው ውሃ ውስጥ ነው እናም ማእበል ተነስቶ ከውቅያኖስ አስፈንጥሮ አውጥቶ ወደዚህ ወደ አንተ ኩሬ ጥግ ጣለኝ ስለዚህ ነፍሴን ለማቆየትና ጊዜው ደርሶ ወደውቅያኖሴ እስክመለስ ድረስ ወሃ ያስፈልገኛል ለዚህ ነው ውሃ ሸቶኝ ወደዚህ ኩሬ የተጠጋሁት ትለዋለች:: ለሌላው ፍጡር ጥገኝነት ለመስጠት የተዘጋጀውና እጅግ ልቡ በኩራት ጢም ያለው አንድ አይና:ከቀኝ ወደ ግራ አንገቱን አጠማዞ ያችን ኩሬ ከቃኘ በኋላ ለራሱ እንዲህ ሲል ተመፅደቀ:: እኔ የዚህ ሁሉ ጌታ ነኝ ይህ ኩሬዬ እሷ ከምትለው ውቅያኖስ በብዙ እጅ እንደሚበልጥ ጥርጥር የለውም ያም ሆነ ይህ እስቲ ልጋብዛትና የውቅያኖስዋን ስፋትና መጠን ታሳየኝ ሲል እምቡር ብሎ ዘሎ ከኩሬው ገባና ዔሊዋም እንድትገባ ጋበዛት:: የኩሬውን ሲሶ እንደዋኙ ዔሊ ሆይ የመጣሽበት ውቅያኖስ ይህን ያሕላል?- ሲል ጠየቃት ወዳጄ ሆይ ወቅያኖስ በጣም ትልቅ ነው ስትል መለሰች። ቆይ እስቲ ጨመር አድርጌ ላሳያትና ምን ማለቴ እንደሆነ ትረዳ ሲል ሁለተኛውን ሲሶ ካሳያት በኋላ ይህንንስ ያህላል? ሲል ጠየቃት ደንቁርናው የገባት ዔሊ ምን መሰለህ ወዳጄ እውነቱን ለመናገር ውቅያኖስ እጅግ በጣም በጣም ትልቅና ሰፊ ነው ፅሃይ ሲመታው አድሮ ሲመታው ቢውልና ቢከርም ጥቂት እንኳን አይቀንስም :ያንተ ኩሬ ግን በሰአታት ጊዜ ውስጥ ደርቆ ያንተንም ሆነ ሌሎች ጥገኞችም ካሉህ ሕይወታችሁ አደጋ ላይ ሊወድቅ ስለሚችል አማራጭ ያስፈልግሃል ስትል ትመልስለታለች።
ያ አንድ አይና ጓጉንቸር ወዲያውኑ ደሙ ተንተከትከ ያቺው ያለቺው አንድ አይኑ ጉሽርጥ መሰለች: ከሰማው መማር ያልቻለው ጓጉንቸር ኩሬዋን ቀውጢ አረጋት አምቦጫርቃት “ስሚ አንቺ:-እንዳንቺ አይነት ዋሾ በዚህ ዓለም ላይ ተፈጥሮ አይውቅም ለመሆኑ ውቅያኖስ የሚባል በዓለማችንስ አለ: ማእበል ምናምን እያልሽ የቀባጠርሽውንስ ማን ሊያምን ይችላል? እኔ ከተወለድኩ ከጥንት:(በዘመን ላስላልሽና)ከዛሬ ሁለት ወር ጀምሮ ኩሬዬ ደርቆ አያውቅም!! ከዬት አምጥተሽ ነው እንዲህ ያለ ነጭ ወሬ የምታወሪው? በይ በይ በይ ውጪልኝ ከኩረዬ ሲል በቁጣ ዔሊዋን አባረራት።
ወደ ተነሳንበት ጉዳይ ልመለስና አንድ ሌላ ምሳሌ ልስጣችሁ:-ወያኔ ያን ሰሞን ከኢትዮጵያ ምእራባዊ ግዛት ድንበር ለመስጠት ከሱዳን ጋር ሲደራደር ኤሊባቦረው ተነስቶ የኤሊባቦር መሬት ተወሰደ! ክፌው ተነስቶ የከፋ መሬት ተወሰደ! ወለጌው ተነስቶ የወለጋ መሬት ተወሰደ! ጎጃሜው ተነስቶ የጎጃም መሬት ተወሰደ! ጎንደሬውም ተነስቶ የጎንደር መሬት ተወሰደ! ብሎ የሚጮህ ከሆነ ካንድ አይናው ጓጉንችር በምን ተሻለ? ሌላው ኢትዮጵያዊስ ጉራጌው ሶማሌው አፋሩ ትግሬው ወሎየው ሸዌው ሃረሬው አያገባውም መባሉ ይሆን የሚል ጥያቄስ አይስነሳም? ይህስ ቅርጹን ይለውጥ እንጂ ዘረኝነት አይደለም?
የዘመነ ፊውዳል ታሪክ ተጠቅሶ ለዛሬው ትውልድ የፖለቲካ ማእድ ማጣበቂያ ማድረግስ የምንመኛትን ታላቂቷን ኢትዮጵያስ ሊያቆያት ይችላልን? ሸዋ በኅይለ-ስላሴ ትግሬን ወርሮ ይህን አድርጎ ነበር ጎንደር በቴዎድሮስ ጎጃምን ወርሮ ይህን ፈፅሞ ወጣ:ትግሬ በዮሐንስ ጎጃምን አቃጥሎ ተበቀለ : ወሎ በእያሱ ትግሬና ጎንደር ላይ አባቱን ንጉስ አድርጎ ሾመ እየተባለ አንዱን ባንዱ የአንድነት ሃይል ላይ ላይ ማነሳሳት ዛሬ ላይ ሆኖ ሲታይ ኋላ-ቀርነት ብሎም ያለፈውና የዛሬው ዘመኑ የትቀላቀለበት ከጆሮ ጠገብነት ባላለፈ የሃገሩን ታሪክ የማይውቅ መሃይም ዜጋ ያሰኛል:: በሌላ መልኩም ዘረኝነት ነው; ከዚያ ከላይ ከተጠቀሰውስ አንድ አይና ጓጉንቸር በምን ይለያል? ይህንን መሰል አስተሳሰብ የአንድነቱ ጎራ ሊፋለመው ይገባል እላለሁ።
ትላንት ታልፏል ዛሬ ደግሞ እየተኖረ ነው መጭው ነገንም መተለም ያስፈልጋል። የትላንትናዋ ኢትዮጵያ መልካም ዝና ያተረፉ ነገስታት እንደነበሯት ሁሉ የተዋረደ ታሪክ የነበራቸው ነገስታትም ነበሯት:: አገር:-ቅን የሚያስቡ ዜጎች እንዳላት ሁሉ ወራዳ አዕምሮ ያላቸው ዜጎችም አሏት::እድፍ አስተሳሰባቸው የሚለካበት:-ነገ አገር ብትፈርስ ለሚፈጠሩት ጥቃቅን መንግስታት ሚኒስቴርና አምባሳደር ለመሆን ጭምር ከወዲሁ ዝግጅት ላይ ያሉ መሆናቸው ነው።
ለአገሪቱ አንድነትና ዲሞክራሲያዊ ትግል ቅንጣት ታክል አስተዋፅአኦ የሌላቸው መፍርሷን ጠብቀው ጦር አሰብቀው(ራሳቸው ሳይዋጉ ማለት ነው) በመንደርተኝነት ተጠራርተው ካቢኔ ማቋቋም ደረጃ ላይ ያሰፈሰፉ ጎጠኞች እየተመለከትን ነው እነዚህ ታዲያ ያንድነቱን ጎራ በስወር ደባ እየቦረቦሩት ይገኛሉ መሰረታቸውም ዝረረኝነትን የተመረኮዘ ነው። ቋንቋቸውን ቋንቋችን መሐላቸውን መሐላችን አድርገው ጊዜዋ እስክትደርስ የሚጠብቁትን እድፋጭ መንደርተኞች ከአንድ አይናው ጓጉንቸር በምን እንለያቸዋለን።
አንዱ የአንድነት ቡድን ያቀደው ተግባር ፍሬ ማሳየት ሲጀምር በመንደር ልጅነት ተጠራርቶና ተመሳሳይ እቅድ አውጥቶ በጎን እጅ መንሻ አሞሌ እየሸጎጡ መሰናክል መሆን ጎራ ለይተው በዘር ከተደራጁት ተለይቶ የሚታይ አይደለም።
ዛሬ ላይ ሆነን ያለፈውን ታሪካችንን ስናጤን ከዛሬ መቶ አመት በፊት ከነበሩ አባቶቻችን በምን እንለያለን? ለያንዳንዳችን ይህን ጥያቄ ልተውና: አዲስ አበባ ውስጥ ጃን ሜዳ ላይ ግንቦት 10 ቀን 1901 ዓመተ ምህረት ንጉሰ-ነገስት ምኒሊክ ያሳወጁትን አዋጅ:ታሪክ ዘጋቢያቸው አፈወርቅ ገብረ-እየሱስ ለታሪክ ባቆዩልን ቃል ልሰናበታችሁ፤
ያገሬ የኢትዮጵያ ሰዎች፣ ልጆች፣ ወዳጆች፣ እግዚአብሔር የገለጸልኝን ምክር ልምከራችሁ፡፡ ምክሬንም እግዚአብሔር በልባችሁ እንዲአሳድርባችሁ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
አፄ ቴዎድሮስ የሞቱ ጊዜ ከሳቸው ጋር የነበረው ሰው ሁሉ ያንዱን አገር አንዱ እደርባለሁ አንዱን ገድዬ እኔ ጌታ እሆናለሁ እያለ ሁሉም ላይረባ ተላልቆ ቀረ፡፡
ከዚህም በኋላ የአፄ ዮሐንስ ሰው የኾነውን የምታውቁት ነው፤ ባገር በሽታ ሳይገባበት ሌላ የባዕድ ጦር ሳይነሳበት በምቀኝነት እርስ በርሱ እንደተላለቀ አይታችሁታል፡፡
አሁንም ልጆቼ ወዳጆቼ አንዱ ባንዱ ምቀኝነት ይቅር ያንድን አገር አንዱ እኔ እንደርባለሁ እንዳትባባሉ፡፡ እኔ እስካሁን በፍቅር እንዳኖርኋችሁ እናንተም ተስማምታችሁ በፍቅር እንድትኖሩ እለምናችኋለሁ፡፡
እናንተ አንድ ልብ ከሆናችሁ በምቀኝነት እርስ በርሳችሁ ተዋግታችሁ ካላለቃችሁ በቀር አገራችንን ኢትዮጵያን ለሌላ ለባዕድ አትሰጧትም ክፉም ነገር አገራችንን አያገኛትም፡፡ ነፋስ እንዳይገባባችሁ አገራችሁን በያላችሁበት በርትታችሁ ጠብቁ፡፡ ወንድሜ፣ ወንድሜ እየተባባላችሁ ተደጋገፉ የኢትዮጵያን ጠላት ተጋግዛችሁ ተድንበር መልሱ፡፡» – ዳግማዊ አጼ ምኒሊክ